1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግርና የምዕተ-ዓመቱ ግቦች

ዘርይሁን ታደሰሐሙስ፣ ሚያዝያ 28 1996

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እ.አ.አ. በ2015 መደረስ ያለባቸው ብሎ ያስቀመጣቸው ስምንት ግቦችን የመምታቱ ጉዳይ አጠራጣሪ እየሆነ መጥቷል። ይህ ከሚገለፅባቸው ገፅታዎች አንዱ የንፁህ ውሃ አቅርቦትና የጽዳት አገልግሎት ለመስጠት የታለመው ግብና ግቡን ለመምታት የሚደረገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያለመጣጣም ማሳየት ነው።

https://p.dw.com/p/E0fk
ምስል Christoph Hasselbach
የዓለም ቀጣይ ልማት ጉባኤ በጆሃንስበርግ ከተካሄደ እነሆ ሁለት ዓመታት አለፉት። በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን ያኔ የንፁህ ውሃ አቅርቦትንና የመጸዳጃ አገልግሎትን በተመለከተ ሃገራትና መንግሥታት የገቡትን ቃል በተግባር እስከዛሬ መለወጥ አቅቷቸዋል።
በቅርቡ በኒው ዮርክ ለሁለት ሳምንታት ያህል የቀጣይ ልማት ኮሚሽን የሚባለውና በጆሃንስበርጉ ጉባኤ የተቋቋመው አካል ስብሰባ ተቀምጦ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የኖርዌይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትርና የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በርገ ብሬንደ ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በዚሀ ከቀጠለ የምዕተ-ዓመቱን ስምንት ግቦች እንደታሰበው የዛሬ 11ዓመት በኃላ ልንመታቸው እንደማንችል ይናገራሉ። እንደሳቸው ግምት በዓለማችን ከሦስት እስከ አምሥት ሚሊዮን ሰዎች በውሃ ወለድ በሽታዎች በየዓመቱ ይጠቃሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርኃ ግብር በበኩሉ፥ከዓለማችን ሕዝቦች በቁጥር ከቢሊዮን የሚበልጠው በከፍተኛ ድህነት የሚሰቃይ ሲሆን ምንም ዓይነት ንፅህናው የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አያገኝም።
በጆሃንስበርጉ ጉባኤ ኃብታሞቹ ሃገራት ዳጎስ ያለ የመዋዕለ-ንዋይ ዕርዳታ፥ የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለማሸጋገርና ለአካባቢ ጥበቃ የሚረዱ መሢያዎችን ለድሆቹ ሃገራት ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።ያኔ ይህ ዕርዳታ የድሃ ሃገራት የምዕተ-ዓመቱን የልማት ግቦችን ለመምታት ያስችሏቸዋል ተብለው ቢጠበቁም የተፈለገው ውጤት ግን ሳይመጣ ቀርቷል።
አይ.ፒ.ኤስ. የተባለው የዜና ወኪል እንዳናገራቸው የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ከሆነ የዚህ ውጤት ማጣት ዋነኛ ምክንያት ለዚህ ዓላማ የሚውል መዋዕለ-ንዋይ ምንጮች መታጣት ነው። በድርጅቱ የምጣኔ ኃብትና የማህበራዊ ጉዳዮች ተቀዳሚ ዋና ጸሓፊ የሆኑት ሆዜ አንቶኒዮ ኦካምፖ የምዕተ-ዓመቱን ግቦች ለመምታት ሃገራት በአሁኑ ሰዓት ለዚህ ዓላማ እያወጡ ያሉትን ወጪ ሁለት እጅ ማውጣት ይኖርባቸዋል ይላሉ።“ይህም ማለት” ይላሉ ሲያብራሩ “ባሁኑ ሰዓት እያወጣን ካለነው 16 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 32 ቢሊዮን መሻገር ይኖርብናል ማለት ነው።”
ሆኖም ይህም መጠን ቢሆን የንፁህ ውሃና የመጸዳጃ አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር በጣም አናሳ ነው፥ እንደ ባለሙያዎች አባባል።ቀጥለውም ይህንን ችግር መቅረፍ የሚቻለው ሃብታም ሃገራት ለድሆቹ የሚሰጡትን ዕርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ሲችሉ ብቻ ነው ይላሉ። እኒህ ሃገራት ግን ለድሆቹ የሚሰጡትን ዕርዳታ የመጨመር ፍላጎቱ የላቸውም። ይልቁንስ አንዳንዶቹ በሙስና እያሳበቡ የሚሰጡትን የዕርዳታ መጠን እየቀነሱ ይገኛሉ። ይህም በመሆኑ ድሃ ሃገራት ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል።
ከሃብታም ሃገራት እንደ ሃሳብ እየቀረቡ ካሉት አማራጮች አንዱ የንፁህ ውሃ አቅርቦትንና የመጸዳጃ አገልግሎትን ወደ የግል ባለቤትነት ማዘዘዋወር ነው። ይህ ሃሳብ ግን ተጠቃሚዎችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው በሚል የድሆች ሃገራት መንግሥታትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አይቀበሉትም። በተጨማሪም በቅርቡ ተቀማጭነቱን በካናዳ ባደረገ አንድ ድርጅት በሃያ ድሃ ሃገራት ውስጥ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት መሠረት በነዚህ ሃገራት የሚኖረው ሕዝብ ባብዛኛው እነዚህ አገልግሎቶች ለግል ድርጅቶች መዘዋወራቸውን እንደሚቃወም አስታውቋል።
የአውሮጳ ኅብረት ከለጋሽ ሃገራት በተለየ መልኩ ለዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የሚሰጠውን ዕርዳታ እንደሚጨምር አስታውቋል። በዚህም መሠረት በኮቶኑ ስምምነት ሥር ለሚካተቱ የአፍሪቃ፥ የካሪቢያንና የሰላማዊ ውቅያኖስ ሃገራት የሚሆን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር የሚልቅ ገንዘብ ለውሃና ውሃነክ ፕሮጄክቶች ማስፈፀሚያ አስቀምጧል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግን ይኸም ቢሆን አገልግሎቶቹን ወደግል ከማዛወር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ፍርሃት አላቸው። በመሆኑም እነዚህ ድርጅቶች ባንድ ላይ በመወገን ኅብረቱ ለሃገራቱ የሚሰጠውን ዕርዳታ አገልግሎቶቹን ወደ ግል ከማዘዋወር ጋር እንዳያያይዝ እየተማፀኑ ይገኛሉ።