1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕጩ ሙሀመድ ቡሀሪ

ቅዳሜ፣ ጥር 30 2007

ባንድ ወቅት የጦር አምባገነን ነበሩ። አሁን የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ሆነው ለመመረጥ ይፈልጋሉ። የጠቅላላ ተራማጆች ኮንግረስ ፓርቲ ዕጩ ሙሀማዱ ቡሀሪ በፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን አንፃር ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ የቀረቡ፣ ደህና ዕድል አላቸው የሚባሉ፣ በተለይ በብዛት ሙሥሊሞች የሚኖሩበት የሰሜናዊ ናይጀሪያ ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው።

https://p.dw.com/p/1EXUj
Wahlkampf in Nigeria 2015 Muhammadu Buhari
ምስል AFP/Getty Images/P. Utomi Ekpei

በሰሜን ናይጀሪያ በምትገኘዋ ትልቋ ከተማ ካኖ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው አደባባይ ወጥቶዋል። ግፊያው ብዙ ነው። ሰዉ በዚሁ አካባቢ የምርጫ ዘመቻ ያካሂዱ የነበሩትን የተቃዋሚውን ቡድን መሪ እና ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሙሀማዱ ቡሀሪን ለማየት ነበር የተሰበሰበው። ቡሀሪ ከአየር ማረፊያው ይጓዙበት የነበረው የተሽከርካሪዎች አጀብ መንገዶቹ ሕዝብ ብዛት በመጨናነቃቸው በናይጀሪያ በትልቅነቷ ሁለተኛ የሆነችው የካኖ ከተማ ሙሥሊሞች መሪ ኤሚር -- በቤተ መንግሥታቸው ሁለት ሰዓት ሙሉ መጠበቅ ነበረባቸው። ቡሀሪ ቤተ መንግሥቱ እንደደረሱም ደስታውን ይገልጽ የነበረው እጅግ ብዙ ስለነበረ ከነበሩበት አውቶቡስ እንኳን መውረድ አልቻሉም። ከደጋፊዎቻቸው መካከል አንዷ፣

« ይህን ዓይነት ድጋፍ አይተን አናውቅም። አምላክን የምንለምነው ቡሀሪ ፕሬዚደንት ሆነው እንዲመረጡ ነው። »

ቡሀሪ ከኤሚሩ ጋ ያደረጉትን የሀሳብ ልውውጥ አብቅተው ከአንድ ሰዓት በኋላ ወደ 80,000 የሚጠጋ እና የተቃዋሚውን ቡድን መሪ የሶስት ደቂቃ ንግግር ለማዳመጥ ወደተሰበሰበበት የካኖ እግር ኳስ ሜዳ ደረሱ። ቡሀሪ ያን ያህል ጥሩ ተናጋሪ ባይሆኑም፣ ሕዝቡ ደማቅ አቀባበል ነበር ያደረገላቸው፣ ምክንያቱም፣ ይላሉ አንዱ ደጋፊያቸው፣ ሕዝቡ ቡሀሪ ብዙ ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ትልቅ ትፅቢት አለው።

Nigeria Oppositionsführer Muhammadu Buhari in Kano
ምስል DW

«እዚህ ናይጀሪያ ውስጥ ትልቅ ስቃይ ውስጥ ነው ያለነው። ቡሀሪ ለሥልጣን ከበቁ ብቻ ነው የቦኮ ሀራም ሽብር ሊያበቃ የሚችለው። »

ብዙ የሰሜን ናይጀሪያ ነዋሪዎች ሙሀማዱ ቡሃሪን በቀድሞ ጀነራልነታቸው ፣ ከጉቦኝነት ነፃ የሆኑ እና ለሥነ ሥርዓት ትልቅ ትኩረት የሚሰጡ አድርገው ነው የሚያዩዋቸው። የጦር ሥልጣናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በጦር ኃይሉ ውስጥ ከፍተኛው ማዕረግ ላይ ለመድረስ ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር። ሀገሪቱን ይገዙ የነበሩት የጦር መሪዎችም ጥሩ ቦታ ሰጥተዋቸዋል። አጥባቂ ሙሥሊም መሆናቸው የሚነገርላቸው እና ሰሜን ናይጀሪያ በእሥላማዊው ሕግ፣ ሽሪዓ ትተዳደር የሚለውን ሀሳብ በመደገፋቸውም የሚታወቁት ሙሀማዱ ቡሀሪ በአንድ የተመረጠ መንግሥት አንፃር በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት እአአ ከጥር 1984 እስከ ነሀሴ 1985 ዓም የሀገር መሪነቱን ሥልጣን ይዘው ነበር። በዚሁ ጊዜ በሥርዓት አልባነት አንፃር ባካሄዱት ትግል ወደ 500 የሚጠጉ ዜጎች በምግባረ ብልሹነት እና ከቀረጥ የተገኘውን የመንግሥትን ንብረት በማባከናቸው ወህኒ እንዲወርዱ አድርገዋል። ወደ ስራ ገበታቸው ዘግይተው የሚመጡ የመንግሥት ሰራተኞች ለመቀጣጫ ከባድ ስፖርት መስራት ይገደዱም ነበረባቸው። ቡሀሪ በሌሎች የናይጀሪይ ፖለቲከኞች አንፃር ራሳቸውን ያላበለፀጉ ሲሆን፣ እስከዛሬ መጠነኛ በሆነ መኖርያ ቤት ውስጥ የሚኖሩት።

ይሁንና፣ ሙሀመድ ቡሀሪ የሀገር መሪነቱ በያዙበት አንድ ዓመት ውስጥ በናይጀሪያ አምባገነናዊ አገዛዝ አስፋፍተው እንደነበር ይታወሳል። ዜጎችን እንዲገደሉ አዘዋል፣ የመገናኛ ብዙኃን ስራቸውን በሚገባ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ደቅነዋል። በተለይ ደግሞ፣ ወታደራዊው አገዛዝ እንዲያበቃ እና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እውቅና ያገኝ ሕጋዊ መንግሥት እንዲተከል በፍፁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ነበር የቀሩት። በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ናይጀሪያዊው ደራሲ ዎሌ ሾይንካ እንዳስታወቁት፣ ናይጀሪያውያን ቡሀሪ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን የሚመርጡ መሪ አድርገው ነው የሚመለከቱዋቸው። ይሁንና፣ ደራሲዋ ሎላ ሾኔዪን ይህን የሾይንካ አስተያየት የተሳሳተ ነው ይላሉ።

Wahlkampf in Nigeria 2015
ምስል AFP/Getty Images/P. Utomi Ekpei

« በመፈንቅለ መንግሥት ነበር ሥልጣን ላይ የወጡት። ይህ ያሁኑ ሁኔታ ግን የተለየ ነው። ገሀዱ የምንኖረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለበት ዘመን ውስጥ ነው። ሁኔታዎች ተቀያይረዋል። ፍርድ ቤቶች አሉን፣ ጠንካራ ሲቭል ማህበረሰብ ፣ ብሔራዊ ምክር ቤት አለን። እና ምናልባት ከ30 ዓመታት በፊት ሊደረጉ ይችሉ የነበሩ ነገሮች አሁን በፍፁም እውን ሊሆኑ አይችሉም። »

ቡሀሪ አሁን በመካሄድ ላይ ባለው በምርጫ ዘመቻው ወቅት ያለፈ አከራካሪ ታሪካቸውን ላለማንሳት ሞክረዋል። የቡሀሪ ተፎካካሪ እና የወቅቱ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ለናይጀሪያ ችግሮች መፍትሔ ባለማስገኘታቸው፣ በተለይም፣ እሥላማዊፅንፈኛቡድን ቦኮ ሀራም ያስፋፋውን ሽብር ማብቃት ባለመቻላቸው ብዙ ናይጀሪያውያን ቅር ከተሰኙበት ሁኔታ ቡሀሪ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተንታኞች ይገምታሉ። አሁን ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዕጩነት የቀረቡት ቡሀሪ እአአ በ2003፣ በ2007 እና በ2011 ዓምም ከገዢው ሕዝባዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ጋር በተወዳዳሪነት ተፎካክረው እንደነበር ይታወሳል። ይሁንና፣ ቡሀሪ የአንድ የተባበረ የተቃውሞ ቡድን ዕጩ ሆነው ሲቀርቡ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። እና በብዛት ክርስትያኖች የሚኖሩበትን ደቡባዊ ናይጀሪያ መራጭ ድምፅ ለማግኘት ከፈለጉ ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው፣ ግን በሳቸው አንፃር ምግባረ ብልሹ ከሆኑ የጠቅላላ ተራማጆች ኮንግረስ ፓርቲ ፖለቲከኞችም ጋ ተባብረው መስራት ይኖርባቸዋል።

አርያም ተክሌ/ሂልከ ፊሸር

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ