1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖቤል ሽልማት በ 3ቱ የሳይንስ ዘርፎች፣

ረቡዕ፣ መስከረም 24 2004

በተፈጥሮ የሳይንስ ዘርፎች፤ ፊዚክስ፤ ሥነ-ቅመማና ሥነ -ህይወት (BIOLOGY)፣ በተለይ የህክምና ምርምር ፣ የዘንድሮዎቹ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ማንነት፤ ከትናንት በስቲያ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በእስቶክሆልሙ የካሮሊንስካ ተቋም የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በተከታታይ በይፋ ተበሥሯል።

https://p.dw.com/p/RpCD
በፊዚክስ፤የዘንድሮዎቹ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፤ ከግራ ወደ ቀን፤ ሶል ፐርልሙተር፤ አዳም ጂ.ሪስ ፤ እና ብራያን ፒ. ሽሚት፣ምስል picture alliance/dpa/DW-Montage

ለሰው ልጅ ብርቱ መቅሠፍት ከሆኑት አደገኛ በሽታዎች መካከል አንዱ ነቀርሳ(ካንሠር)አብነት ይገኝለት ይሆን?መንገድ የጠረጉ ተማራማሪዎች ነበሩ፤ ከትናንት በስቲያ የታዋቂው የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች መሆናቸው የተበሠረው!አሜሪካዊው ብሩስ ቦይትለርና የሉክሰምቡርኹ ተወላጅ ዩልስ ሆፍማን፤ እ ጎ አ ከ 1990ኛዎቹ ዓመታት አንስቶ ፣ ማንኛውም የሰውነት ጠንቅ የሆነ ተኀዋሲ አካል ውስጥ ገብቶ ሲወር፤ የሚቀበለው የፕሮቲን ዓይነት የትኛው እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፤ የተውሳክ መከላከያ የተፈጥሮ ኀይል የመጀመሪያው እንቅሥቃሴ እንዲጠናከር ማድረግ የሚቻልበትንም ብልሃት ያገኙ ተመራማሪዎች ናቸው። ባለፈው ዓርብ ፣ በ 68 ዓመታቸው በካንሠር ሳቢያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፤ ካናዳዊው የህክምና ተመራማሪ ራልፍ እስቴይንማን ፤ ከ20 ዓመት ገደማ በፊት አንስቶ፣ ሲያካሂዱ በነበረው ምርምራቸው ይታወቃሉ። እስቴይንማን፤ በሠራ-አካላችን የውጭው ቆዳ ክፍል ያሉ ኅዋሳት እንዲተጉ መልእክት የሚያስተላልፉ፤ ወረራ የሚያካሂዱ ተኀዋስያን እንዲጠቁ ከተደረገ በኋላም ፣ ቀጣዩን የበሽታ መከላከያ ተግባር የሚያንቀሳቅሱ ኅዋሳትን ፣ሥራውን የሚያስተካክሉትንም ሆነ የሚመሩትን ጠንቅቀው በመከታተላቸውና ፤ ካንሠርንና ሌሎች ተዛማች በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል ለሚቻልበት ብልሃት ዐቢይ ድርሻ በማበርከታቸው ነበረ ለዘንድሮው የኖቤል ሽልማት ታጭተው የነበሩት። ግን ያሳዝናል! የተመራመሩበት ጠንቀኛው በሽታ ፣ ነቀርሳ(ካንሠር) ዕድሜአቸውን አሣጠረው።

3 ቱ ተመራማሪዎች አሁን እጅግ ከፍተኛ ስም ያለው የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ለመሆን ከመብቃታቸው በፊት፤ ለምሳሌ ያህል ቦይትለርና ሆፍማን፤ እ ጎ አ በ 2004፤ እስቴይንማን እ ጎ አ በ 1999 ዓ ም የታወቀውን የጀርመን ሽልማት የሮበርት ኮህን ሽልማት ተቀብለው ነበር። «የአሜሪካ ኖበል ሽልማት» የሚሰኘውን የ Albert Lasker ሽልማት ደግሞ ፣ እስቴይንማን እ ጎ አ በ 2007 ማግኘታቸው ታውቋል።

እንደገናም ፤ 3ቱ ሳይንቲስቶች፤ የአሌክሳንደር ሁምቦልትን የምርምር ሽልማት ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።

የእስቴይንማን ምርምር ውጤት፤ ወደፊት ለተለያዩ በሽታዎች ክትባት ለማዘጋጀት፣ ሳይረዳ እንደማይቀር ነው የሚታሰበው። በጀርመን ሀገር በ Tübingen ዩኒቨርስቲ የበሽታ መከላከያ ምርምር ነክ ፕሮፌሰር ሐንስ-ጊዖርግ ራመንዜ፤ 3 ቱ ተመራማሪዎች የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች መሆናቸው እንደተነገረ፤ ይገባቸዋል በማለት በደስታ ነው ብሥራቱን የተቀበሉት፤

«እንዴታ! ደስ ነው ያለኝ፤ በተለይ ራልፍ እስቴይንማን በማሸነፋቸው። በተለይ በበሽታ ተከላካይ ኅዋሳት ላይ ያደረጉት ምርምር ፤ ለሽልማቱ ፍጹም ብቁ ያደርጋቸዋል። »

ሰውነትን የሚጎዳ ተኀዋሲ አካል ውስጥ ሲገባ ፣ እንደ ዘበኛ ቆመው የሚጠባበቁት፤ የኮከብ ዓይነት ቅርፅ ያላቸው ኅዋሳት ተኀዋሲውን ይሰለቅጡና መልሰው አበጥረው ፤ ለይተው ይዘረግፉታል። ያኔም በተራ የከዋክብት መሰሎቹ ኅዋሳት የትግል ዘመቻ ይካሄዳል። እነርሱም ነጥለው ተኀዋሲውን ያጠቃሉ።

ለህክምና አዲስ በር መከፈቱን የሚያምኑት የክትባት ጉዳዮች ተመራማሪ ሃንስ ጊዖርግ ራመንዜ፣ በመጨረሻ እንዲህ ብለዋል።

«ያተኮረንበት ሙያ፤ በእነዚህ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ድጋፍ ጭምር ፤ ለምሳሌ፤ በተጨባጭ ሁኔታ ካንሠርን ለመታገል፤ በተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ ዘዴን በማትጋት ፤ ካንሠሩን የሚያጠቃውን መከላከያ ማወቅ የሚበጀን ነው።»

ፍጥረተ ዓለምና ሀድ በሌለው መጠኑ የታላላቅ ከዋክብት ፍንዳታ ጠቋሚነት፣

ሲያስቡት ህልም እንጂ ፣ እውን አይመስልም። ከቅርባችን ያለው፣ ተጣርቶ ሳይመረምር ፣ የህልም ዓለም ስለሚመስለው፤ ለማወቅ መጣሩ ፤ የሰውን ልጅ የማወቅ ጉጉነት ከማመላከት አልፎ፣ ምን ዓይነት ፋይዳ ያስገኝ ይሆን?!

እስካሁን ድረስ፣ ከብርሃን የሚፈጥን ምንም እንደሌለ ነው የሚታወቀው። እርግጥ ነው፣ በቅርቡ የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN)፣ ኢምንት የአቶም ቅንጣቶች «ኒውትሪኖስ» ከብርሃን ፍንጠቃ በላቀ ፍጥነት ሳይንቀሳቀሱ እንዳልቀሩ መጠቆሙ የሚታወስ ነው። ያም ሆኖ ፣ ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ አይደለም። ስለዚህ እስካሁን ምንጊዜም ፈጣኑ ብርሃን ነው ማለት ይቻላል። ብርሃን በሴኮንድ 299,792,458 ሜትር (ከሞላ ጎደል በሴኮንድ 300,000 ኪሎሜትር ነው) የሚፈነጥቀው። ለምሳሌ ያህል ፀሐይ፤ ከምድራችን 150 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቀት ያላት ሲሆን፣ ብርሃንዋ የሚደርሰን በ 8 ደቂቃ ከ 19 ሴኮንድ ነው። ሰው፣ በዚህ የብርሃን ፍጥነት መጓዝ ቢችል፤ ማለት በሴኮንድ 300,000 ኪሎሜትር መክነፍ ቢችል፤ እናም ከ 25 እስከ 65 ዓመቱ ፤ 40 ዓመታት ቢጓዝ፣ ርቀቱ ከ 40 የብርሃን ዓመታት ላይበልጥ ይችላል። እናም ከምድራችን ከ 20 እስከ 40 የብርሃን ዓመታት ርቀት ካላቸው ከዋክብት ብቻ ነው መድረስ የሚችለው።

አንድ የብርሃን ዓመት 6 ትሪሊዮን ማይልስ ገደማ ወይም 9,5 ትሪሊዮን ኪሎሜትር ገደማ ነው። የሥነ ፈለክ ጠበብቱ፣ 21 ሚሊዮን የብርሃን ዓመት ገደማ ርቀት ስላላቸው ከዋክብት ሲያወሱ ፤ ከተዘረጋ 13,75 ቢሊዮን ዓመታት እንደሆኑት ስለሚገመተው ኅዋ ምንነት አስቡ! ከዘንድሮዎቹ በፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚዎች ጋር ማለት ነው!

በሙዩኒክ ፤ የጀርመን የማክስ ፕላንክ ተቋም የሥነ ፈለክ ምሁር ሃንስ -ቶማስ ያንካ እንደሚሉት ተሸላሚዎቹ ለዚህ ሞገሥ የበቁት ፣ --

በፊዚክስ የዘንድሮ ሽልማት አሸናፊዎች የሆኑት ጠበብት፤ ከ 50 በላይ የሚሆኑ እጅግ ራቅ ብለው የሚገኙ ግዙፍ ከዋክብት(ሱፐርኖቫዎች)(ከእኛዋ ፀሐይ ፤ ቢያንስ 8 እጥፍ የላቀ ግዝፈት ያላቸው መሆናቸው ነው፤ )የሚፈነጥቁት ብርሃን ከተጠበቀው በላይ ደካማ ሆኖ መገኘቱን በምርምራቸው ላይ ደርሰውበታል። ይህ ደግሞ ፣ እንደተባለው ፍጥረተ ዓለም መጠኑ እጅግ እየሰፋና ፍጥነቱም እጅግ እየናረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው የሚያስረዳው። የፍጥረተ ዓለም መጠን እጅግ እየሰፋና ፈጥነቱም እየናረ መሄዱ ከቀጠለ፤ ፍጻሜው ወደ በረዶ መለወጥ ይሆናል ነው የሚባለው። ፍጥረተ ዓለምን የሚያከንፈው «ጽልመታዊ ኀይል (Dark Energy) የሚሰኘው ነው ። ይህ ደግሞ ከፍጥረተ ዓለም በበይት ምሥጢራት አንዱ መሆኑ ነው የሚነገረው። ፍጥረተ ዓለም ፣ መገመት በሚያዳግት ፍጥነት በሚጓዝበት የማያልቅ ጉዞ፣ ፕላኔታችን፤ ምድርና በውስጥዋና በላይዋ የሚኖረው ፍጡር ፤ ጸሐይና አጫፋሪዎቿ ፕላኔቶች፤ ጨረቃዎች፤ ስብርባሪ ከዋክብት ፤ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ የሚገኙበት የኅዋ ቀጣና ፤ ፍኖተ ኀሊብ (MILKY WAY)በሰዓት 2,1 ሚሊዮን ኪሎሜትር ነው የሚከንፈው።

ስለኅዋ ፤ ስለ ጽልመታዊ የኃይል ምንጭም ሆነ ፤ ጽልመታዊ ቁስ አካል ስለሚባለው የሚታወቅ ነገር የለም። ታዲያ እምብዛም በማይታወቅ ጉዳይ፣ ተማራማሪዎች እጅግ ከፍተኛው ሽልማት ሲሰጣቸው ማስገረሙ አይቀርም። አሁንም ሃንስ ቶማስ ያንካ፤

«እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ሽልማቱ አስገርሞኛል፤ እርግጥ ነው ግኝቱ፤ ሥር ነቀል ሊሰኝ የሚችል ነው። የፍጥረተ-ዓለም ተመራማሪውን ዓለም፣ መሠረታዊ አመለካከትም አጠያያቂ ነው የሚያደርገው።

በሌላ በኩል እነዚህ እጅግ ግዙፍ የሩቅ ከዋክብት (SUPERNOVAE)ምነነታቸውና ባህርያቸው መቶ በመቶ የሚታወቅ አይደለም። እንዲሁም ጽልመታዊው የኃይል ምንጭ የሚሰኘው ከዋክብቱን የሚያከንፈው ኃይል ምንነት በትክክል አይታወቅም። ታዲያ ለአንዲህ ዓይነቱ «ሾላ በድፍን» ዓይነት የምርምር ውጤት የኖቤል ሽልማት መስጠቱ አያስደምም አይባልም።»

ትናንት በፊዚክስ የዘንድሮዎቹን የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ሥም ያበሠረው የአስቶክሆልሙ ተቋም፤ ዛሬም ረፋድ ላይ፤ በሥነ ቅመማ የ 1,5 ሚሊዮን ዶላር (10 ሚሊዮን ክሮነ)አሸናፊው Daniel Shechtman የተባሉ እሥራኤላዊ ሳይንቲስት መሆናቸውን አስታውቋል። ዳንኤል ሸሽትማን ለዚህ ከፍተኛ ሽልማት የበቁት፤ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ እንደገለጸው፤ ጠጣር ፤ በአመዛኙም አንጸባራቂ ጣጣር ነገሮች(ክሪስታልስ) ፣ እንበል አልማዝ መሰል ማዕድናትና ሌሎችም፤ በተስተካካለ መጠን፤ የአቶም ቅንጣቶች የሚገኙባቸውና ተደጋጋሚ ቅርጽ የሚታይባቸው ናቸው ተብሎ የሚታመንበትን ሁኔታ በሚጻረር መልኩ፤ በተፈጥሮ ፤ ተደጋጋሚ ቅርጽ የማይታይባቸው ብርቅ የሆኑ አንጸባራቂ ጠጣር ቁስ አካሎችን ማግኘት እንደሚቻል በምርምር በማረጋገጣቸው ነው። አድማጮቻችን፣ የዛሬውን ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብር እዚህ ላይ እንደመድማለን፤ ሳምንት በተለመደው ክፍለ ጊዜ መልሰን እስክንገናኝ ፣ ተክሌ የኋላ ነኝ ፤ ደህና ሁኑ።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ