1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑሮ ልዩነት በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 9 2010

በኢትዮጵያ በሀብታምና በድሃ መካከል ያለዉ የኑሮ ልዩነት እየሰፋ መጥቷል ተባለ።ሰሞኑን መንግስት ይፋ ባደረገዉ አምስተኛዉ የድህነት ትንተና ጥናት ላይ እንደተገለፀዉ የድህነት መጠን በሀገሪቱ ቢቀንስም በዜጎች መካከል ያለዉ የኑሮ ልዩነት ደረጃ ግን እየጨመረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2ltpJ
Karte Äthiopien englisch

The Gap Between The poor and Rich in Ethiopia - MP3-Stereo

የየምጣኔ ሀብት ባለሙያወች በበኩላቸዉ የድሃዉን ህዝብ የገቢ መጠን የሚጨምር  የተቀናጀ የኢኮኖሚ ፓሊሲ  ልዩነቱን ለማጥበብ ይረዳል ሲሉ ይመክራሉ። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፕላን ኮሚሽን ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ባካሄዱት የ2008 የድህነት ትንተና የናሙና ጥናት መሰረት የድህነት መጠን  በሀገሪቱ ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃጸር 6 በመቶ ቀንሷል።ይሁን እንጅ በድሃዉና በሀብታሙ፣በገጠርና በከተማ ነዋሪዉ እንዲሁም በድሃዉና በድሃዉ ህዝብ መካከል ሳይቀር የኑሮ ልዩነት በእጅጉ እየሳፋ መምጣቱን አመልክቷል።ጥናቱን በተመለከተ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ተክለማርያም እንደሚሉት የኑሮ ልዩነቱ እየሰፋ የመጣዉ በዋናነት በዜጎች መካከል ያለዉ የገቢ ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ ነዉ።
አቶ ጌታቸዉ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ነዉ ቢባልም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መሆን ሲገባዉ  ወደ አገልግሎት ተኮር ዘርፍ ተቀይሯል።በመሆኑም አብዛኛዉ የሀገሪቱ ምርት በዚህ ዘርፍ እንዲመረት እየሆነ ነዉ።ይሁን እንጅ ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ድሃዉን ሳይሆን ሀብታሞችን የበለጠ ሀብታም የሚያደርግ ነዉ ይላሉ።
ይህ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከስራ ፈጠራ አንፃርም የገጠሩን ነዋሪ ህዝብ ገቢ የሚጨምር አይደለም።ከግብርና የሚወጣዉ የሰዉ ሀይል ወደ አገልግሎት ዘርፍ ሲሄድ ለዘርፉ  በእዉቀትና በክህሎት የሚጨምረዉ አስተዋፅኦ ዝቅተኛ በመሆኑ የሚቀጠረዉ በዝቅተኛ የስራ ዘርፍ ሲሆን ገቢዉም በዚያዉ መጠን ዝቅተኛ ነዉ ።በተቃራኒዉ በአገልግሎቱን በማቅረብ  የተሰማራዉ ክፍል ገቢ ግን ይጨምራል።ያ ደግሞ በገጠርና በከተማ ነዋሪዉ መካከል ያለዉን የኑሮ ልዩነት የበለጠ በማስፋት ረገድ ያለዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነዉ ሲሉ ባለሙያዉ ገልጸዋል።
አብዛኛዉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከተማ ተኮር መሆንም ሌላዉ ችግር ነዉ ተብሏል።
እንደ አቶ ጌታቸዉ ገለፃ  ለድሃዉ ህዝብ ተብለዉ በመንግስት የሚሰሩ  የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና የተቋማት ግንባታወችን አቅርቦቱን የሚመሩት ሀብታሞች በመሆናቸዉ አገልግሎት ሲጨምር ተጠቃሚ የሚሆነዉ ይሄዉ ክፍል ነዉ።የዋጋ ዉድነትና ተቀጣሪ የሆነዉ የህብረተሰብ ክፍል ገቢ ለዉጥ የማይታይበት መሆኑም ለተከሰተዉ የኑሮ ልዩነት ሌላዉ ምክንያት ነዉ።

በፌስቡክና በዋትስ አፕ አስተያየታቸዉን ለዲቼ ቬለ ያጋሩ አንዳንድ አስተያየት ሰጭወች በበኩላቸዉ ሙስናና፣ የዘመድ አዝማድ አሰራርና አድልኦ ልዩነቱን እያሰፋዉ ነዉ ብለዋል።በዚህም የተነሳ ኑሮ ለድሃዉ ህዝብ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አንድ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።
የዋጋ ዉድነትን በአግባቡ መቆጣጠር ፣የኢንደስትሪ ዘርፍን ማሳደግ ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚሰሩ የኢኮኖሚ አማራጮችን ባሉበት መደገፍና የድሃዉን ህዝብ የገቢ መጠን የሚጨምር የተቀናጀ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ልዩነቱን ለማጥበብ ይረዳል ሲሉ ባለሙያዉ መክረዋል።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ