1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሆነዋል።

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት የካቢኔ አባላትን ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አድርጎ ሾሟል። ሹመቱ ግን ዝም ብሎ ሹመት አይመስልም። የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃ በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች የአምባሳደርነት ሹመቱ "ሰዎች ከመሐል ፖለቲካው ዘወር እንዲሉ የሚደረግበት" ሥልት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/2hGt0
Äthiopien Addis Abeba Vereidigung Kabinett
ምስል Imago/Xinhua

MMT Ethiopia appointed senior officials as ambassadors - MP3-Stereo

ኢትዮጵያ ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መገዛት ከጀመረች በአስረኛ ወሯ ከጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔ ሁለት ሰው ጎደለ።  የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሣ ተክለ ብርሃንና እና የትምህርት ሚኒሥትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የጠቅላይ ሚኒሥትሩ ካቢኔ በተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ ከዘጠኝ ወራት በኋላ በአምባሳደርነት የተሸኙ ናቸው። የሆርን አፌርስ ድረ-ገጽ መስራቹ ዳንኤል ብርሃነ እንደሚለው እርምጃው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቡድኖች አንዳቸው በሌላቸው ላይ የበላይነት ለመውሰድ ያደረጉት ሳይሆን አይቀርም ባይነው። ''ዋና አላማው ሶስት እና አራት ሰዎች ሹመት ነው። የቀረው ሌላው ሹመት ግን ማደናገሪያ ነው'' የሚለው ዳንኤል አምስት ስድስት ዲፕሎማቶችን አብረው ሲሾሙ ነገሩን "የተለመደ" ለማስመሰል ያደረጉት ነው ብሎ ያምናል።

''ከላይ ያሉትን ስሶት አራት ሰዎች ስታይ ነገሩ ሌላ ነገር እንዳለ ታያለህ። በትክክል የትኛው ወገን እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም አንድ ኃይል ለማረጋገጥ እየሞከረ ያለ ይመስለኛል። አንድ ወጥ የሆነ ሰልፍ ለመምፍጠር እየተሞከረ ያለ ይመስለኛል። እስካሁን አራት አምስት ቡድን በአንድ ላይ ታጭቆ ነበረ። ስራ አይሰራም። እርስ በርስ ይጠባበቃል፤ከመካከል የሰለቸው አለ። ያው ዞሮ ዞሮ አንድ ቡድን ነው ለመጠቅለል እየሞከረ ያለ የሚመስለው። ማን እንደሆነ ምንም ግልፅ ባይሆንም።"

Professor Beyene Petros derzeitiger Vorsitzender des Oppositionsbündnisses Medrek
ምስል DW

በተቃዋሚዎች እና ተቺዎች ገለልተኝነቱ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢው የፕሮፌሰር መርጋ በቃና እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ "ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር" ተብለው ከተሾሙት መካከል ይገኙበታል። የመድረክ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግን ሹመቶቹን አምርረው ይተቻሉ።

"የመጦሪያ ምደባ፤ሹመት ነው። ይቺን ምርጫ እንኳ በብቃት፤በፍትኃዊነት ማካሔድ ያልቻሉትንም ግለሰቦች ወስዶ ደግሞ አሁን አንዱ ጋ አምባሳደር ይባላል። ይኼ ምንድነው? በብቃት ነው? ሙያና ባለሙያን ማገናኘታቸው ነው?  

የሹም ሽር ዜናው የተሰማው መንግሥት በቅርቡ የጣለዉ የግምት ግብር ሌላ ተቃዉሞ በቀሰቀሰ ማግሥት ነው። የግብሩ ተቃዉሞ እልባት ሳያገኝ የሐገሪቱ መንግስት «በሙስና» የሚጠረጠሩ ያላቸዉን ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተሰምቷል። የኩነቶቹ መደራረብ በገዢው ግንባር አገር የመምራት ብቃት ላይ ጥያቄ ያጭራል? ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ አርጋው አሽኔ ኢሕአዴግ "ግር" ሳይለው አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለው።

"ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ገዢው ፓርቲ አንደኛ በራሱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን መፍታት አልቻለም። ሁለተኛው ነገር ደግሞ ከሕዝቡ የተነሳው ቁጣ እየጨመረ፤በተለይ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችልበት ደረጃ እየተመናመነ በመምጣቱ እነዚህን ሁለት ትልልቅ ፈተናዎች እንዲጋፈጥ ሆኗል። ስለዚህ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ የአጭር ጊዜ ማስመሰያ አንዳንዶቹም ደግሞ ለችግሮቹ መፍትሔ ያልሆኑ የማስመሰያ መፍትሔዎችን በመውሰድ ለውጥ እያደረገ መሆኑን ወይም ደግሞ ከሕዝብ በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ የመፍትሔ ኃሳቦች እየመጡ መሆኑን እና እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ለማሳየት ነው እየተሞከረ ያለው።"

Äthiopien Neubildung Kabinett
ምስል DW/Y. Gebergziabeher

በኢትዮጵያ ፖለቲካ አምባሳደርነት ሹመት እንዳልሆነ የሚናገረው አርጋው አሽኔ "ሰዎች ከመሐል ፖለቲካው ዘወር እንዲሉ የሚደረግበት" ሥልት ነው ባይ ነው። ከትናንትናው ሹመት በስተጀርባ ከአዲስ አበባ ርቀው እንዲጓዙ የተወሰነባቸው ስለመኖራቸው የሚያውቀው ገዢው ግንባር ብቻ ነው።

ትንታኔዎቻቸው ይለያዩ እንጂ አርጋው አሽኔም ይሁን ዳንኤል ብርሃነ በገዢው ግንባር ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች በመኖራቸው ይስማማሉ። ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሥትር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ አሸናፊ የሆኖ የወጣ ወገን እንዳልነበር የሚናገረው ዳንኤል የሰሞኑ ኩነቶች መንግሥት በመጪዎቹ ቀናት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ግልፅ ይሆናሉ የሚል እምነት አለው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ