1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀርያ ጦር እና ፀረ ቦኮ ሀራም ትግሉ ተዓማኒነት ማጠያየቁ

ቅዳሜ፣ መስከረም 17 2007

የናይጀሪያ ጦር በቦኮ ሀራም አንፃር በጀመረው ትግሉ እንደቀናው ገለጸ። የናይጀሪያ ጦር ባለፉት ጊዚያት በአሸባሪው ድርጅት ቦኮ ሀራም አንፃር በተደጋጋሚ አሰመዘገብኩት ያለው ድል ብዙ ማነጋገር ይዞዋል።

https://p.dw.com/p/1DLnt
Nigeria Soldaten
ምስል picture-alliance/AP Photo

በሰሜናዊ ናይጀርያ የሚንቀሳቀሰው የፅንፈኛው ቡድን አባላት ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ጥቃታቸውን አጠናክረው በተቆጣጠሩት ሰፊ አካባቢ እሥላማዊ መንግሥት ማቋቋማቸውን ካስታወቁ በኋላ፣ አሁን የናይጀሪያ ጦር ባካሄደው አፀፋ ዘመቻ በቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ነው የሚናገረው። የናይጀርያ ጦር ቃል አቀባይ ክሪስ ኦሉኮላድ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ እንዳስታወቁት፣ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የቦኮ ሀራም ተዋጊዎች ለመንግሥቱ ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል፤ የቡድኑ መሪ አቡበከር ሼካውም መገደላቸውን አመልክቶዋል።

« አንድ ቦኮ ሀራም ባለፉት ጊዚያት ባስተላለፋቸው የቪድዮ መልዕክቶች ላይ ራሱን ሟቹን የቡድኑ መሪ አቡበከር ሼካው ነኝ በማለት ያስተዋውቅ የነበረ መሀመድ በሺር የተባለ ግለሰብ በሰሞኑ የጦር የጥቃት ዘመቻ ሞቶዋል።»

የፖለቲካ ታዛቢዎች ግን የቦኮ ሀራምን ሽብር ተግባር ማብቃት ባለመቻሉ ሰፊ ነቀፌታ የተፈራረቀበት የናይጀሪያ ጦር ሼካውን ወይም እሳቸውን የሚመስለውም ሰው በሰሞኑ የጦሩ ዘመቻ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ገደልኩ ማለቱን ተጠራጥረውታል። የናይጀሪያ ጦር ባለፈው ዓመት ሼካው በአንድ የተኩስ ልውውጥ ወቅት መገደሉን አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሱን ኢማም ሲል የሰየመው ሼካው ቦኮ ሀራም ባወጠው ቪድዮ ላይ ታየ። በዚያን ጊዜ ጦሩ ሼካው መሞቱን አላረጋገጠም፣ ቦኮ ሀራምም በቪድዮው የሚታየው ሼካውን የሚመስል ሰው ነው በሚል የተሰማውን ጥርጣሬ አላስተባበለም። በጡረታ የሚገኙት የናይጀርያ ጦር ኮሎኔል ሀሚድ አሊ ሼካው ብርግጥ መገደሉን አጠያይቀዋል።

« ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ነበር ይኸው የናይጀሪያ ጦር ሼካውን በተኩስ ልውውጥ እንደገደለው ገልጾ ነበር። እና አሁን ደግሞ ሼካውን እንደገና እንደገደለው ይናገራል። በጣም የሚያስገርም ነገር እኮ ነው። ሼካው ስንት ነፍስ ነው ያለው? »

ሀሚድ አሊ የናይጀርያ ጦር ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ አስመዘገብኩት ያላቸውን ድሎች ሁሉ የፈጠራ ወሬ ሲሉ አጣጥለውታል።

« የቦኮ ሀራም መሪ የነበሩት ዩሱፍ መሀመድ እአአ በ2009 ዓም በተገደሉበት ጊዜ የቦኮ ሀራም ፍፃሜ ይሆናል ተብሎ ነበር፣ ግን ፣ ምንድን ነው እያየን ያለነው? ያልጠበቅነው አስከፊ ሽብር ነው የተከተለው። ስለዚህ ሼካው በህይወት መኖሩ ወይም መሞቱ አይደለም ወሳኙ ጉዳይ። »

»

ይሁን እንጂ፣ ማሌም ዩሱፍን የመሳሰሉ በቦርኖ ግዛት የምትገኘው የማይዱግሪ ሕዝብ ግን ባለፈው ረቡዕ ጦሩ ሼካውን ገደልኩ ያለበት ዜና የቦኮ ሀራምን ሽብር ያበቃ ይሆናል በሚል ደስታውን ገልጾዋል።

«ማይዱግሪ የምንኖረው ሁሉ ዛሬ በደስታ ስሜት ውስጥ ነው የምንገኘው። ምክንያቱም የናይጀሪያ ጦር የቦኮ ሀራም መሪ መግደሉን አረጋግጦልናል፤ 135 የቡድኑ ተዋጊዎችም በአዳማው ግዛት እጃቸውን መስጠታቸውን እና ሌሎች 45ም መያዛቸውን ገልጾዋል።

ይሁናና፣ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ናይጀሪያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማክ ሚዥንያና ሼካው ሞቱ አልሞቱ ጦሩ የቦኮ ሀራምን ሽብር ማብቃት አለመቻሉ ነው የሚታየው።

« አሁን የሚሰማው ፕሮፓጋንዳ ትርጉም የለውም፣ ምክንያቱም የአንድ ሰው ሞት የሚለውጠው ነገር ስለሌለ፣ ቡድኑ እንደሆን ሽብሩን ማስፋፋቱን ቀጥሎዋል። የቦኮ ሀራም መሪ ሞተ አልሞተ በወቅቱ ግልጽ የሆነው ጉዳይ መንግሥት እና ጦሩ ቦኮ ሀራም የፈጠረውን ችግር ማብቃት አለመቻሉ ነው። »

ናይጀሪያዊው ጋዜጠኛ አህመድ ሳሊኪዳ የናይጀርያ ጦር ዘገባ ሀሰት ሲል አስተባብሎዋል። ቦኮ ሀራም ያገታቸውን ልጃገረዶች ለማስለቀቅ በመንግሥቱ እና በቦኮ ሀራም መካከል በተካሄደው እና ውጤት አልባ በሆነው ድርድር በሽምጋይነት የተሳተፈው ሳሊኪዳ አንዳንድ የቦኮ ሀራምን ምጮች ጠቅሶ እንዳስታወቀው፣ ቦኮ ሀራም ከተቆጣጠራቸው ከተሞች መካከል እስካሁን አንድም ነፃ አልሆነም። አቡበከር ሼካውም በህይወት አለ።

ሼካው ሞተ መባሉ አንዳችም ፕሮፓጋንዳዊ ጠቀሜታም እንደሉለው ጡረተኛው ሀሚድ አሊ አስረድተዋል። የጦሩ አቅም አልባነት እንደሆነ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ጎልቶ ታይቶዋል። የቦኮ ሀራም ን ሽብር እና ግድያ እስካላበቃ ድረስ ሕዝቡ በጦሩ ላይ እምነት አይኖረውም። ጦሩ የቦኮ ሀራም ተዋጊዎችን ማረኩ ወይም የጦር መሳሪያ ትጥቅ አስፈታሁ በሚል ያሰማውንም ጠገባ እስካሁን አንድም ነፃ ምንጭ ባለማረጋገጡ የሕዝቡ ጥርጣሬ መቀጠሉ አይቀርም።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

Karte Nigeria Adamawa Borno Chibok Gwoza
Nigeria Flüchtlinge in Maiduguri
ምስል picture alliance/AP Photo
Nigeria Boko Haram Abubakar Shekau Archiv
ምስል picture alliance/AP Photo