1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዋሪዎችና ፖሊስ ግጭት በድሬዳዋ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2009

በድሬዳዋ ከተማ በመንግሥት ታጣቂዎችና በነዋሪዎች መካከል ተከስቶ በነበረ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፤ ቁስለኞችም ሐኪም ቤት እንደሚገኙ የዓይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ። ለሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ግጭት ባለፈዉ ዓርብ እለት የተቀሰቀሰዉ ወታደሮች አንዲት ግለሰብ በጥይት መትተው ከገደሉ በኋላ መሆኑን እማኞቹ ያስረዳሉ።

https://p.dw.com/p/2jSd0
Äthiopien Alte Eisenbahnverbindung
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ቁስለኞች ዛሬም ድረስ በተለያዩ የድሬደዋ ሐኪም ቤቶች እንደሚገኙ የዓይን እማኞች ይናገራሉ። ለሰው ሕይወት መጥፋት ሰበብ የሆነው ግጭት ባለፈዉ ዓርብ እለት በድሬደዋ ከተማ ተቀስቅሶ የነበረው በፌዴራል ፖሊስ እና በነዋሪዎች መካከል ነውም ተብሏል። የግጭቱ መንስኤ ደግሞ ፖሊስ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኗል ያለውን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ባደረገው ሙከራ አንዲት ዕድሜያቸው ከ35 እስከ 40 የሚገመቱ ሴት በጥይት ከተገደሉ በኋላ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እማኝ ገልጠዋል። 

«ወደ ድሮ ኬላ አካባቢ ትንሽ  ከፍ ብሎ ነው። የዛን እለት አንድ የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነ መኪናን ሲያሳድዱ ጎማው ይተነፍስና ገደል ውስጥ ይገባል። ባለ እቃዋም ጋቢና አብራ ነበረች። ሴትዮዋ ልታመልጥ ስትል ወዲያውኑ ነው በመሣሪያ የገደሏት።  በዛ መሀል ሕዝቡ ተናዶ ድድናጋይ ሲወረውር» ሌላ ተጨማሪ ኃይል ወደ የከተማው እንደተሰባሰበ የገለጡት የዓይን እማኙ፦ ግጭቱ «በጣም እያየለ ሲመጣ ከመኤሶ መከላከያ ተደውሎለት መጣ» ብለዋል። «እነሱ ናቸው እንግዲህ በመሣሪያ፤ በተኩስ ሰዉን  የበተኑት። የሞተውም ሞተ፤ የቆሰለም አለ ብዛቱን እርግጠኛ አይደለሁም።»

የዓይን እማኙ በስፍራው በተከሰተው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሰባት እንደሚደርስ ተናግረዋል። የፌዴራል ፖሊስ የቀድሞ የሥራ ባልደረባው ሻለቃ ዓሊ ሰምሬ ስገድ በበኩላቸው የሞቱት አንዲት ሴት ብቻ ናቸው ይላሉ። ሻለቃ ዓሊ የመንግሥት ታጣቂዎችና የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተጋጭተዋል የተባሉበት አካባቢ ማለትም የድሬዳዋ ከተማ የቀበሌ 09 አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን ከአምስት ሰው በላይም መቁሰሉን ተናግረዋል። መረጃ ከአካባቢው በፍጥነት እንደሚደርሳቸው የሚገልፁት ሻለቃ ዓሊ በኮንትሮባንድ ሰበብ ሰዎች መገደላቸው አዲስ ነገር እንዳልሆነም ይናገራሉ።

«ከዚህ በፊትም [እኔ በሥራ ላይ በነበርኩበት ወቅት] ሰዎች በኮንትሮባንድ ሰበብ የተገደሉበትና የቆሰሉበት ሁኔታዎች ነበሩ። 3 ሰዎች በወቅቱ ሞተዋል ተብለው ነበር። ግን በኋላ ስናረጋግጥ አንዲት ሴት ናቸው የሞቱት። ከአምስት ሰው በላይ ደግሞ ቆስሏል በከፍተኛ ሁኔታ። ድሬዳዋ የተለያዩ ሐኪም ቤቶች ውስጥ ሕክምና ላይ ነው ያሉት። የአካቢው ሰው እስከዛሬ ድረስ በጣም ተዋክቧል።»

Polizisten in Dire Dawa Äthiopien
ምስል DW

የዓርብ እለቱ ግጭት የሰው ሕይወት ቢጠፋበትም ተዳፍኖ ነው የቀረው ያሉት የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪው የዓይን እማኝ ወደ ስፍራው ያቀኑት የተኩስ ሩምታ ከሰሙ በኋላ ነበር።

«በቦታው ነበርኩ። ማንንም ሰው ስለማይመርጡ ከርቀት እየሸሸን ነው ያየሁት። የጥይት የተኩስ ድምጽ በጣምለ ረዥም ሰአት ነው የተሰማዉ። እና ምንድን ነው ብዬ ስሄድ ነው ያየሁት እንጂ ሆን ብዬ አይደለም።  ረብሻ ነበር፤ የድንጋይ ውርወራም ነበር። ወንዱም ሴቱም፤ የአካባቢው ህዝብ  በቃ ድንጋይ ይወረውራል እነዛም ይተኩሳሉ፤ ያንን ነው ያየሁት።»

እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ለአራት ዓመታት ያኽል የዎርልድ ቪዥን ግብረ-ሠናይ ድርጅት የሶማሌ ክልል የጸጥታ ጥበቃ ኃላፊ እንደነበሩ የተናገሩት ሻለቃ ዓሊ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች ላይ ጫና መበርታቱን ገልጠዋል። «ማንኛውም በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ወጣት በተለይ ደግሞ ሞባይል የያዘ ወጣት  ያው መረጃ እያስተላለፋችሁ ነው እየተባለ እየታሰሩ ነው» ሲሉም አክለዋል።

ግጭቱ ሲባባስ እና ሰዎች መታሰር ሲጀምሩ ከአካባቢው ርቄ ሄድኩ ያሉት የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪው የዓይን እማኝ ሁለት ወታደሮች መፈንከታቸውን ተናግረዋል። በፌስቡክ ገጻችን አስተያየት ያደረሱን ተከታታዮቻችን በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተሠማሩት በመከላከያ ውስጥ የሚሰሩና ከፍተኛ መኮንኖች ናቸው የሚሉ አስተያየቶቻቸዉን አስፍረዋል።  ጉዳዩን ከድሬዳዋ ፖሊስ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ግን አልተሳካም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ