1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንፁህ መጠጥ ዉኃ ችግር በከተሞች

ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2009

በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች የንፁህ መጠጥ ዉኃ እጥረት እንዳጋጠማቸዉ ነዋሪወች በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። በተለይ በአዲስ አበባ ከ መጠጥ ዉኃ እጥረትና መቆራረጥ ባለፈ የጥራት ችግር በመኖሩ ለአንዳንድ ዉኃ ወለድ በሽታዎች እየተጋለጥን ነዉ ሲሉ ነዋሪወች ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/2dCY0
Äthiopien Wokro In the drought area in Wokro ( avalibility of Water by UNESCO support )
ምስል DW/G. Tedla

Shortage of Clean Water in Addis Ababa and other cities - MP3-Stereo

የአዲስ አበባ ዉኃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ ስፋት እንደሌለዉ ጠቁሞ ለመፍትሄዉ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በሎጊያ ፣በመናገሻ፣  በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች ነዋሪወች እንደገለፁት በየአካባቢወቻቸዉ የመጠጥ ዉኃ ችግር ከፍተኛ ነዉ። አህመድ ሙሃመድ የተባሉ የአፋር ክልል የሎጊያ ከተማ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት በከተማዋ የአብዛኛዉ ክፍል ዉኃ ከተቋረጠ ከሳምንት በላይ በመሆኑ ከቦታዉ ሞቃታማነት ጋር ተያይዞ ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘዉ የመናገሻ ከተማም ችግሩ ተደጋጋሚ መሆኑ ተገልጿል። የከተማዋ ነዋሪ እንደሆኑ የገለጹልን አቶ ሰሎሞን እንደሚሉት በአካባቢዉ ዉኃ መጥፋትና መቆራረጥ የተለመደ ችግር ሆኗል። ከዚህ የተነሳም የአካባቢዉ ነዋሪ ዉኃ ለመግዛት ለበርካታ ስዓታት እንደሚሰለፍ ገልጸዉ ችግሩን ለሚመለከተዉ አካል ቢያሳዉቁም የመብራት ችግር ነዉ ከማለት የዘለለ መፍትሄ አለመገኘቱን ተናግረዋል።
ሌላዉ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ጀማል የተባሉ የሰበታ ከተማ  ነዋሪ  እንደገለፁት በዚህ ወር በአካባቢዉ ዉኃ የለም። ሕዝቡ የጉድጓድ ዉኃ እንደሚጠቀምና በግዥ ለአንድ ጀሪካን ዉኃ እስከ 10 ብር እንደሚያጣ ነዋሪዉ አብራርተዋል።
በአዲስ  አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢወችም የመጠጥ ዉኃ ችግር ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። በከተማዋ ከሚያጋጥመዉ የመጠጥ ዉኃ መቆራረጥና መጥፋት ባሻገር የንጽህና ጉድለትም ሌላዉ ችግር መሆኑ ተገልጿል።
የሌሎቹን ከተሞች የሚመለከታቸዉን አካላት ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት ባይሳካም ፤የአዲስ አበባ ከተማ የዉኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ግን ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም እንደገለጹት ቀደም ሲል ችግሩ ስፋት እንደነበረዉ አስታዉሰዉ ከ2008 ጀምሮ ግን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ በርካታ ሥራወች በመሥራታቸዉ የዉኃ አቅርቦቱ በከተማዋ ተሻሽሏል ይላሉ።
ይሁን እንጅ በአንዳንድ አካባቢወች በመብራት መቆራረጥ፣ በቧንቧዎች እርጅናና በመሳሰሉ ምክንያቶች  አሁንም ድረስ ችግር መኖሩን ጠቁመዉ መስሪያ ቤታቸዉ ችግሩን ለመፍታት እየጣረ መሆኑን አስታዉቀዋል።
የዉኃ ብክለት መከሰቱንም ኃላፊዉ አልካዱም። ምክንያቱ ግን የቧምቧዎች ማርጀት በመሆኑ አሮጌ መስመሮችን በአዲስና በቀላሉ በዝገት በማይበላሹ የመተካት ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ችግሩ እንደተከሰተ ወዲያዉኑ ቢያሳዉቅ የሚስተካከል መሆኑን አመልክተዋል።
በመብራት መቆራረጥ ሳቢያ የሚከሰዉን የዉኃ እጥረት ለማቃለልም  ጄኔሬተሮች መገዛታቸዉን ሀላፊዉ ተናግረዋል። በጋምቤላ፣ በባህርዳር በባኮና በሌሎች የሀገሪቱ አንዳንድ ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር እያጋጠመ መሆኑን ከነዋሪዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

Äthiopien Schlimmste Hungersnot seit 30 Jahren
ምስል Reuters/T. Negeri

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ