1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናጄሪያ ግጭትና የሠብአዊ መብት ጥሠት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2006

አዋጁን-።«ለማስከበር እና ቦኩ ሐራምን ለማጥፋት» ተብሎ የዘመተዉ ጦር ሕዝቡን መዉጪያ መግቢያ አሳጣዉ።የጠረጠረዉን በመደዳ-ያስር፤ያሰረዉን ይገርፍ፤ ያሰቃይ፤ እስራት-ስቃዩን ለማምለጥ የሞከረዉን እያሳደደ-ይገድለዉ ያዘ።አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ይሕ የሁለቱ ሐይላት እርምጃ ከጦር ወንጀል የሚቆጠር ነዉ።

https://p.dw.com/p/1BZmY
ምስል DW/U.Haussa

ሰሜን ምሥራቅ ናጄሪያ የሸመቀዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኩ ሐራምና ደፈጣ ተዋጊዉን ቡድን የሚወጋዉ የናጄሪያ መንግሥት ጦር በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መግደል፤ ማሰር ማሰቃየታቸዉን ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል አጋለጠ።የመብት ተሟጋቹ ድርጅት እንደሚለዉ ሁለቱም ተፋላሚ ሐይላት ከፍተኛ ሠብአዊ ጥፋትና የጦር ወንጅል ፍፅመዋል፤ የተፈፀመዉ ወንጀል በገለልተኛ ወገን መጣራት አለበት።እዚያዉ ናጄሪያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማትም የዓለም አቀፉን ድርጅት ወቀሳ ይጋራሉ። የናየናጄሪያ መንግሥት ግን ወቀሳዉን አጣጥሎ ነቅፎታል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኩ ሐራም ለመንግሥት ያደሩ፤ ከመንግሥት ጦር ጋር የተባበሩ፤ እስልምናን የሚረክሱ እያለ ሰላማዊ ሰዎችን ልጅ ካዋቂ ሳይለይ በቦምብ-መትረየስ ያጭዳል።አክራሪዉ ድርጅት የሚገደል፤ የሚያሰድድ፤የሚሰቃየዉን ሕዝብ መጠበቅ የሚገባዉ የናጄሪያ መንግሥት ጦርም አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ከቦኩ ሐራም ብዙም አልተሻለም።ሰሜን-ምስራቅ ናጄሪያ።

መንግሥት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገደብ ጥሎበታል።አዋጁን-።«ለማስከበር እና ቦኩ ሐራምን ለማጥፋት» ተብሎ የዘመተዉ ጦር ሕዝቡን መዉጪያ መግቢያ አሳጣዉ።የጠረጠረዉን በመደዳ-ያስር፤ያሰረዉን ይገርፍ፤ ያሰቃይ፤ እስራት-ስቃዩን ለማምለጥ የሞከረዉን እያሳደደ-ይገድለዉ ያዘ።አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ይሕ የሁለቱ ሐይላት እርምጃ ከጦር ወንጀል የሚቆጠር ነዉ።

General Ibrahim Attahiru
ምስል DW/Katrin Gänsler

«ሰሜን ምሥራቅ ናጄሪያ ዉስጥ የሚደረገዉ ዉጊያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀዉ ግጭት ያለፈ ነዉ።በዚሕ የተወሳሰበ ዉጊያ ማለት ቦኩ ሐራም በሚፈፅመዉ ጥቃት እና በፀጥታ ሀይሉ አፀፋ ጥቃት ሁለቱም ሐይላት የሠብአዊና የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ብለን እናምናለን።»

ማክሚድ ካማራ ናቸዉ።በአምንስቲ ኢንተርናሽናል የናጄሪያ ጉዳይ አጥኚ።ጉዳዩን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ባስቸኳይ እንዲያጣራዉም የካማራ-ድርጅት ጠይቋል።አምስቲ ኢንተርናሽናል እንድሚለዉ ካለፈዉ ጥር-እስካለፈዉ ሳምንት በነበረዉ ሰወስት ወር ብቻ ሰሜን ናጄሪያ ዉስጥ ከ1500 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

አሶሽየትድ ፕረስ የተሰኘዉ ዜና አገልግሎት እንዳሰላዉ ባለፉት ሰወስት ወራት የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር ቦኩ ሐራም ብርት አንስቶ መዋጋት ከጀመረበት እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ2010 እስከ 2013 ጥር ድረስ ከተገደለዉ ሰዉ የበለጠ ነዉ።ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት ደግሞ ዜና አገልግሎቱ እንደዘገበዉ የከፋ ጥፋት የደረሰበት ነዉ።ከጥር-እስከ ነሐሴ በተቆጠሩት ስምንት ወራት ብቻ፤ማይዲንጉሪ-ከተማ ጊዋ በተባለዉ ጦር ሠፈር ብቻ ታሠረዉ የነበሩ ከሰወስት ሺሕ ሰወስት መቶ በላይ ሰዎች ተግድለዋል።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናሉ አጥኚ በፋንታቸዉ ከሁለት ሳምንት በፊት እዚያዉ ጊዋ ጦር ሠፈር ላይ የደረሰዉን ጥቃት ለመበቀል ጦሩ በስድስት መቶ ሰዎች ላይ የወሰደዉን ዘግናኝ እርምጃ መረጃ እየጠቀሱ ይዘረዝራሉ።

«ካገኘናቸዉ መረጃዎች አንዳዶቹ እንደሚጠቁሙት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር እኛ በይፋ ካስታወቀነዉ የበለጠ ነዉ።በጊዋ ጦር ሰፈር ላይ አደጋ በተጣለ ማግሥት ጦሩ የወሰደዉን እርምጃ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች፤ፎቶዎች፤የአካባቢዉ ነዋሪዎችና ከጥቃቱ ያመለጡ ሰዎች የስጡት መረጃዎች አሉን።ቢያንስ ሁለት የጅምላ መቃብሮች መኖራቸዉን የሚጠቁም የሳተላይት ምሥልም አለን»

የናጄሪያ መንግሥት መረጃዉንም ወቀሳዉንም አጣጥሎታል።የመከላከያ ሚንስቴር ቃል አቃባይ ብርጌድየር ጄኔራል ክሪስ ኦሉኮላንዴ ከዚሕም አልፈዉ «እኛ ከአሸባሪ ድርጅት እኩል እንዴት እንፈረጃለን» በማለት ተቆጥተዋል።የናጄሪያ የሲቢል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ሕብረት ተወካይ አወል ሙሳ ራፍሳንጃኒ ባንፃሩ የፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን መንግሥት ጥፋቱን ከማስተባበል ይልቅ የጦሩን አጥፊዎች ቢመረምር ይሻላል ባይ ናቸዉ።

Nigeria Baga Kämpfe mit Boko Haram 21.04.2013
ምስል picture alliance/AP Photo

«ከነዚሕ ችግሮች አንዳዶቹ በራሱ በጦር ኃይሉ እንደሚፈጸም ተረድተናል።መንገዶች በሙሉ ተዘግተዉ፤የፀጥታ ኃይሎች ቁጥርና ቁጥጥር እጅግ በናረበት ሐገር ደፈጣ ተዋጊዎች በየት አልፈዉ ነዉ-ሰዎችን በጅምላ የሚገድሉት።ሥለዚሕ እንደሚመስለኝ መንግሥት ለደረሰዉ ጥፋት በሙሉ ተጠያቂ ነዉ፦ፀጥታ አስከባሪዉን መመርመር አለበት።»

ከናጄሪያ አጠቃላይ ስፋት አንድ ስድተኛዉን በሚይዙት በሰወስቱ የሐገሪቱ ክፍለ-ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ ገደብ ከተጣለ በመጪዉ ግንቦት ዓመት ይደፍናል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ