1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ቦኮሃራምን የማጥፋት ዘመቻ

ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2006

በርካታ ንፁሐን የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፤ አዳዲስ የጭካኔ ርምጃዎቹ ዜጎችን ፍርሃትና ስጋት ላይ ጥሏል። የናይጀሪያ መንግስት ጦር አሸባሪዉን ቡድን ቦኮ ሃራምን በተጠናከረ ኃይል እንዳያንሰራራ አድርጎ ለመምታት አልሟል። ምንም እንኳን በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ለዚህ ተግባር ቢሰማሩም ቡድኑ አሁንም በጥቃቱ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1A7S2
ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ምሽት የቦኮሃራም አባላት ዳማቱሩ በተባለችዉ የናይጀሪያ ግዛት የፀጥታ ኃይሎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ነዉ ያደረሱት። ዛሬ ከሃኪም ቤት የወጡ መረጃዎች እንደሚሉትም 35 አስከሬኖች ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ናቸዉ። አስከሬኑ ግን በትክክል የየትኛዉ ወገን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አልሆነም። ዘገባዎች እንደሚሉት የቦኮሃራም ታጣቂዎች ጥቃት ሲሰነዝሩ ለማደናገር ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰዉ በተደጋጋሚ ታይተዋል።

ፖሊስና ኗሪዎች ታጣቂዎቹ ወደዳማቱሩ ከተማ ገሚሱ በእግር ቀሪዎቹም በተሽከርካሪ መግባታቸዉን ቢናገሩም ወታደራዊ የደንብ ልብስ ስለመልበሳቸዉ ያሉት የለም። እነዚህ ጠመንጃና ፈንጂዎችን የታጠቁ የቦኮሃራም አባላትም አራት የፖሊስ ሕንጻዎች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ አቃጠሉም። ከፀጥታ ኃይሎች ጋራም ለሰዓታት የዘለቀ ከባድ የተኩስ ልዉዉጥ ቀጠለ። የጆስ ከተማ አንድ ወታደራዊ መኮንንን እንደሚሉትም በነበረዉ ዉጊያ የተጎዱ ሌሎች 20 ወታደሮች ሃኪም ቤት ይገኛሉ። አሁን መንግስት ቦኮሃራምን ጠርጎ ለማጥፋት የከፈተዉ ዘመቻ አምስተኛ ወሩን ይዟል።

Nigeria Kampf gegen Boko Haram Islamisten
ምስል Getty Images/AFP

የጦር ኃይሉም ቡድኑ ከእንግዲህ የተቀናጀ ጥቃት ለመሰንዘር አቅም እንደሌለዉ ይገልጻል። በተቃራኒ የሚታየዉ ግን ቦኮሃራም በተጠናከረ ጥቃቱ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ኗሪዎችን ማሸበሩን መቀጠሉ ነዉ። የግጭት መንስኤዎችን የሚያጠናዉ የዓለም ዓቀፉ ድርጅት የናይጀሪያ ጉዳይ ተንታኝ ናምዲ ኦባሲም ይህንኑ ነዉ የሚያስረዱት፤

«በእርግጥ አልተሸነፉም። አጠናክረዉ ከያዙት አካባቢና ከጣቢያቸዉ ሊያስወጧቸዉ ይችላሉ። ይህ ግን በግልፅ ድል መንሳት አይደለም፤ ፅንፈኝነታቸዉንም ማስተዉ ማለትም አይደለም። ቡድኑ የሚያንቀሳቅሰዉ አስተሳሰብም አሁንም አለ።»

ተንታኙ እንዳሉትም ቦኮሃራም ማለትም «የምዕራባዉያን አስተምህሮ ዉጉዝ ነዉ» በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰዉ ቡድን የሚያራምደዉ አስተሳሰብ በተደጋጋሚ ጥቃት በሚያደርስበት በሰሜን ናይጀሪያም ቢሆን ቀላል የማይባል ደጋፊ እንዳለዉ፤ ሂልደጋርድ በህረንት ኪጎሲ አቡጃ የሚገኘዉ የጀርመኑ ኮንራድ አደናወር ተቋም ሥራ አስኪያጅም ይናገራሉ።

General Ibrahim Attahiru
ጀነራል ኢብራሂም አታሂሩምስል DW/Katrin Gänsler

«በፅንሰ ሃሳቡ የመሳቡ ነገር ያለ የሚመስለኝ ሰዎች ስለኑሮ መሻሻል የሚገቡት ቃል ነዉ። ማለትም ይህን ቃላቸዉን ባላሟሉት በእስከዛሬዎቹ ፖለቲከኞችና በናይጀሪያ ምሁራን ባጠቃላይ ትልቅ ቅሬታ አለ። እናም ፅንፈኛ ሙስሊሞቹ ስልጣን ቢይዙ የኢስላምን ማኅበራዊ ድንጋጌዎች ያከብራሉ የሚል እምነት ያሳድራሉ።»

የቦኮሃራም ታጣቂዎች ድርጊት ግን ይሄን አያሳይም። ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ብቻ ቦርኖ በተባለችዉ መንደር 20 ሰዎች ተገድለዋል። ቀደም ሲልም ትምህርት ቤቶች ላይ ቡድኑ የሰነዘረዉ ጥቃት አሰቃቂ ነበር። ምንም እንኳን የናይጀሪያ ጦር ኃይል ቦኮሃራም ላይ ጫና አሳድሬያለሁ ቢልም ናምዲ ኦባሲ ደካማ ጎን አለዉ ባይ ናቸዉ።

«የናይጀሪያ ጦር ኃይል በመሠረታዊ ደረጃ ለመደበኛ ዉጊያ የሰለጠ ይመስለኛል፤ በቅርቡ እንደምናዉ ያለ የአሸባሪዎች ተግዳሮት ይኖራል የሚል ግምት አልነበረም። እናም ለጦሩ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ራሱን እንደገና ለማደራጀትና ለማሰልጠን ጊዜ ያስፈልገዋል።»

Nigeria Notstand Islamisten Truppen Armee Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚህም ሌላ ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣዉ አዲስ ዘገባ ጦር ኃይሉ ላይ ጫና አሳድሮበታል። ቦኮሃራም ከከፈተዉ ዘመቻ ጋ ተያይዞ የጦር ኃይሉ ጭካኔ የተሞላባቸዉ ርምጃዎች ወስዷል በሚልም እየተተቸ ነዉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ካለፈዉ ጥር ወር እስከ ሰኔ ያለዉን ይዞታ በቃኘ ዘገባዉ 950 እስረኞች እንደተገደሉ ገልጿል። የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት አስመልክቶ ለቀረበዉ ዘገባ የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ ጀነራል ኢብራሂም አታሂሩ ሁኔታዎችን መረዳት እንደሚገባ ነዉ የሚናገሩት፤

«ሁኔታዎች እንዴት እንደሚከናወኑ ትልቅ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፤ አንድ ቦታ የመሸጉ ወታደሮች አይደሉም፤ በጣም ይንቀሳቀሳሉ፤ ካሜሮን ሊገቡና ሊመለሱም ይችላሉ፤ እናም አማፂዎችን ነጥሎ ለመምታት የሚችል ይህ ነዉ የሚባል ልዩ ጥይት በየትኛዉም ዓለም የለም።»

እናም የመንግስት ወታደሮች ከፍተኛ ጥቃት በሰነዘሩ ቁጥር አሸባሪዉ ቡድን ወደጎረቤት ሃገራት ፈጥኖ የመሰወር ስልት እየተከተለ መሆኑ ነዉ የሚገለጸዉ። ቀደም ሲል ታዛቢዎች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ቢሰነዘር ዉጤት ሊያመጣ እንደሚችል አመልክተዉ ነበር። የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ እንደገለጹት ግን በዲፕሎማቶች ደረጃ ቢነሳም ከካሜሮን ጋ ገና ከስምምነት አልተደረሰም። የናይጀሪያ ጉዳይ ተንታኙ ግን የተጠናከረ ጦር ኃይል ዉጊያ ብቻ መፍትሄ እንደማይሆንና ናይጀሪያ ዘመቻዉን ዳግም ብታጤነዉ ይመክራሉ።

ካትሪን ጋይዝለር/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ