1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔቶ ጉባኤ፤ ጦርነት እና የትራምፕ ገለፃ 

ዓርብ፣ ግንቦት 18 2009

የአጠቃላይ ገቢያቸዉን 2 በመቶ ለጠመንጃ ያዋሉት ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ፤ በእዳ የምትዳክረዉ ግሪክ፤ትንሺቱ ኢስቶኒያ እና ፖላንድ ብቻ ናቸዉ።ታዛቢዎችን ያስገረመዉ ትራምፕ ሥለዋሹ አይደለም።የዲፕሎማሲ ለከት ማታጣታቸዉ-እንጂ።

https://p.dw.com/p/2deNm
Belgien NATO-Gipfel
ምስል Reuters/J. Ernst


MMT Nato Gipfel Trump - MP3-Stereo

የሠሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል ሐገራት መሪዎች ድርጅታቸዉ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት  (ISIS) ብሎ የሚጠራዉን ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገዉ ዉጊያ በቀጥታ እንዲሳተፍ ተስማምተዋል።ትናንት ብራስልስ የተሰመዉ የኔቶ አባል ሐገራት ጉባኤ አባል ሐገራት ለድርጅቱ የሚያደርጉትን የገንዘብ መዋጮ ገቢር የሚያደርጉበት ዕቅድ እንዲያቀርቡም ወስኗል። ይሁንና ጉባኤዉ ከጋራ አቋምና ሥምምነት ይልቅ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕ መመሪያ፤ ገለፀና ወቀሳ ጎልቶበት ነዉ የዋለዉ። 

28ቱም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራት ከኢራቅ-እስከ አፍቃኒስታን፤ እስከ ሶሪያ ይዋጋሉ። ግዙፉ የጦር ድርጅትም ከየጦር አዉዱ አልተለየም።እርግጥ ነዉ የመብት ተሟጋቾች በየጦርነቱ ሠላማዊ ሰዎች ማለቃቸዉ እንዲቆም መጠየቅ፤ መጮሕ ማስጠንቀቃቸዉ አልቀረም።
የብራስልሱ ጉባኤ በሚደረግበት መሐል ትናንት እንኳን የተባበሩት መንግስታት  የሠብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ ኃላፊ ዘይድ ራዐድ አል ሁሴይን ሶሪያ ዉስጥ ከአሸባሪዉ ድርጅት ISIS ጥቃት የሚያመልጡ ሠላማዊ ሰዎች በአሜሪካ መራሹ ጦር ጥቃት ሰለባ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።
የአሜሪካ አጥኚዎች በበኩላቸዉ አሜሪካ መራሹ ጦር በአንዲት የኢራቅ ከተማ ሞሱል ብቻ፤ በአንድ የመጋቢት ሳምንት ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሠላማዊ ሰዎችን በአዉሮፕላን-ቦምብ ሚሳዬል መግደሉን አረጋግጠዋል።ትናንት።
በትናንቱ ጉባኤ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉ ይቁም የሚል ሐሳብ አልተነሳም። ለየጦርነቱ ሠላማዊ እልባት እንዲፈለግ የጠየቀም የለም።የዓለም ብቸኛ የጦር ድርጅት በየጦርነቱ በቀጥታ ይዋጋ-እንጂ።እንዲያዉም የኔቶ  ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልትንበርግ እንዳሉት የማንቸስተሩ ጥቃት የድርጅቱ አባላት የፀረ-ሽብር ዉጊያቸዉን ማጠናከር እንዳለባቸዉ አመልካች ነዉ።
                               
«ማንቸስተር የደረሰዉ የአሸባሪዎች ጥቃት፤አሸባሪነትን ለመዋጋት በጋራ መቆማችንን የሚያረጋግጥ መልዕክት ማስተላለፍ እንዳለብን አመልካች ነዉ።»
ወትሮም አልተነጣጠሉም።ትናንት ደግሞ ኔቶ ISISን በቀጥታ እንዲወጋ ወሰኑ።ዉሳኔ-ዘመቻዉ ግን እግረኛ ጦርን አይጨምርም።ምክንያት፤- ሰላማዊ ሰዎች በሚያልቁ-በሚሰደዱበት ጦርነት የኔቶ ወታደር እንዳይሞት።
ታዛቢዎችን፤ያስደመመ፤ ተቺዎችን የማረከዉ ግን  የጉባኤተኞች ዉሳኔ-የመብት ተሟጋቾች ዉትወታ፤ ወይም የዉሳኔ-እዉነታዉ ተቃርኖ አይደለም።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ንግግር፤ትችትና ማስጠንቀቂያ እንጂ።አንዳዶች ንግግሩን ለሌሎቹ መሪዎች የተሰጠ መመሪያ ሲሉት፤ ብዙዎቹ ገለፃ ብለዉታል።ሌክቸር።
                     
«ከ28ቱ አባል ሐገራት 23ቱ ለመከላከያ ኃይላቸዉ መክፈል ያለባቸዉንና የሚገባቸዉን እስካሁን አልከፈሉም።ይሕ ለዩናይትድ ስቴትስ ግብር ከፋዮች ጥሩ አይደለም።እብዛኞቹ ሐገራት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ብዙ ዉዝፍ ገንዘብ አለባቸዉ።ሁሉም አባል ሐገራት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢያቸዉ 2 በመቶዉን ብቻ አምና አዋጥተዉ ቢሆን ኖሮ፤ አሁን ለጋራ መከላከያችን 119 ቢሊዮን ዶላር ይኖረን ነበር።»
ሰዉዬዉ በርግጥ አላበሉም።ባለፈዉ ዓመት የአጠቃላይ ገቢያቸዉን 2 በመቶ ለጠመንጃ ያዋሉት ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ፤ በእዳ የምትዳክረዉ ግሪክ፤ትንሺቱ ኢስቶኒያ እና ከምዕራቦች ጋር ሲነፃፀር ደሐይቱ  ፖላንድ ብቻ ናቸዉ።ታዛቢዎችን ያስገረመዉ ትራምፕ ሥለዋሹ አይደለም።የዲፕሎማሲ ለከት ማታጣታቸዉ-እንጂ። ገለፃዉ ለአዲሱ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ፤ ለሌሎቹ አስደንጋጭ፤ ለጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት «የአፀፋ ምት» ቆስቋሽ ሳይሆን አልቀረም።
                             
«ለወደፊቱ አባል ሐገር የሚመዘነዉ ለመከላከያ ምን ያሕል አወጣች በሚለዉ ሳይሆን፤ ለኔቶ አስተዋፅኦ የማድረግ አቅማችን እስከምን ድረስ ነዉ በሚለዉ መሆኑ ደስ ብሎናል።በዚሕ ረገድ እንደሚመስለኝ ጀርመን ጥሩ አቋም ላይ ናት።»
ኔቶን በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት-«ያረጀ» ያሉት ትራምፕ ያሉትን ቢሉም እንደፎከሩት ከአንጋፋዉ የጦር ድርጅት አልወጡም።ኔቶ 68 ዓመቱ ነዉ፤ትራምፕ 71። ያረጀዉ ማነዉ?

NATO Donald Trump Belgien Mimik
ምስል Getty Images/J.Tallis
Belgien Nato-Gipfel | Trump und Merkel
ምስል picture alliance/dpa/K. Nietfeld

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ