1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሚሶም ተልዕኮ ዉድቀት ወይስ ስኬት

እሑድ፣ ሰኔ 26 2008

ዘንድሮ ደግሞ ለጦሩ ከፍተኛዉን ወጪ የሚከፍለዉ የአዉሮጳ ሕብረት የበጀቱን ሐያ በመቶ እንደሚቀንስ አስታዉቋል።የአዉሮጳ ሕብረት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዩሮ ለአሚሶም ይከፍል ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት ዉሳኔን በመቃወም ይመስላል ለአሚሶም የመጀመሪያዉንና ከፍተኛዉን ወታደር ያዋጣችዉ ዩጋንዳ ጦሯን በ2017 ለማስወጣት ወስናለች።

https://p.dw.com/p/1JHcw
ምስል DW/E. Lubega

እንወያይ

በ2006 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሶማሊያ የዘመተዉ የኢትዮጵያ ጦር ያኔ የሶማሊያን አብዛኛ አካባቢ ይቆጣጠር የነበረዉን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን ማጥፋቱን ሲያዉጅ ሶማሊያ ከጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ መንግሥት መወገድ በኋላ አይታዉ የማታዉቀዉ ሠላምና መረጋጋት ሰፈነባት አሰኝቶ ነበር።

ግን ብዙ አልቆየም።ከሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ፍርስራሽ የወጣዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አ-ሸባብ አብዛኛ ሶማሊያን ባጭር ጊዜ መቆጣጠሩ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ኒዮርክ፤ ከዋሽግተን እስከ ብራስልስ የሚገኙ ፖለቲከኛ-ዲፕሎማቶችን ያራዉጥ ገባ።መፍትሔ የተባለዉ፤ በሶማሊያ የአፍሪቃ ሕብረት ተልዕኮ (AMISOM በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የተባለዉን ጦር ማዝመት ነዉ።

ዘመቻዉ አሸባብንና ተባባሪዎቹን ለመዉጋት በመሆኑ ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ጦር ማዝመት አልፈለጉም።የተቀሩትም ጦር ለማዝመት የገቡትን ቃል በማጠፋቸዉ ሐላፊነቱን መጀመሪያ ዩጋንዳ እና ቡሩንዲ፤ ዘግየት ብለዉ ደግሞ ኬንያ፤ ጅቡቲ (በመሐሉ ሴራሊዮ እስከ 2014 ድረስ) እና ኢትዮጵያ መሸከም ግድ ሆኖባቸዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የጦር አማካሪዎች፤ ስዉር ኮማንዶ ጦር እና ሰዉ አልባ አዉሮፕላን ድሮን የሚታገዘዉ የአሚሶም ጦር ከሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ጋር በመሆን ከ2007 ጀምሮ ከአሸባብ ጋር በገጠመዉ ዉጊያ በርካታ ትላልቅ ከተሞችን መማረክ ችሏል።ዉጊያዉ ግን አሁንም አልቆመሞ።ዘጠኝ ዓመት አለፈዉ።አሸባብ በሚያደርሰዉ ጥቃት፤ ትክክለኛዉ አሐዝ በይፋ ባይነገርም፤ ከ3000 በላይ የአሚሶም ወታደሮች መገደላቸዉ ይገመታል።

Uganda Ankunft von Särgen
ምስል DW/E. Lubega

ዘንድሮ ደግሞ ለጦሩ ከፍተኛዉን ወጪ የሚከፍለዉ የአዉሮጳ ሕብረት የበጀቱን ሐያ በመቶ እንደሚቀንስ አስታዉቋል።የአዉሮጳ ሕብረት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዩሮ ለአሚሶም ይከፍል ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት ዉሳኔን በመቃወም ይመስላል ለአሚሶም የመጀመሪያዉንና ከፍተኛዉን ወታደር ያዋጣችዉ ዩጋንዳ ጦሯን በ2017 ለማስወጣት ወስናለች።

22ሺ ከሚገመተዉ የአሚሶም ወታደርና ፖሊስ 6 ሺሕ አምስት መቶ ያሕሉ የዩጋንዳ ነዉ።የዘመቻዉ ዉጤት፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና የዩጋንዳ ዉሳኔ፤ የአካባቢዉ ሠላም እንዴትነት የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ሰወስት