1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአል-ሸባብ ርምጃና ሶማሊያ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 4 2003

ከአዋጅ ባለፍ በጫት ነጋዴዎች ወይም ሸማቾች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርጎ አያዉቅም ነዉ።አሁን ግን ሸባቦች በጫት ላይ ጠጠር ብለዋል።በዚሕም ምክንያት፥-ሶማሊያዊዉ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንዳለዉ ሞቃዲሾ ዉስጥ ከትናንት ጀምሮ ጫት የለም።

https://p.dw.com/p/PeEv
የአል-ሸባብ ታጣቂዎችምስል AP

14 10 10

የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል ሸባብ ወደ ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾ ጫት እንዳይገባ አገደ።የቡድኑ ታጣቂዎች ከኬንያ ጫት የሚጓጓዝባቸዉ አነሰተኛ አዉሮፕላኖች የሚያርፉበትን የመስክ አዉሮፕላን ማረፊያ ወርረዉ ጫት የጫኑ አዉሮፕላኖች ከትናንት ጀምሮ እያንዳርፉ አግደዋል።ቡድኑ በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች የሚኖረዉ ሕዝብ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን እንዳይመለከበት ፥የምዕራባዉያን ፊልም እንዳያይና ሙዚቃ እንዳይሰማ አግዷል።የሞቃዲሾዉ የዶቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንደሚለዉ የአሸባብ እርምጃ የሕዝቡን ኑሮ እያወከ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።

አክራሪዊ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች ቡድኑ ጫት በአደባባይ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ በይፋ ካገደ ቆይቷል።ይሁንና ከአዋጅ ባለፍ በጫት ነጋዴዎች ወይም ሸማቾች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርጎ አያዉቅም ነዉ።አሁን ግን ሸባቦች በጫት ላይ ጠጠር ብለዋል።በዚሕም ምክንያት፥-ሶማሊያዊዉ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንዳለዉ ሞቃዲሾ ዉስጥ ከትናንት ጀምሮ ጫት የለም።

«ከሁለት ቀናት በፊት ነዉ-አዉሮፕላን ማረፊያዉን የወረሩት።በዚሕም ምክንያት ከትናንት ጀምሮ ጫት ነጋዴዎቹ በሚጠቀሙበት በዚያ አዉሮፕላን ማረፊያ በኩል ጫት አልገባም።እናም ሞቃዲሾ ዉስጥ ጫት የለም።(ሸባቦች) አዉሮፕላን ማረፊያዉን ባሁኑ ጊዜ የወረሩበት ምክንያት ግልፅ አይደለም።ባካባቢዉ የነበሩ የአዉሮፕላን ጣቢያዉ ሠራተኞች ጣቢያዉን እንዲዘጉ፥ ነጋዴዎቹም ጫት እንዳያስገቡ አዘዙ።»

ጫት፣- ለሚቅመዉ ለአብዛኛዉ ሶማሊያዊ እንደመዝናኛ፥ ከጓደኛ ዘመድ-ወዳጅ ጋር እንደመወያያ፥ እንደ ሥራ ማቀጃ-ማከናወኛም ይታያል።ይዘወተራልም።ለሚሸጥ-ለሚለዉጠዉ ደግሞ ጥሩ የገቢ ምንጭ ነዉ።, መተዳዳደሪያ።የአሁኑ አል-ስባብ እርምጃ ሙስጠፋ ሐጂ እንደሚለዉ የብዙ ሰዎችን ኑሮ ይጎዳል።

«እርምጃዉ በጫት ንግድ የሚተዳደሩ የበርካታ ሰዎችን ኑሮ ያናጋል።በተለይም ጫት በመሸጥ አነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩ የሞቃዲሾ ሴቶችን ሕይወት ክፉኛ ነዉ-የጎዳዉ።አል ሸባብ በሞቃዲሾ ዋና ዋና የገበያ ሥፍራዎች የሚገኙ የጫት መደብሮችን ከዘጋ ቆይቷል።ይሁንና ነጋዴዎቹ ከመሐል ከተማ ወጣ ብለዉ ጫት የሚሸጡበት ሥፍራ ከልሎላቸዉ ነበር።እና እስካሁን ጫት ንግድን በከፊል እንጂ ሙሉ በሙሉ አላገደም ነበር።»

አል-ሸባብ በሚቆጣጠረዉ አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን በቴሌቪዥን እንዳይመለከት፥የምዕራባዉያን ፊልምና ሙዝቃዎችን እንዳያይ ወይም እንዳያዳምጥ ሌላ ቀርቶ በተንቀሳቃሽ ሥልክ እንኳን ሙዚቃ እንዳያጫዉት ካገደ ቆይቷል።ሕዝቡ እንዲሕ አይነት እርምጃዎችን መቃወሙ አልቀረም።ለማስለወጥ ግን ሙስጠፋሐጂ እንደሚለዉ አቅም የለዉም።

«አሸባብ በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች የደነገጋቸዉን እንደነዚሕ አይነቶቹን ጥብቅ ደንቦች ሕዝቡ ይቃወማቸዋል።ችግሩ ግን አል-ሸባብ በጣም ሐይለኛና ሕዝቡን በጠመንጃ አፈሙዝ የሚገዛ ሐይል ነዉ።የአል-ሸባብ መሪዎች የሕዝቡን ፍላጎት አይጠይቁም።ሕግ ያዉጃሉ።ይሕን ሕግ የሚጥስ ማንኛዉም ሰዉ እጁ ወይም እግሩ ይቆረጣል፥ ይገደዳል ወይም ይታሰራል።»

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ