1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነፈሰበት የደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት 

ዓርብ፣ ጥር 12 2009

የደቡብ ሱዳን የመንግሥት ባለሥልጣን የሰጡት አስተያየት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ሳይቀዛቀዝ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ አጭሯል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ግን ምንም የተፈጠረ ነገር የለም እያለ ነው።

https://p.dw.com/p/2W9K0
Afrika Juba - Äthiopischer Premierminister Hailemariam Desalegn und südsudanischer Präsident Salva Kiir
ምስል Reuters/J. Solomon

The South Sudan rhetoric against Ethiopia - MP3-Stereo

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለሥልጣን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ጥያቄ የሚያጭር አስተያየት ሰጥተዋል። የደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚኒሥትር ሚካኤል ካኩይ የቅርብ ረዳት የሆኑት አቴም ዴንግ ማኩአክ ኒያማይልፔዲያ ለተሰኘው የድረ-ገፅ መገናኛ ብዙሃን በቀጣናውም ይሁን ከቀጣናው ውጪ ማንንም አንፈራም ሲሉ ተናግረዋል። የአቴም ዴንግ አስተያየት የተደመጠው መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በብሔራዊው ቴሌቭዥን ቀርበው አገራቸው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረር ሥምምነት ከግብፅ ጋር አለመፈጸሟን ካስረዱ በኋላ ነው።

 የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ወደ ካይሮ አቅንተው ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታሕ አልሲሲ ጋር ከመከሩ በኋላ ኢትዮጵያ በቤኒሻንጉል ክልል የምትገነባውን የኃይል ማመንጫ ግንባታ የሚያደናቅፍ ሥምምነት ሳይፈርሙ አልቀረም የሚሉ ያተረጋገጡ ወሬዎች ተናፍሰው ነበር። የግጭት ትንተና እና አፈታት ባለሙያው አቶ አለማየሁ ፈንታው ወሬው ከአሉባልታ የዘለለ አይደለም ይላሉ።

6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ታቅዶ በ4.7 ቢሊዮን ዶላር በግንባታ ላይ የሚገኘው የኃይል ማመንጫ በካይሮ እና አዲስ አበባ መካከል ያለውን ግንኙነት አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለ ንትርክ ውስጥ ሲከት ተስተውሏል። ግብፅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ወደ ደቡብ ሱዳን  ከሚዘምተው የሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ ወታደሮቿን ለማካተት ፍላጎቷን አሳይታለች። የደቡብ ሱዳን የሰላም ሥምምነት እንዲፈረም ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ሚና መጫወቷን የሚያስታውሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ቃል-አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በሁለቱ አገሮች መካከል ምንም አይነት እንከን አንዳልተፈጠረ ተናግረዋል። አቶ ተወልደ የሰሞኑን ጥርጣሬ በይሆናል የተገመደ መደምደሚያ ነው ብለዋል። የግጭት ትንተና እና አፈታት ባለሙያው አቶ አለማየሁ ፈንታው ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ሁልጊዜም ልትፈትሽ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ