1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማኑኤል በረከት ዜና ዕረፍት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16 2003

ይሕ ልሳን ተዘጋ።አማኑኤል በረከት ነገ-አይጠብቀንም፥ ትናንት እንጂ ዛሬም የለም።ከአርባ ዓመታት በላይ በተለያዩ ጣቢያዎች በራዲዮ ጋዜጠኝነት ያገለገለዉ በጣሙን በስፖርት ጋዜጠኝነኝ እዉቅናን ያተረፈዉ አማኑኤል በረከት በቃ።አረፈ።ስልሳ ዘጠኝ አመቱ ነበር።ማንተጋፍቶት ስለሺ አጭር ዘገባ አለዉ።

https://p.dw.com/p/RPoY
ጋዜጠኛ አማኑኤል በረከትምስል DW

የዶቼቬሌ ሬዲዮ የረዥም ጊዜ ተከታታዮች በተለይ በስፖርት አዘጋጅነቱ ያስታውሱታል። አንጋፋው ጋዜጠኛ አማኑኤል በረከት። ዜና-ረፍቱ ሲሰማ ያልደነገጠ እጅግ አብዝቶም ያላዘነ አልነበረም። የረዥም ጊዜ የስራ ባልደረባው ተክሌ የኋላ። ጋዜጠኛ አማኑኤል በረከት ከአማርኛው ክፍልም አልፎ በዶቼቬሌ ሬዲዮ ጣቢያ ሌሎች ክፍልም ሲበዛ የሚታወስ ነው። በዶቼቬሌ ሬዲዮ የኪስዋሂሊ ክፍል ሃላፊና ከ10 ዓመታት በላይ አማኑኤልን የሚያውቁት አንድሪያ ሽሚት «አማኑኤልን በሙያው በኩልም ሆነ በግል ህይወቱ የምናውቀው የኪስዋሂሊ ክፍል ባልደረቦች በአጠቃላይ፤ ጡረታ ከወጣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ማረፉን ስንሰማ እጅግ በጣም ነው የደነገጥነው። ሁላችንም እጅግ ሲበዛ አዝነናል» ገና ከወጣትነት ዘመን አንስቶ ወዳጁ ነበር። በብስራተ-ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ በኋላም በዶቼቬሌ የስራ ባልደረባው አቶ ንጉሴ መንገሻ፤ ዜና ረፍቱን ሲሰማ ማመን ነው የተሳነው። የጋዜጠኛ አማኑኤል በረከትን ገራገርነትና ለጋስነት ሁሉም ይስማሙበታል። «አማኑኤል በረከት ፈፅሞ ልዩ ሰው ነበር። በጣም ተወዳጅ፣ ሁሌም ሰዎችን ለመርዳት የተዘጋጀ፣ አንድም ጊዜ ሰዎችን ተቆጥቶ የማያውቅ ሰው ነበር። አማኑኤል ድንቅ ጋዜጠኛም ነበር። የአማርኛውን ክፍል በጥሩ ሁኔታ ለረዥም ዓመታት እንደመራ እርግጠኛ ነኝ። ክፍሉን በትክክለኛው መንገድ ከመምራቱም ባሻገር በአማኑኤል በረከት የረዥም ግዜ አስተዳደር ክፍሉ ተጠቃሚ ሆኗል» አንጋፋው ጋዜጠኛ አማኑኤል በረከት የአንዲት ሴት ልጅና የሁለት ልጆች አያት ነበር። ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ነው ያረፈው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ