1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአልጀሪያ ምርጫ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 2009

በአልጀርያ ዛሬ ምክር ቤታዊ ምርጫ ተካሂዷል። ይሁን እና ምርጫው የጥቂት አልጀሪያውያንን ትኩረት ብቻ መሳቡ እንደ አንድ ችግር ተወስዷል። ምን ያህል መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት ይወጣሉ የሚለው እስከዛሬዋ እለት ድረስ ሲያነጋግር የቆየ ጉዳይ ነበር። ምርጫው ይጭበረበራል የሚል ስጋት ያላቸው አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል።

https://p.dw.com/p/2cOe2
Wahlen in Algerien Präsident Abd al-Aziz Bouteflika
ምስል picture-alliance/dpa/S. Djarboub

MMT Algerien Parlamentswahl - MP3-Stereo


ዛሬ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ያካሄደችው አልጀሪያ አስቸጋሪ የኤኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው። በዚህ የተነሳም የበጀት ቅነሳ እና የቁጠባ እርምጃዎችን ወስዳለች። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለብዙ ጊዜ ታመው ነበር። እርሳቸውን ተክቶ ማን ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ እንደቆየ ግልጽ አልነበረም ። ዛሬ ግን በተሽከርካሪ ወንበር እየተገፉ ድምጻቸውን ሲሰጡ ታይተዋል። እነዚህ ዛሬ በተካሄደው ምክር ቤታዊው ምርጫ ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ ከሚባሉት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። አልጀሪያ ዝግ አገር ብትባልም በርካታ ዜጎቿ ግን ሃሳባቸውን በቀጥታ ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም፤ ስለ ምክር ቤታዊው ምርጫም ቢሆን። ከምርጫው በፊት ቃለ መጠየቅ ከተደረገላቸው አልጀሪያውያን አንዳንዶቹ ምርጫ ስለመኖሩ እንኳን አያውቁም አንዳንዶቹ ደግሞ የሚመርጥ መኖሩንም ይጠራጠራሉ። 
«እኔ ለመምረጥ የሚወጣ አላውቅም»
«ምን ምርጫ አለ? ይህን በፍጹም አላውቅም ።» 
40 ሚሊዮን ህዝብ ካላት አልጀሪያ 23 ሚሊዮኑ ድምጹን መስጠት ይችላል። ትልቁ ጥያቄ ግን ከመካከላቸው ምን ያህሉ ዛሬ ድምጻቸውን ሰጥተዋል የሚለው ነው? ኢሳንድር አምራኒ በሃገራት መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች መፍትሄዎችን የሚያጠናው ክራይስስ ግሩፕ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባልደረባ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት ብዙ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ፍላጎት ማጣታቸው በመንግሥት እና በምክር ቤቱ ሥራ ተስፋ መቁረጣቸውን ያሳያል።
« ብዙ አልጀርያውያን ይህ ምርጫ ምንም ትርጉም የለውም ሊሉ ይችላሉ። ከምክር ቤቱ ምንም ተስፋ የሚያደርጉት ነገር የለም። በቡተፍሊካ የሥልጣን ዘመን ምርጫ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሰጣቸው ደረጃ መውረዱ በእርግጥ አስገራሚ ነው።»
ለ18 ዓመታት አልጀርያን የመሩት የ80 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቡተፍሊካ ባጋጠማቸው የአንጎል ውስጥ ደም መርጋት ከባድ የጤና ችግር ላይ ይገኛሉ። በዚህ የተነሳም ለዓመታት ለህዝብ ታይተው አያውቁም። ዛሬ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ድምጻቸውን ሲሰጡ ታይተዋል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በአልጀሪያ በትክክል ማን በበላይነት እንደሚመራ ብዙ ግምቶች መሰንዘራቸው አልቀረም። ፖለቲከኞች፣ ጦር ኃይሉ፣ የደህንነት መሥሪያ ቤት ተሰሚነት ያላቸው ባለሀብቶች እነዚህ ሁሉ በሀገሪቱ ኃይል ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ወደ ምርጫው ስንመለስ የቀድሞ ዲፕሎማት እና የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አብደላዚዝ ራሃቢ የከዚህ ቀደሙን የድምፅ አሰጣጥ ልምዳቸውን ለዶቼ ቬለ አካፍለዋል።
« ባለፈው ምርጫ ፣ በምርጫ ጣቢያየ ወደ 10 ሰዓት ላይ ድምጽ ሰጥቼ ነበር። በወቅቱም የመራጮች ተሳትፎ ምን እንደሚመስል ጠይቄ ነበር፤ የተነገረኝ እኔ በመረጥኩበት አካባቢ 8 በመቶ መሆኑ ነበር። ይሁን እና ማታ በይፋ የተነገረው 88 በመቶ ተብሎ ነበር። ከ10 እጥፍ በላይ ነው። እኔ የዜግነት ግዴታየን ተወጥቻለሁ። ግን እንደተሰረቅኩ ይሰማኛል።»
ከ5 ዓመት በፊት በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ድምፁን የሰጠው መምረጥ ከሚችለው 43 በመቶው መሆኑ ተነግሯል። ዛሬ ድምጽ የሰጠው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም። አንድ መምህር ለአንድ የአልጀሪያ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የምክር ቤት መቀመጫዎች ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ ብለዋል። ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የታሰሩት የገዥው የብሔራዊ ነፃነት ግንባር ዋና ፀሐፊ የተገኘባቸውን የመራጮች ስም ዝርዝር የያዘ ወረቀት እና ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደ አንድ ማስረጃ ይቀርባል። ብዙ አልጀርያውያን በተለይም ወጣቶች ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን ማዳበር እንጂ የህዝቡን ችግር ለማስወገድ ይሰራሉ ብለው አያስቡም። ምንም እንኳን የአልጀሪያ መንግሥት ከዛሬ 6 ዓመት በፊት በተካሄደው የአረቡ ዓለም ህዝባዊ አመጽ ማህበራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ከፍ ለማድረግ ቃል ቢገባም አሁን ዝቅ ለማድረግ ተገዷል። ይህ ደግሞ በአንዳንድ ቦታዎች አመጽ እያስነሳ ነው። በሌላ በኩል መንግሥት ከዚህ ቀደም ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የጠፋበትን ኢስላሚክ ሳልቬሽን ፍሮንት ከተባለው አክራሪ የፖለቲካ ፓርቲን ሲካሂድ የቆየውን ትግል ግን አሸንፏል። ይሁን እና ሀገሪቱ ተረጋግታ እንድትቀጥል ተቋማቷ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ።
የንስ ቦርሸርስ/ኂሩት መለሰ

Algerien Parlamentswahlen 04.05.2017
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Djarboub

ሸዋዬ ለገሠ