1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ጉባኤና የፖለቲካ ይትባሐሏ

ሰኞ፣ ኅዳር 3 2005

ዱሀንግ ሻዉ ፒንግ በ1980 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዘወሩት የፀረ-ድሕነት መርሕ፣ ማኦ ዜዱንግ ኮሚንስታዊ ሥርዓት ጋር የዘሩትን የረሐብ፣ ርዛት ሙጃን ከቻይና ምድር ጠራርጎ ካጠፋ ዉሎ አደረ።ቻይናዊዉም ዛሬ በአሜሪካኖች የምቾት ኑሮ ብዙ የሚቋምጥበትን ዘመን አልፎታል።

https://p.dw.com/p/16hWs
Chinese President Hu Jintao delivers a speech during the opening ceremony of 18th National Congress of the Communist Party of China at the Great Hall of the People in Beijing, November 8, 2012. China's outgoing President Hu said the nation faced risk and opportunity in equal measure as he formally opened a congress of the ruling Communist Party that will usher in a once-in-a-decade leadership change. REUTERS/Jason Lee (CHINA - Tags: POLITICS)
ሁ ጉባኤዉን ሲከፍቱምስል REUTERS

አሜሪካኖች በድፍን ዓለም የሚደረግ፣ የሚሆነዉን፣ ድፍን ዓለምን ከሚያዳርሱት ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት አርቀዉ፣ የአብዛኛ ዓለምን አይን-ጆሮ መቆጣጠራቸዉ ለቤጂንግ ፖለቲከኞች ደስታ፣ ይኽ ቢቀር እፎይታ ብጤ ነዉ።ተራዉ ቻይናዊ ቤጂንግ ላይ ከሚሆነዉ ይልቅ ዋሽግተን የሚሆነዉን ሳያዉቅ አይቀርም።ብዙ መታወቅን የሚፈልጉት፣ ሐብት፣ ጉልበት፣ ፊልም፣ ዘፈን ዳንኪራቸዉ ከሚፈልጉት በላይ ብዙ ያሳወቁቿዉ አሜሪካኖች ይኽን አይጠሉትም።ቤጂንጎችም ይወዱታል።የዓለም አንደተኛ ሐብታም-ሐያሎች በዓለም መንፈስ ታጅበዉ መሪያቸዉን በመረጡ ማግስት፣ የሐብት፣ ሕዝባቸዉን ብዛት ለፖለቲካቸዉ መደበቂያ ያዋሉት ቤጂንጎች መሪያቸዉን ሊሰይሙ ጉባኤ ተቀመጡ።ጉባኤዉ መነሻ፤ ዉጤቱ ማጣቀሻ፣ የቻይኖች የፖለቲካ ይትበሐል መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
                        

የመብት፣ ነፃነት፣ የፍላጎት አማራጭ እንዴትነት ከተነሳ በዲሞክራሲ፤ በመብት፣ ነፃነታቸዉ መከበር ዓለም አብነታቸዉ፥ብዙ የሚነገርላቸዉ፥ አሜሪካዉያን ራሳቸዉ የፈለጉትን መሪ ወይም እንደራሴ ለመምረጥ የመወሰን መብት፣ ነፃነታቸዉ በርግጥ ዉስን ነዉ።በሁለት መርሕ የተቸከሉት ሁለት የፖለቲካ ማሕበራት ካቀረቡላቸዉ ፖለቲከኞች አንዱን ከመምረጥ፣ ወይም ሁለቱንም ካለመምረጥ ሌላ ሌላ ምርጫ የላቸዉም።


ዉስኑን መብት ነፃነት አሜሪካ-ምዕራብ አዉሮጶኖች ሲያደርጉት በቴሌቪዥን-ራዲዮ ከማየት ባለፍ (ያዉም አቅሙ ካለዉ) በየሐገሩ የማያቀዉ የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብ በአሜሪካኖች ወይም በምዕራብ አዉሮጶች የመተመቸ ኑሮ፣ በመብት ነፃነታቸዉ መከበር እንደቀና፣ ያን ሥርዓታቸዉን እንደናፈቀ በየገዢዎቹ በጎ ፍቃድ የቆየባትን ምድር መሰናበቱ ግን ሐቅ ነዉ።ሐቁ በርግጥ አሳዛኝ።

ዱሀንግ ሻዉ ፒንግ በ1980 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዘወሩት የፀረ-ድሕነት መርሕ፣ ማኦ ዜዱንግ ኮሚንስታዊ ሥርዓት ጋር የዘሩትን የረሐብ፣ ርዛት ሙጃን ከቻይና ምድር ጠራርጎ ካጠፋ ዉሎ አደረ።ቻይናዊዉም ዛሬ በአሜሪካኖች የምቾት ኑሮ ብዙ የሚቋምጥበትን ዘመን አልፎታል።


በፖለቲካዉ መስክ ግን እንደ ብዙዉ የዓለም ብጤዎቹ ሁሉ የኦባማ-ሮምኒን የምረጡኝ ዘመቻ፣ የቴሌቪዥን ሙግት፣ ክርክር፣ የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች ሥለየእጩዎቹ መርሕ፣ አለማ፣ ሥብዕና የመዘገብ መብት፣ ነፃነታቸዉን ሥፋት፣ የመራጩን ነፃነት ገደብየለሽነት ሲመለከት ግን ቻይናዊ እንደ ምጣኔ ሐብቱ ሁሉ በፖለቲካ፣ ሰብአዊ መብት ነፃነቱም አሜሪካኖች ከደረሱበት ለመድረስ፣ ማሰብ መመኘቱ አይቀርም።

የአብዛኛዉን ቻይናዊ ምኞት ፍላጎት ለማንፀባረቅ የሞከሩ አልጠፉም።ፍፃሜያቸዉ ግዞት፥ ወሕኒ ቤት ወይም ስደት መሆኑ እንጂ ዚቁ።ቻይናን ከስልሳ ዘመን በላይ የገዛዉ ኮሚንስት ፓርቲ ተወካዮች ወትሮም የሚታወቀዉን የወደፊት መሪ ለመምረጥ ቤጂንግ ለመሰብሰብ ሲዘጋጁ፥ ከግዞት፥ እስራት፥ ስደት የተረፉ የመብት፥ ነፃነት ተሟጋቾች እየተለቀሙ ታስረዋል።

በዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የእስያ ተወካይ ሮዚያን ሪፍ እንዳሉት ጉባኤዉ ከመጀሩ በፊት ብቻ አንድ መቶ ሠላሳ የመብት ተሟጋቾች አንድም ታስረዋ።ወይም እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል።
                
«ከአንድ መቶ ሠላሳ የሚበልጡ ሰዎች አንድም መታሰራቸዉን፥ አለያም እገዳ የተጣለባቸዉ መሆኑን የሚገልፅ ዘገባ ደርሶናል።እነዚሕ በግዳጅ ከመኖሪያ ቀዬ ከመነሳት በሐይማኖትና በጎሳዎች ላይ እስከ ተጣለ ገደብ ያሉ የተለያዩ ጉዳዮችን ለማንሳት የሚሞክሩ ሰዎች ናቸዉ።በዚሕ የለዉጥ ጊዜ ሰዎች የሚጠብቁት በፖሊሲዎች ላይ ለዉጥ እንዲደረግ ነዉ።እነሱ ያነሱት ይሕን ነዉ፥ መጨረሻቸዉ አፋቸዉን ማዘጋት ሆነ-እንጂ።»

ለቲቤቶች የአሜሪካኖች የኢኮኖሚ፥ ፖለቲካ፥ የፕረስ ነፃነትን ማግኘት አይደለም መመኘቱ ራሱ ቅንጦት አይነት ነዉ።ኮሚንስታዊት ቻይና ሐገራችንን በሐይል ይዛለች፥ ሐይማኖታዊ፥ ሰብአዊ መብታችንን ደፍልቃለች የሚሉት የተራራማይቱ ግዛት ነዋሪዎች እስከ ሰሞኑ እንደሚያደርጉት ሁሉ በጉባኤዉ ዋዜማ ብሶት ተቃዉሟቸዉን ለማሰማት አንድ ሁለት ማለታቸዉ አልቀረም ነበር።አካባቢዉን ያጥለቀለቀዉ ፀጥታ አስከባሪ እንቅስቃሴዉን ሰጥ-ለጥ፥ ለማድረግ አፍታም አልፈጀበት።

ከጠንካራዉ የፀጥታ አስከባሪዎች እጅ ካልገቡት መሐል አራቱ ባለፈዉ ሮብ እራሳቸዉን በእሳት አጋይተዉ ገደሉ።በማግስቱ ሐሙስ የትም፥ ምንም እንዳልሆነ ሁሉ የታታላላቆቹ ኮሚንስቶች ታላቅ ጉባኤ፥ ከትልቂቱ ከተማ ትልቅ አዳራሽ ተጀመረ።ቤጂንግ።
                  
በሰላሳ አንዱ ክፍለ-ግዛቶች በሚገኙ መስሪያ ቤቶች፥ በየፋብሪካ፥ ኩባንያዉ፥ በየአገልግሎት መስጪያዉ እና አካባቢዉ በሚሊዮን በሚቆጠሩ መሠረታዊ ድርጅቶች በጥብቅ የተማገረዉ ኮሚንስታዊ ፓርቲ ከሰማንያ ሁለት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።1.3 ቢሊዮን የሚገመተዉን ሕዝብ ይወክላሉ የሚባሉት የፓርቲዉ አባላት የመረጧቸዉ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ስልሳ-ስምንት ፖለቲከኞች የዘንድሮ በጉባኤ ተሳታፊዎች ናቸዉ።

ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ከታላቁ አዳራሽ አካባቢ ከጉባኤተኞች በስተቀር «ወፍ ዝር አይልም።» በአዳራሹ በኩል የሚያልፉ ባለ ታክሲዎች የኋላ በር-መስኮታቸዉን እንዲቆልፉ ታዘዋል።ምክንያት ተንኮለኛ ተሳፋሪ ድንገት ዘሎ ወደ አዳራሹ እንዳይጠጋ።በታላቁ አዳራሽና ባካባቢዉ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚበር መጫዎቻ ወይም አርቴፊሻል አዉሮፕላን ማብረር፥ የላስቲክ ፊኛ ማንሳፈፍ፥ የቴኒስ ኳስ መወራወር ጨርሶ አይቻልም።

ሌላ ቀርቶ አንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት ቤጂንግ ዉስጥ ሴንጢና ቢላ መሸጥ ተከልክሏል።የዚያን ቀን ጠዋት አዳራሹ ዉስጥ መዝሙሩ ገና እየተንቆረቆረ ነበር።
                   

ካዳራሹ ዉጪ። ሴትዮዋ  በየሰወስት-አራት ሜትሩ የተገጠገጡትን ፖሊሶች ያለፈችበት መንገድ አይታወቅም።ብቻ እየሮጠች ካዳራሹ በቅርብ ርቀት ከሚገኘዉ ከታሪካዊዉ የታይናሚን አደባባይ ደረሰች።አደባባዩ መሐል ቆማ ወረቀት ስትበትን ፖሊስ በቅፅበት ማንቁርቷን ይዞ ከመኪናዉ ወረወራት።የሴትዮ ስም-አይታወቅም።አድራሻ አታወቅም።ወይም ፖሊስ ነዉ የሚያዉቀዉ።

አለማዋ-ስትጮሕ የሰሙ እንዳሉት-ጉባኤተኞቹን መቃወም ነዉ።«ሽፍቶች፥ሌቦች» ብላለች»-አሉ ሰማናት ያሉ።የኮሚንስት ፓርቲዉን መሪዎች ዘራፊ፥ ሌባ የሚለዉ ቻይናዊ ተበራክቷል።እርግጥ ነዉ ዱሀንግ ሻዉ ፒንግ የማኦዋን ቻይናን የምጣኔ ሐብት መርሕ እንደ ጥሩ ባለ እጅ አግለዉ፥ ጨፍልቀዉ፥ ሞርደዉ ሐብት የመሚዛቅበት አካፋ ሲያደርጉት «ድመቷ አይጥ እስከያዘች ድረስ ጥቁር ትሁን ነጭ ጉዳያችን አይደለም» ነበር ያሉት።የትም-ፍጪዉ ዱቄቱን አንጪዉ አይነት።

በዱሐግ የምጣኔ ሐብት መርሕ የተገኘዉ ሐብት የመላዉን ቻይናዊ ሕይወት ኑሮ፥ መቀየሩ አላጠያየቀም።የሴትዮዋን የቅፅበት ጩኸት ሊሰሙ ቀርቶ መኖሯንም የማያዉቁት ፕሬዝዳንት ሁ ጂንታኦ ለጉባኤተኞቹ እንዳሉት በዱሐንግ መርሕ እስካሁን የተገኘዉ ሐብት፥በመጪዉ ስምንት ዓመታት አሁን ካለዉ በእጥፍ ይጨምራል።
          
«የቻይናን ምጣኔ ሐብታዊ እድገት ተመጣጣኝና ዘላቂነት ለማድረግ ባለን ፍላጎትና ዕቅድ መሠረት የሐገሪቱን አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት እና አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢን እስከ 2020 ድረስ በእጥፍ ማሳደግ አለብን።»   

የፊታችን ሐሙስ የፕሬዝዳትነቱንና የኮሚንስት ፓርቲዉን የዋና ፀሐፊነት ሥልጣን ወይም ከሁለት አንዱን ለምክትላቸዉ የሚያስረክቡት ሁ ጂንታኦ ሥለ ምጣኔ ሐብቱ እድገት ያሉ-ያቀዱትን ተጀታዮቻቸዉ ገቢር ያደርጉት ይሆናል።ፖለቲካዉ በኮሚንስታዊ ሥርዓት እንደተማገረ ከተትረፈረፈዉ ሐብት ብዙ የሚጠቀመዉ ማነዉ-ነዉ ነዉ-ጥያቄዉ።

የጥያቄዉ መሠረት፥ በ1989 የለዉጥ ፈላጊ ተማሪዎች ጥያቄና አመፅ ከተደፈለቀበት አደባባይ ባለፈዉ ሐሙስ ብልጭ-ከማለቷ ድርግም ያለችዉ ሴትዮ ስድብ፥ የአብዛኛዉ ቻይናዊዉ ሐሜት-ትችት፥ የምሑራን ወቀሳ ምክንያትም ከተገኘዉና ከሚገኘዉ ሐብት ጠቀም ያለዉን የሚዝቁት የኮሚንስት ፓርቲዉ ትላልቅ መሪዎች መሆናቸዉ ነዉ።

ሁ የኮሚንስት ፓርቲዉ ሹማምንታት የሚከብሩ፥ የሚደላቀቁበትን ሙስናን የወደፊቱ መንግሥት ካልጠፋ አጠቃላይ ሥርዓቱ መናጋቱ እንደማይቀር መናገራቸዉ ማስፈራራታቸዉም አልቀረም።
                
«ችግሩን መቆጣጠር ካልቻልን፥ ለፓርቲዉ መጥፎ አብነት፥እንዲያዉም ለፓርቲዉና ለመንግሥት ተያይዞ መዉደቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል።»

ሁ ባለፉት አስር ዓመታት ያላደረጉትን ከእንግዲሕ እንዴት እንደሚያደርጉት ማወቁ ሲበዛ ከባድ ነዉ።ባጭር ጊዜ በምጣኔ ሐብት ጉልበቷ ከዓለም የሁለተኝነቱን ደረጃ የያዘችዉ ቻይና ብዙ የፖለቲካና የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት በምጣኔ ሐብቱም፥ በፖለቲካዉም መስክ የተሐድሶ ለዉጥ ያሻታል።

ሁ እስከ ዛሬ አላደረጉትም።ወይም አልቻሉም።የእሳቸዉ የታላቅ መሪነት ዘመን አብቅቷልም።ሁን እንደሚተኩ የሚታመነዉ ሺ ቺ ፒንግ የሃያ-አንደኛዉ ክፍለ-ዘመን ዱሐንግ መሆን አለመሆናቸዉ ግን አይታወቅም።በቦን ዩኒቨርስቲ የቻይና ፖለቲካዊ ጉዳይ አጥኚ ጉ ሹ ቩ እንደሚሉት ቻይና ለዉጥ ማድረግ አለባት።

ሺ ወይም ሌሎቹ የኮሚንስት ፓርቲዉ መሪዎች ግን መሠረታዊዉን የተሐድሶ ለዉጥ ቀርቶ ሙስናን መቆጣጠሩን እንኳን የፖለቲካ አዋቂዉ እንደሚሉት አይፈልጉትም።በሁለት ምክንያት፥- ለዉጡ ሥልጣናችንን ያሳጠናል-የሚለዉ አንድ፥ ሙስናን መዋጋቱ ሐብታችንን ያሳጣናል የሚለዉ ፍርሐት ሁለት።                

        
«ቻይና የፖለቲካ ተሐድሶ ማድረግ አባት።ይሕ አሁን በሁሉም ዘንድ ይታወቃል።ለዉጡ የማይደረግበት ምክንያት ግን ለዉጥ ከተደረገ ሐብቱ መከፋፈል ሥለሚኖርበት ነዉ።ገንዘቡ ያላቸዉ ባለሥልጣናት እንዲሕ አይነቱን ለዉጥ አይፈልጉትም።»

ለማኦ ዜዱንግ ተራዉ ዜጋቸዉ የሚመኘዉ ያ የአሜሪካና የምዕራብ አዉሮጶች ሥርዓት «ሰዉ በላ፥ ኢምፔሪያሊት» ሐብት ጉልበቱ ደግሞ «የወረቀት ላይ ነብር» ነበር።ለዱሐንግ ግን የኢምፔሪያሊስቶቹ የመክበሪያ ሥልት መርሕ ጠቃሚ፥ ሕዝብን መቀለቢያ፥ ሐይል ጉልበት ማጠንከሪያ ብልሐት ነዉ።ሁ በወጣትነታቸዉ ከመለመለቿዉ ከዱሐንግ የተለየ መርሕ-እምነት አላራመዱም።

የማዖዋ ቻይና እንደተለወጠች ሁሉ የደሐንጓ ቻይናም ብዙዎች እንደሚሉት መለወጥ አለባት።ሺ-የዓለምን ሁለተኛ ምጣኔ ሐብት የምትቆጣጠረዉን ትልቅ ሐገር የመለወጥ ፍላጎት፥ አቅም፥ ብልሐቱ ይኖራቸዉ ይሆን?።ላሁኑ ሺን የሚሰይመዉ ጉባኤ በዝግ መቀጠሉ ነዉ-እርግጡ።የወደፊቱን ለማየት-መስማት ያብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ


















 

Tibetan exiles stand in silence with a portrait of their spiritual leader the Dalai Lama along with other posters seeking United Nations intervention on the alleged torture and cultural genocide on Tibetans inside Tibet, during a campaign in Kolkata, India, Monday, Sept. 3, 2012. According to London-based Free Tibet, 51 Tibetans have died of self-immolations protesting against the Chinese rule since 2009. (Foto:Bikas Das/AP/dapd).
የቲቤቶች ጥያቄምስል AP
Military delegates leave the Great Hall of the People, the venue of the 18th National Congress of the Communist Party of China, after the opening ceremony, in Beijing, November 8, 2012. REUTERS/David Gray (CHINA - Tags: POLITICS)
ጉባኤተኞችምስል Reuters
Hotel guides pose for a photo in front of the Great Hall of the People, the venue of the 18th National Congress of the Communist Party of China, in Beijing, November 8, 2012. REUTERS/David Gray (CHINA - Tags: POLITICS)
ከአዳራሹ ዉጪምስል Reuters
A general view showing delegates attend the opening ceremony of 18th National Congress of the Communist Party of China at the Great Hall of the People in Beijing, November 8, 2012. REUTERS/Carlos Barria (CHINA - Tags: POLITICS)
ጉባኤዉምስል Reuters