1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔዘርላንድስ ምርጫ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2009

የነገው የንዘርላንድስ ምርጫ ጊዜያዊ ችግሮችን በማጋነን እና በመደጋገም የህዝቡን ስሜት በመቀስቀስ ድጋፍ የሚያገኙ ፓርቲዎች በተጠናከሩበት በፈረንሳይ እና በጀርመንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ። በዚህ ምርጫ ለ150 የምክር ቤት መቀመጫዎች 28 ፓርቲዎች ይወዳደራሉ ።

https://p.dw.com/p/2ZATo
Geert Wilders und Mark Rutte Niederlande
ምስል picture alliance/dpa/Y.Herman

የኔዘርላንድስ ምርጫ እና ቀኝ ፅንፈኞች

የኔዘርላንድስ ህዝብ ነገ የምክር ቤት እንደራሴዎቹን ይመርጣል ። በዚህ ምርጫ ስደተኞች በብዛት ኔዘርላንድስ መግባታቸውን ፣እስልምናን እና የኔዘርልንድስን የአውሮጳ ህብረት አባልነት የሚቃወመው «የነጻነት ፓርቲ »የተባለው ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ ብዙ የምክር ቤት መቀመጫ ሊያገኝ ይችላል የሚል ግምት ሲሰነዘር ቆይቷል ። በሌላ በኩል ግምቱ ላይዝ ይችላል ሲሉ የሚከራከሩም አሉ ።  በጎርጎሮሳዊው 2017 ትኩረት ከሳቡት የአውሮፓ ምርጫዎች አንዱ ነገ በኔዘርላንድስ የሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ነው ። ባለፈው ዓመት ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2016 ፍጹም ሳይጠበቅ የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት መወሰኑ እና ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት መሆናቸው፣ በኔዘርላንድስም ከተለመደው የፖለቲካ አካሄድ ያፈነገጠ መንግሥት ሊመረጥ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል ። ቀኝ ጽንፈኞች በአውሮጳ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኙ መምጣታቸው ከኔዘርላንድስ በተጨማሪ በዓመቱ በፈረንሳይ እና በጀርመንም በሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ተጽእኖ እንዲሁ ማሳሰቡ ማነጋገሩ ቀጥሏል  ። የነገው ምርጫ  ጊዜያዊ ችግሮችን  በማጋነን እና በመደጋገም የህዝቡን ስሜት በመቀስቀስ ድጋፍ የሚያገኙ ፓርቲዎች በተጠናከሩበት በፈረንሳይ እና በጀርመንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ። በዚህ ምርጫ ለ150 የምክር ቤት መቀመጫዎች 28 ፓርቲዎች ናቸው የሚወዳደሩት ። ከመካከላቸው አንዱ በጌርት ዊልደርስ የሚመራው   ፓርቲ ፎር ፍሪደም ወይም የነፃነት ፓርቲ የተሰኘው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ነው ። በጋራ ገንዘብ ዩሮ መገበያየትን እና እስልምናን የሚቃወመው ይህ ፓርቲ እና ገዥው የነጻነት እና የዴሞክራሲ ለዘብተኛ ፓርቲ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ ፉክክር ሲያካሂዱ ቆይተዋል ። የዊልደርስ የምርጫ ዘመቻ መፈክር «ኔዘርልንድስ እንደገና የኛ ትሆናለች» የሚል ነው ። ሲያስተላልፉ የቆዩት መልዕክትም ስደተኞች ወደ ኔዘርላንድስ እንዳይገቡ ድንበርን መዝጋት ኔዘርላንድስን ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ማስወጣት የጋራውን ሸርፍ ዩሮን መተው እና የተለመደው የፖለቲካ አካሄድ በአጠቃላይ የሚቃወም ነው ። በርግጥ በኔዘርላንድስ የስደተኞች ቁጥር ዜሮ ሊባል ከሚችል ደረጃ ተነስቶ ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ወደ አስር በመቶ አድጓል ። በነዚህ  ጊዜያትም ይህን እንደ ችግር እያነሱ የህዝቡን ስሜት የሚቀሰቅሱ ፖለቲከኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ። ከመካከለቸው ጌርት ዊልደርስ የመሪነቱን ቦታ ይይዛሉ ። አቶ ሲራክ አስፋው  39 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ኔዘርላንድስ ኖረዋል ። በማህበራዊ ጉዮች መስሪያ ቤት ውስጥ የምክር አገልግሎት ይሰጣሎ ። የኔዘርላንድስን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉት አቶ ዮናስ ፣ዊልደርስ የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ የተለያዩ ስልቶችን ቢጠቀሙም ፣ አመዛዝኖ ድምጽ የሚሰጠውን ዜጋ ድጋፍ ማግኘታቸውን  ይጠራጠራሉ ። ይሁንና  ዊልደርስን የሚመርጡ ጥቂት ላይሆኑም ይችላሉ ይላሉ ።

Niederlande vor der Wahl | Mark Rutte
ምስል picture alliance/abaca/D. Aydemir

ሆላንድን ወደ መሰረቷ ወደ ክርስትና እመልሳለሁ የሚሉት ዊልደርስ እስልምናን ጠላት ነው የሚሉት ።  በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት  ሀገራቸውን መታደግ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ ።

«ሰዎች እንደገና እንዲመቻቸው ማድረግ ኔዘርልንድስን ለነርሱ መልሶ ለመስጠት ፤ለዚህ ብቻ ነው የምታገለው ።ለዚህም ነው ይህ ምርጫ ወሳኝ እና ታሪካዊ ምርጫ የሆነው ። ይህን ካላደረግን ግን ህይወታችን ይቆማል ።ኔዘርላንድስን እናጣለን ። ምንም ዓይነት ነፃነትም ሆነ ሉዓላዊነት አይኖረንም »

ዊልደርስ የተለመደውን ፖለቲካዊ አካሄድ ይቃወማሉ ። የብሪታንያን ከአውሮጳ ህብረት መውጣት  እና በአሜሪካንም ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት መመረጣቸውን የሚደግፉ ፖለቲከኛ ናቸው ። ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሠረት በነገው ምርጫ የዊልደርስ ፓርቲ አሁን በምክር ቤት ውስጥ የያዘውን መቀመጫ በእጥፍ ሊያሳድግ የሚችል ውጤት ያገኛል የሚል ግምት አለ ። በነዚሁ መመዘኛዎች ዊልደርስ ቀላል አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የቅርብ ጊዜው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ዊልደርስ ያላቸውን የህዝብ ድጋፍ 15 በመቶ አካባቢ ያደርሰዋል  ።ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ የሚመራው ገዥው ወግ አጥባቂው ለዘብተኛ ፓርቲ ካለው ድጋፍ በመጠኑ የሚያንስ ነው ተብሏል ። ፓርቲዎች ተጣምረው መንግሥት የመመሥረት ልምድ ባለባት በኔዘርላንድስ  ዊልደርስ ቀላል አብላጫ ድምጽ አግኝተው ቢያሸንፉ እንኳን ሁሉም ፓርቲዎች ማለት ይቻላል ከርሳቸው ጋር ተጣምረው መንግሥት መመሥረት አይፈልጉም ።  በርካታ የኔዘርላንድስ ፖለቲከኞች የዊልደርስን ፖሊሲ ጠብ አጫሪ እና ኢ ህገ መንግሥታዊ ሲሉ ይቃወሙታል ። በአሁኑ ምርጫ የሚወዳደሩት የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ ከርሳቸው ጋር መሥራት እንደማይፈልጉ ካሳወቁት የኔዘርላንድስ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው ።

Niederlande | Geert Wilders auf Wahlkampfveranstaltung
ምስል Reuters/M. Kooren

«ለኔዘርላንድስ ህዝብ መልዕክቴን ለማስተላለፍ እየታገልኩ ነው ። በተቻለ መጠን ስለ ኔዘርላንድስ መጻኤ እድል ስላለኝ አመለካከት  ከብዙ ሰዎች ጋር እየተወያየሁ ነው ። ከዚህ የተለየ ሰው ጋር ግን አላደርገውም ።»ማርክ ሩተ የተለየ ሰው ያሉት ስደተኞች በብዛት ወደ ሀገሪቱ በገቡበት በዚህ ወቅት ላይፍልሰት ችግር ያመጣል ፣ የኔዘርላንድስን ህዝብ ማንነት እና እሴቶች ይሸረሽራል እያሉ በህዝቡ ዘንድ ፍርሀት የሚነዙትን ዊልደርስ ነው ። ይሁን እና የዊልደርስ ጠንካራ ተፎካካሪ  የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ ከዊልደርስ ጋር ስልጣን አልጋራም ቢሉም በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2010 ሥልጣን ሊይዙ የቻሉት መንግሥታቸውን እንዲደግፉ ከዊልደርስ ጋር ከተስማሙ በኋላ ነበር ። የማርክ ሩተ ፓርቲ ግን ይህ አሁን አይደገምም እያለ ነው ። ዊልደርስ ከ2010 ዓም አንስቶ ሙስሊም ስደተኞች ወደ ኔዘርላንድስ እንዳይገቡ ይታገዱ፣ እንዲሁም እስልምናን የፋሹስት ሃይማኖት ነው እያሉ ቅስቀሳ ያካሂዱ ነበር ። ከሰባት ዓመታት በኋላ ደግሞ አሁን ኔዘርላንድስ የሚገኙ መስጊዶች በሙሉ እንዲዘጉ ፣ ቁራን መሸጡ እንዲቆም እንደሚፈልጉ እና እንደሚያደርጉትም ቃል ገብተዋል ። ይሁን እና ይህ የዊልደርስ ምኞት የኔዘርላንድስ ህገ መንግሥት የሚያረጋግጠውን የሃይማኖት ነፃነት የሚጋፋ ነው ።ያም ሆኖ እነዚህ ሀሳቦችም የአንዳንድ ኔዘርላንዳውያንን ቀለብ መሳባቸው አልቀረም ።አንዳንዶች ስደተኞች ከዜጎች በላይ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል የሚል ቅሬታ ይሰነዝራሉ ።ይህም እኚህ ዜጋ እንደሚሉት ዊልደርስን የሚመርጡበት ምክንያት ነው ።

« ተገን የተሰጣቸው ስደተኞች ከና ከዜጎቹ በላይ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ።  ለዊደርስ ድምጼን የምሰጥበት ዋናው  ምክንያት ይሄ ነው ።»

ዊልደርስ ከአውሮፓ ህብረት መስራች ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኔዘርላንድስ ብሪታንያ እንዳደረገችው ከአውሮጳ ህብረት እንድትወጣ ይፈልጋሉ ።  በሀገሪቱ በጋራው የመገበያያ ገንዘብ ዩሮ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም ይጠይቃሉ ። እኚህ ሞሮኮአዊ ነጋዴ ደግሞ ይህ የዊልደርስ አቋም ለሀገሪቱ ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም ነው የሚሉት ። «የሚፈልገው ድንበሮቹን መዝጋት ነው ።ዊልደርስ ሀገሪቱን የሚመራ ከሆነ ለኔዘርላንድስ ኤኮኖሚ ጥሩ አይደለም ።»

Infografik Umfrage Wahl Niederlande 2017 DEU

አቶ ሲራክ ዊልደርስ ብዙ መራጭ ቢያገኙም አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ ብለው አያስቡም።

በቅርቡ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው የኔዘርላንድስ ህዝብ በሀገሪቱ ፖለቲከኞች ላይ እምነት አጥቷል ።እንደ ጥናቱ ከ61 በመቶው በላይ የሚሆነው ህዝብ ፖለቲከኞቹ ተዓማኒ አይደሉም ብሎ ነውየሚያስበው  ። ይሁን እና ህዝቡ በፖለቲከኞቹ ላይ ያለው እምነት ቢቀንስም ድምፅ ለመስጠት የሚወጣው ህዝብ ቁጥር ግን ከፍተኛ ነው ። ከመካከሉ እስካሁን ማንን እንደሚመርጥ ያለወሰነም አለ። ለምሳሌ እኚህ የቮለንዳም ነዋሪ አንዱ ናቸው ።

«ለመወሰን እቸገራለሁ ። በዓለማችን ብዙ ክስተቶች ስለነበሩ ራስን አንዱ ጋ ለማድረግ ይከብዳል ። ስለዚህ እኔ ማንን እንደምመርጥ እስካሁን አላውቅም ። እንደምመርጥ ግን አውቃለሁ ።»

17 ሚሊዮን ህዝብ ባላት በኔዘርላንድስ ድምፅ መስጠት የሚችለው ቁጥር 12.6 ነው ። ዘንድሮ የድምጽ ቆጠራ የሚካሄደው እንደቀድሞው በአውቶማቲክ መቁጠሪያ ሳይሆን  በእጅ ነው ። ድምፅ ጠላፊዎችን ለማገድ የታሰበ የተሰጠ መፍትሄ ነው  ። የተወዳዳሪ ፓርቲዎቹ  መብዛት ከውጤቱ በኋላ ተጣማሪ መንግስት ሊመሠርቱ የሚችሉትን ፓርቲዎች ቁጥር ያሳድጋል የሚል ግምት አለ ። ምናልባትም 4 ወይም ከዚያ በላይ ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ሊመሰርቱ ይችሉ ይሆናል ። እስካሁን በተሰበሰበው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ  በሥልጣን ያለዉ ለዘብተኛ ፓርቲ  ከ24 እስከ 28 የሚደርሰዉን የምክር ቤት መቀመጫ ያገኛል የሚል ግምት አለ ። የዊልደርስ ፓርቲ ደግሞ ከ20 እስከ 24 ያገኛል እየተባለ ነው ። ማን ምን ያህል መቀመጫ እንደሚያገኝ  በነገው ምርጫ ይለያል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ