1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነጭ ዓባይ ምንጭ እና ቡሩንዲ  

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 2010

ቡሩንዲ በሀገሯ ደቡባዊ ከፊል ባሉ ተራሮች ስር የሚገኘውንና የነጭ ዓባይ ይመነጭበታል የሚባለውን ቦታ እአአ በ2007 ዓም በዩኔስኮ በቅርስነት አስመዝግባዋለች። በዚሁ ቅርስ አማካኝነትም የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ ተስፋ አድርጋለች። ይሁን እንጂ፣ በሀገሪቱ ከሁለት ዓመት በፊት የታየው የፖለቲካ ቀውስ ቱሪስቶችን የሚያበረታታ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/2pCsw
DW Akademie Südsudan
ምስል DW

ቡሩንዲ

ቡሩንዲ ጀርመናዊ ተመራማሪ ቡርክሀርት ቫልዴከር የነጭ ዓባይን ምንጭ መጀመሪያ እንዳገኙ ይነገራል። በሀገር አስጎብኚነት ሙያ የተሰማሩት ናሂማ ናሄርሞ እንደሚያስታውሱት፣ በጎርጎሪዮሳዊው 1930 ዓም ግብፅን የጎበኙት እና የዓባይ ወንዝ ከሜድትሬንያን ባህር ጋር ሲቀላቀል  የተመለከቱት ቡርክሀርት ቫልዴከር የወንዙ ውሀ ከየት እንደሚመነጭ በማጠያየቅ የምንጩን፣ ብሎም የነጩን ዓባይ ምንጭን የመፈለጉን ስራ ለመጀመር ወሰኑ። ይህ ፍለጋቸው አራት ዓመት ወሰዶባቸዋል፣ ወደ 7,000 ኪሎሜትር  ያህል በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ምንጩን በደቡባዊ ቡሩንዲ ባሉ ተራሮች ስር ማግኘታቸውን እና በዚሁ ቦታ ለመታሰቢያ አንድ ንዑሱን ፒራሚድ ማቆማቸውን ናሄርሞ ተናግረዋል፣ ቡሩንዲ ይህንኑ ቦታ እአአ በ2007 ዓም በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፣ በምህፃሩ በዩኔስኮ በቅርስነት ብታስመዘግብ እና ቦታውን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ብትፈልግም፣ ፍላጎቷ እንዳልሰመረ ናሄርሞ በቅሬታ ገልጸዋል።
« በአሁኑ ጊዜ አካባቢውን የሚጎበኘው ሰው ቁጥር ብዙ አይደለም።  ቀደም ባለ ጊዜ ፣ በተለይ ከ2015 የፖለቲካ ቀውስ በፊት ግን የጎብኚዎች ቁጥር ብዙ ነው። አሁን በቀን ምናልባት አንድ ቱሪስት ይመጣ ይሆናል፣ በፊት ግን 10 አንዳንዴም 20 ሀገር ጎብኚዎች ይመጡ ነበር። » 
የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመቀጠል የወሰኑበትን ድርጊት በመቃወም የተፈጠረው ደም አፋሳሹ ውዝግብ  እና የጸጥታ አባላት የወሰዱት የኃይል ርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፣ በመቶ ሺዎች የሚሆኑትን ደግሞ ለስደት ዳርጓል። ሀገሪቱ አሁንም በሰብዓዊ መብት ጥሰት አብዝታ ትወቀሳለች። ይህ በተጨማሪ ቱሪስቶችንም ከሀገሪቱ አርቋል። 
ይሁንና፣ ቡሩንዲ በወቅቱ የተረጋጋች እና አስተማማኝ ፀጥታ የሚታይባት ሀገር መሆኗን የፀጥታ እና ፖሊስ ሚንስቴር  ቃል አቀባይ ፒየር ንኩሩኪዬ በመግለጽ የሀገር ጎብኚዎችን ስጋት ለመቀነስ ሞክረዋል። 
« ሁኔታዎች ወደነበሩበት ተመልሰዋል። በ2015 ዓም ቡሩንዲ ውስጥ ዓመፅ ተነስቶ ነበር። በዚያን ጊዜ ሰዎች በመዲናይቱ ቡጁምቡራ መንገዶች ይገደሉ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ንቅናቄ ተደምስሷ። እና አሁን ሰላም ፀጥታ ሰፍኗል። »
የፀጥታ እና ፖሊስ ሚንስቴር  ቃል አቀባይ ፒየር ንኩሩኪዬ ይህን ይበሉ እንጂ፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ እስካሁን ብዙም የታየ መሻሻል እንደሌለ በኤኮኖሚ ሚንስቴት የቱሪዝሙ ክፍል ኃላፊ ሌዎኒዳስ ሀቦኒማና ገልጸዋል። ምክንያቱም ሲያስረዱ፣  «ትልቁ ተግዳሮት የፀጥታው ጉዳይ ሳይሆን ለቡሩንዲ የተሰጠው ገፅታ ነው፣ ይህ በፍጹም ገሀዱን አያንፀባርቅም።»    ብለዋል። 
ጀርመናዊው ተመራማሪ ቡርክሀርድ ቫልዴከር የነጭ ዓባይ ምንጭ ባሉት መታሰቢያ ፒራሚድ ካቆሙበት ቦታ በመኪና የአንድ ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ በሚገኘው መንደር  የሚኖሩት የሀገሪቱ ዜጎች ግን የቱሪስቶች ቁጥር መቀነስ ቡሮች አዳጋች እንዳደረገባቸው ይናገራሉ።
« ኑሮ ከባድ ነው። ለመኖር ያህል እንኖራለን። ለዛሬ የምንበላውን ምግብ ለመግዛት የሚበቃ ደሞዝ እናገኛለን። ነገ ግን ምን እንደሚሆን የሚያውቅ የለም።  አንድም እቅድ ማቀውጣት አትችልም። ባጠቃላይ እድገት የለም።»
ከዓለም ድሆች ሀገራት አንዷ የሆነችው ቡሩንዲ በፖለቲካው ቀውስ ሰበብ ይበልጡን ደህይታለች። የውጭ ሰዎች ለጉብንት ቢመጡ ሀገሪቱ እንደ ኬንያ ወይም ታንዛንያ ልትድግ ትችል ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ የዓባይ ምንጭ አስጎብኚው ናሄርሞ  የተሻለ የወደፊት ሁኔታ ይመጣል ብለው ተስፋ አድርገዋል። 

 
አርያም ተክሌ/ሊንዳ ሽታውደ

ነሽ መሀመድ