1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዋስ ግንድ ምርምርና «ዶሊ»፣

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2005

ፊዚክስ፤ የሥነ ፍጥረትን ምሥጢር ፤ ፍጥረተ ዓለም የተዘረጋበትን የተፈጥሮ ህግጋት ፤ደንቦችና የመሳሰለውን ለማወቅና ለመመራመር የሚረዳ የዕውቀት ዘርፍ ነው። ሥነ ቅመማ ፣ የተፈጥሮ ማዕድናትን የተናጠልና ውሁድ ባህርይ ለማወቅ ፤ የሚበጅ ወይም የሚያጠፋ ንጥረ ነገር ለመቀመም የሚያስችል ነው።

https://p.dw.com/p/17diF
ምስል picture-alliance/dpa

ሥነ ህይወት፣የኅልውናን ምሥጢር ፣ የኅዋሳትን አሠራር ፤ የህክምናው ረድፍም፤ እንከኖቹን ለመመርመርና አብነቱን ለማግኘት የሚያስችለውን የምርምር በር ይከፍታል።

ሁሉንም፣ በተለያየ መልኩ የሚያስተሳስራቸው ሁኔታም ሰፋ ያለ ነው።

ምንም እንኳ፤ በዓለም ዙሪያ 65 ከመቶ ያህል የሰው የጤና ጠንቅ ፤ ከሥነ ልቡና የመነጨ ሳይሆን እንዳልቀረ ቢነገርም። የአካልን የውጭና የውስጥ ደዌ ለመፈወስ የህክምና ሳይንስ እንደሚበጅ የታወቀ ነው። የህክምና ሳይንስ ፣ በሥነ- ቅመማና ፊዚክስም እንደሚደገፍ የታወቀ ነው። የህክምና ሳይንስ ካተኮረባቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ፤ በእንጭጭ ላይ ያለን ኅዋስ፤ በሰውነት ውስጥ ፣ በአጠቃላይ እንደሚገኙት 220 የተለያዩ ዋና -ዋና ኅዋሳት --ማዳበር ነው፤ እንደ ደምና የአንጎል ኅዋሳት የመሳሰሉትን ማለት ነው።

Demonstranten mit Schafs-Masken
ምስል AP

አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ወይም ተመራማሪዎች ያሳደሩት ዐቢይ ተስፋ፤ በኅዋሳት በተለይም የኅዋሳት ግንዶች በሚባሉት ላይ የሚደረገው ምርምር፤ ለተለያዩ ተውሳኮች በተለይም እጅግ አደገኞች ወይም ጠንቀኖች ከሆኑት በሽታዎች መካከል፤ የልብ ድካምን ፣ የስኳር በሽታን፤ መጃጀትን፤ መርሳትን የማስተዋል አቅም ማጣትንና የመሳሰሉትን ለመቋቋምም ሆነ ለመፈወስ ያስችላል የሚል ነው። በአንድ በኩል ይህን የመሰለ ተስፋ ቢኖርም፤ በሌላ በኩል፣ ተማራማሪዎች ከእንስሳትም አልፈው በሰው ጽንስ ላይ ሥነ ምግባርም ሆነ ሞራል የጎደለው ተግባር እንዳያካሂዱ ብርቱ ሥጋት አለ። አሥጊ የሚሰኘው በእርግጥ ምን ዓይነት ምርምር ቢሆን ነው?

ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ -ጊዜ በጨረፍታም ቢሆን እንዳወሳነው፣ በሽታን ከሥር ከመሠረቱ ለመቋቋም ይበጃል በማለት አብነቱን በኅዋሳት ላይ በመጣል ፤ በተፈጥሮ ጽንስ ላይ ሰው ሠራሽ የምርምር እርምጃዎችን መወሰዳቸው አልቀረም። ለዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ ፤ እ ጎ አ ሐምሌ 5 ቀን 1996 ዓ ም እንደተወለደች የተነገረላትና በ 6 ዓመት ከመፈንቅ ዕድሜ ገደማ፣ በሳንባ ምች ሳቢያ የካቲት 14 ቀን 2003 ዓ ም፣ የሞተችው፤ በቤተ ሙከራ የተፈጠረችው ማለት ይቻላል፣ «ዶሊ» ትባል የነበረችው እንስት በግ ሁኔታ ነው። በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በተለመደው ተፈጥሮአዊ ርቢ ሳይሆን፣ እስኮትላንድ ውስጥ ፤ በኢድንብራ ዩንቨርስቲ፣ ሮስሊን በተሰኘው የምርምር ተቋም ፣ በቤተ ሙከራ ከሽል፣ የራሷ የዘር ቅጂ እንዲኖራት ተደርጋ በሰው ሠራሽ መነገድ ነፍስ የዘራች በግ ነበረች። በሌላ አገላለጽ፤ በሰው ሠራሽ ጥበብ፤ ፍጹም ተመሳሳይ መንትያ ያላት ሆና እንድትገኝ ነበረ የተደረገው። በዚህ መንገድ፤ መንትዮቹ፤ አንድ ዓይነት የማንነት መለያ ዘር (DNA) እንዲኖራቸው ይደረጋል ማለት ነው።

Ian Wilmut - "Vater" von Klonschaf Dolly
ምስል AP

በህይወት ዘመኗ 3 ግልገሎች (4 መሆናቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ይጠቁማሉ)ያፈራችው «ዶሊ» ፣ ከሞተች፣ ነገ የካቲት 7 ቀን 2005 (እ ጎ አ የካቲት 14 ,2013፣ የቫለንታይን ዕለት)10 ዓመት ይደፍናል ማለት ነው። ለነገሩ በጎች፤ በአማካዩ ዕድሜአቸው ከ 10 -12 ዓመት መሆኑ ነው የሚነገረው። በጎች ፤ ዕድሜአቸው ረዘመ ቢባል ከ 20 ዓመት በላይ አይኖሩም።

ለማንኛውም፤ ዶሊ የዕድሜ ባለጸጋ አልነበረችም። በተፈጥሮ ሳይሆን፣ በሰው ሠራሽ መንገድ በመወለዷ ይሆን!? አነጋጋሪ ከሆኑት ጥያቄዎች አንዱ ነው። የሮስሊን ተቋም ባልደረባ ዶክተር ሃሪ ግሪፍን እንደሚሉት ከሆነ ፣ በዕድሜ የገፉ በጎች በተለይ በቤት የሚውሉም ሆኑ የሚኖሩ በጎች ይበልጥ ለሳንባ ምች ይጋለጣሉ። ለዶሊ መፈጠር ፕሮጀክቱን በመምራት አስተዋጽዖ አድርገዋል ከሚባሉት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ፣ፕሮፌሰር ኢያን ዊልመት፣ ዶሊ፣ ያለዕድሜዋ መሞቷ ፣ አንድን ሽል ድርብ ወይም የራሱ የዘር ቅጂ እንዲኖረው አድርጎ ለህይወት የማብቃቱ ቴክኒክ፣ ጉድለት እንደታየበት ነበረ፣ በበኩላቸው የተናገሩት። ይኸው እንከን ደግሞ፣ ዶሊን ለመፍጠር የተደረገው ዓይነት የምርምር ተግባር በሰው ጽንስ ላይ እንዳይቃጣ ማስጠንቀቂያም ሆነ ማሳሰቢያ መሆኑን ፣ የምርምርና የሞራል ጉዳይ ጸሐፊ፣ ዶክተር ፓትሪክ ዲክሰን አስገንዝበው ነበር። ፕሮፌሰር ኢያን ዊልመት እንዳብራሩት፤ የዶሊ ፕሮጀክት እንዲሳካ 66% አስተዋጽዖ ያደረጉት ባለፈው ጥቅምት መባቻ በ 58 ዓመታቸው ያረፉት ፣ የዚሁ ፤ የሽል ማራባት ተመራማሪ ቡድን ባልደረባ ፕሮፌሰር Keith Campbell ነበሩ።

ከዶሊ በኋላ፣ በሽል ላይ የሚደረገው ምርምር እየተጠናከረ ከመጣ ወዲህ ፤ እንግሊዛዊው የሥነ-ህይወት ተመራማሪ ጆን ገርደን እና ጃፓናዊው የኅዋሳት ተመራማሪ ፣ ፕሮፌሰር Shinya Yamanaka ፤ በህክምና ምርምር ፣ እ ጎ አ የ 2012 የኖቤል አሸናፊዎች ለመሆን መብቃታቸው የሚታወስ ነው።

Symbolbild Stammzellenforschung Mensch DNA
ምስል AP

የሥነ ህይወት ና ሥነ-ህክምና ተመራማሪዎች፣ በኅዋሳት፣ በተለይም በኅዋስ ግንድ (Stem Cell) በተሰኘው ላይ ምርምራቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ ናቸው።

የኅዋስ ግንድ ፣ የሚባለው ምንጩ፤ ጽንስ ወይም የዐዋቂዎች፤ ጡንቻ ነው።

እንደ ካንሠር(ነቀርሳ) ኅዋሳት ሁሉ፤ ጤናማ ኅዋሳት፣ በሰውነት ውስጥ በአቅድ፣ ወይም ሥርዓት ይዘው ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ናቸው። ለአያንዳንዱ የአካል ዓይነት፣ ለምሳሌ ያህል፤ የቆዳ፣ አንዠት ፤ የሆድ ዕቃ ግድግዳ ፤ ፀጉር፤ ቀይና ነጭ የደም ኅዋሳት ወይም፤ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ኅዋሳት በጥቂት ሺ የሚቆጠሩት ናቸው በሥርዓት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርጉት። እነዚህ የኅዋሳት ግንድ በመባል የታወቁት የሰውነት አካላት ኅዋሳት፤ (ሴሎች) ሲከፋፈሉ፤ እጅግ በማዝገም ነው። ሰውነታችን የሆነው ሆኖ ፣ በየዕለቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ ኅዋሳት ያስፈልጉታል። የኅዋሳት ግንዶች ግን፣ መቅድማዊ ኅዋሳትን ከገነቡ በኋላ፤ እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት፤ በመከፋፈል በሠራ አካላት፣ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎቻቸውን ይወጣሉ።

Laborantinnen arbeiten mit Stammzellen
ምስል AP

ስለኅዋሳት ግንዶች የሚደረገው ምርምር ተጠናክሮ እንደመቀጠሉ መጠን፣ በአብያተ ሙከራ፤ ለጥገና የሚበጁ፤ ተተኪ አካላትን ፈጥሮ ከአንዱ ወደ ሌላው ሰው ለማዛወር ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ በቅርቡ የሰውን የፅንስ ኅዋስ ግንድ በ 3 ማዕዘናዊ መልክ ቀርጾም ሆነ አትሞ ማሳየት መቻሉ ተረጋግጧል። በዚህ ረገድ የሚደረገው ምርምር የሚቀጥል ሲሆን፣ የሳይንስ ጠበብቱ በዚህ ረገድ፣የሚደረገውን የምርምር ሥነ-ቴክኒክ በተሟላ ሁኔታ ሥራ ላይ ማዋል ሲጀምሩ፣ የሰዎችን የተለያዩ ጡንቻዎች በተለያዩ የኅዋሳት ግንድ ተክቶ በማፋፋት የተለያዩ የአካላት መዋጮ የሚያደርጉ ሰዎች ጥረት ወይም በእንስሳት ላይ ፣ በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚደረገው ምርምር ፣ ሁሉም እንዲቀር አስተዋጽዖ ይኖረዋል ነው የሚሉት። ይህም ሲሆን በግንድ ኅዋሳት እንከን ያለበትን ልብ፤ ሳንባንም ሆነ ኅብለ-ሠረሠርን ማደስ ይቻላል ማለት ነው።

የአእምሮን የማስተዋልም ሆነ የማስታወስ ችግር ለመክላትና ብሎም ራሰ-በራነትን ከሥር ፣ ከመሠረቱ ለማስወገድ ፣ ይኸው የምርምር ሥነ-ቴክኒክ አለኝታ እንደሚሆን፣ ተመራማሪዎቹ ጠበብት ይናገራሉ። ጃፓናውያን ተመራማሪዎች፤ ለምሳሌ ያህል፣ የሰው የኩላሊት ጡንቻ፣በኅዋሳት ግንድ አማካኝነት ከመሠረቱ ታድሶ እንዲያድግ ማድረግ መቻሉን፤ የገለጡ ሲሆን ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ በኩላሊት ተግባር ማከናወን አለመቻል ለሚሠቃዩ ሰዎች፣ ብሩኅ ተስፋ ማስጨበጡን ፣ በኪዮቶ ዩንቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ኬንጂ ኦሳፉን የተባሉት ሳይንቲስት አስታውቀዋል።

በአውሮፓና በዩናይትድ እስቴትስም ይኸው በኅዋሳት ግንዶች ላይ የሚደረገው ምርምር ተጠናክሮ ነው የቀጠለው። አንዳንድ የዩናይትድ እስቴትስ ተማራማሪዎች፤ የቤተ-ሙከራው አሠራር እንዲከሽፍ በሚደረግ ፅንስ ላይ ያተኮረ ነው በማለት ቅሬታቸውን ቢያሰሙም፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በፅንስ የኅዋሳት ግንድ ላይ ምርምር እንዲቀጥል መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማም ሆነ እርዳታ መግታት እንደማይቻለው ታውቋል።

Großbritannien Embryo Stammzellenforschung
ምስል AP/RBM ONLINE/LIFE SCIENCE CENTER

ከጊዜ ወደ ጊዜ በረቀቁ የሥነ-ቴክኒክ መሣሪያዎች እገዛ ጭምር የተስፋፋው ምርምር በተለይ በሰው ጽንስ ላይ የሚደረገው --ገደቡ ዬት ላይ ነው?

ሳይንስና ሞራል እንዴት ሊጣጣሙ ይችላሉ?ምርምርን ፣ አላግባብ ማዋል ሊከሠት አይችልም ወይ? እነዚህና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እጅግ የሚያሳስቡ ቢሆኑም፣ ብዙዎቹ በአብያተ-ሙከራ ምርምር የሚያካሂዱ ጠበብት፣ በሁለት ጉዳዮች ላይ ነው የላቀ ትኩረት ያደረጉት። እነርሱም---የምርምር ነጻነት፤ የሰዎች መብት መከበር ፣ ጤንነት፣ እንዲሁም የደኅንነታቸው መጠበቅ የሚሉት ናቸው።

በአውሮፓ አሉታዊነት ያለው ምርምር ድጋፍ ሊሰጠው እንደማይገባ፤ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስትር የነበሩት ወ/ሮ አኔተ ሻባን እንዲህ ሲሉ አስገንዝበው አንደነበረ የሚታወስ ነው።

«የግንድ ኅዋስን ምርምር በተመለከተ፤ ጀርመን ብቻ ሳትሆን፤ በዛ ያሉ የአውሮፓ ዜጎች(ሴቶችም፤ ወንዶችም)የሚጠብቁት፤ የሰውን ጽንስ ኅልውና የማያሳጣ ምርምር ይካሄድ ዘንድ ፣ ፍትኃዊ እርምጃ እንዲወሰድ ነው»።

በአርግጥ ፤ ምርምር ለብዙ ችግሮች መፍትኄ ሊያስገኝ ስለሚችል ሊደገፍ ይገባዋል። የሰውን ጤንነት ለመጠበቅ ከበሽታ ለመከላከል የሚደረገው ጥረትም ሊበረታታ ይገባል። በፅንስ ላይ የሚካሄድ ምርምር ግን ብርቱ ጥንቃቄና ሥነ ምግባርን የሚጠይቅ ነው። «እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት » እንዳይሆን!

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ