1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2009

በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጀሪያውያን የገጠማቸውን ኤኮኖሚያዊ ችግር በመቃወም የንግድ መናኸሪያ በሆነችው የሌጎስ ከተማ ትናንት አደባባይ ወጥተው ዋሉ።  ፀረ መንግሥት ተቃውሞ የተካሄደው የሃገሪቱ ፕሬዚደንት መሃማዱ ቡሃሪ ለዕረፍት እና ለህክምና ወደ ብሪታንያ መዲና ለንደን በሄዱበት እና ቆይታቸውን ባራዘሙበት ጊዜ ነው።

https://p.dw.com/p/2X7fp
Nigeria Proteste gegen Muhammadu Buhari in Lagos
ምስል DW/S. Olukoya

M M T/ Nigeria Proteste - MP3-Stereo


በናይጀሪያ የዋጋ ግሽበቱ ካለፉት 11 ዓመታት ወዲህ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ በሃገሪቱ ብርቱ ቁጣ ቀስቅሶ ፣ ተቃዋሚዎች ይህንን ሁኔታ እንዲቀይር በመጠየቅ በትናንቱ ዕለት በሌጎስ ከተማ ሰልፍ አካሂደዋል። የሌጎስ ከተማ ፖሊስ  የናይጀሪያ መንግሥት ደጋፊዎችም ትናንት በተመሳሳይ ጊዜ አደባባይ ሊወጡ ይችሉ ይሆናል በሚል ሁከት እንዳይፈጠር የሰጋው የሰብዓዊ መብትየ ተሟጋቾች እና ሙዚቀኞ ጭምር የተሳተፉበትን የትናንቱን ተቃውሞ እንዳይደረግ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም፣ ሰልፉ ተካሂዷል። የተቃውሞ ሰልፉን ካዘጋጁት መካከል ዋነኛ የሆነው ሶዌቶ ሃሳን እንዳሉት፣ እየከፋ በሄደው የናይጀሪያ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ አሳሳቢነት የተነሳ ሰልፉን ማካሄድ አስፈላጊ ነበር።
« ይህች ሃገር ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከተለችው የኤኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ስልት ግልጽ አይደለም።  እና ናይጀሪያውያን በዚሁ ሰበብ የተሰማቸውን ቁጣ ለመግለጽ ነው አደባባይ የወጡት።  በመሃማዱ ቡሃሪ መንግሥት ላይ አሳድረውት የነበረው ተስፋቸው  ቅሬታ ብቻ ነው ያስከተለባቸው።  ግዙፉ ስራ አጥነት፣ ከባዱ የኑሮ ሁኔታ  ሕዝቡን አበሳጭቷል፣ ብዙው የሃገሪቱ ሕዝብም እየተራበ ነው።  በመሆኑም ሰዎች በብዙ ሃብት የታደለችው ናይጀሪያ ለምንድን ነው በዚህ ዓይነት ድህነት ውስጥ መኖር ያለባት በማለት ማጠያየቅ ይዘዋል። »
በተቃውሞው ከተሳተፉት መካከል ተመሳሳይ ምክንያት ያላቸው ለምሳሌ፣ ወጣቶች፣ በተለይም፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አብቅተው ስራ አጥ የሆኑት፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ያልቻሉ ዳባ ኦሞሬጂን የመሳሰሉ ሴቶች ይገኙባቸዋል። 
«   እናት በመሆኔ  ነው ተቃውሞ የወጣሁት፣ እንደሚታወቀው፣ እኛ እናቶች የህብረተሰቡ የጀርባ አጥንት ነን። ልጆቻችን ትምህርት ቤት መሄድ ሳይችሉ፣ ሲራቡ ወይም ባሎቻችን ስራ ሲያጡ  ችግራቸውን በቅርብ የምናየው እና ስቃያቸውም የሚሰማን፣ ችግሩንም ለማቃለል የምንጥር  እኛ ሴቶች ነን።  እና ይህ መንግሥት እኛን ለስልጣን ሊያበቃ ይገባል። » 

Karte Nigeria Uyo
ምስል DW

የሌጎሱ ተቃውሞ በስልጣን ላሉት ግልጹን መልዕክት ያስተላለፈ የተሳካ እንደነበር ጃስቲን ቼንዱ አመልክተዋል።
« ይህ ተቃውሞ  የመንግሥት ባለስልጣናት ለህዝቡ ምን እየሰሩ ነው በሚል ናይጀሪያውያን  ለመጀመሪያ ጊዜ ባንድነት ጥያቄ ያቀረቡበት ነበር።  መንግሥት የሾማቸው ባለስልጣናትም ስራቸውን በሚገባ በማከናወን ላይ አለመሆናቸውን ያስታወቁበትም ነበር። ይህ የህዝብ ተቃውሞ በስልጣን ላይ ያሉትን ኅሊና እንደሚነካ እና እነዚሁ ባለስልጣናትም ቢያንስ  አሰራራቸውን ለመቀየር እንዲሞክሩ ይገፋፋል  ብዬ  አስባለሁ። ብዙ ነገር አይደለም የጠየቅነው። »

Paris Medef Zentrale Buhari Gattaz
ምስል Getty Images/AFP/E. Piermont

በናይጀሪያ የሚታየውን ኤኮኖሚያዊ ችግር መቋቋም የከበደው የሃገሪቱ ሕዝብ በድምፁ በመረጣቸው ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በብሪታንያ መዲና በሚገኙት እና የህክምና ምርመራ ውጤት ለመጠበቅ በሚል የለንደኑን ቆይታቸውን ባራዘሙት በፕሬዚደንት መሃማዱ ቡሃሪ ላይ የነበረውን እምነት እያጣ መሄዱን አሳይቷል። ትናንት በሌጎስ ከተማ ያካሄደውንም ተቃውሞ አሁን አቡጃ፣ ካኖ እና ፖርት ሀርኩርትን ወደመሳሰሉ ሌሎች ከተሞችም ለማስፋፋት እቅድ ወጥኖ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። 


አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ