1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምነስቲ ወቀሳ እና የናይጄሪያ ምላሽ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2006

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት -አምነስቲ ኢንተርናሽናል የናይጀሪያ ጦር የሰብዓዊ መብት ረገጣ ፈፅሞዋል ሲል ወቀሳ ሰንዝሯል። ይህንን ወቀሳ የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዝም ብሎ አላለፈውም።

https://p.dw.com/p/1Cq29
Nigeria Soldaten
ምስል AFP/Getty Images

በአምነስቲ ዘገባ መሠረት፣ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ በመንግሥቱ ጦር እና በቦኮ ሀራም መካከል በተካሄደው ግጭት ከ4,000 የሚበልጥ ሰው ተገድሎዋል። የመንግስት ወታደሮች ቦኮሃራምን በማጥፋት ዘመቻ ያለፍርድ ሂደት ከስድስት መቶ ሰዎች በላይ መረሸናቸዉ ተገልጿል።

እሥላማዊው ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሀራም በሚሰነዝረዉ ጥቃት በየሳምንቱ በሰሜን ናይጄሪያ ሰዎች ይሞታሉ። ሰሞኑን ግን ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት-አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰነዘረዉ ከባድ ወቀሳ ቡድኑን ሳይሆን እሱን ለማዳከም የሚንቀሳቀሰውን የናይጄሪያ የመከላከያ ኃይል ይመለከታል። እንደ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ዘገባ ከሆነ የናይጄሪያ ጦር በሀገሪቱ ለሚፈፀሙ የጦር ወንጀልዎች ተጠያቂ ነው።ድርጅቱ እዚህ ወቀሳ ላይ የደረሰው በተለይ በአንድ ቪዲዮ ላይ ተመርኩዞ ነው። ተንቀሳቃሽ ምስሉ «የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ታጋጆችን በቢለዋ አንገታቸውን እየቆረጡ በጅምላ ወደ ጉድጓድ ሲወረውሩ ያሳያል። በዚህ መንገድ 14 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት ደግሞ ተተኩሶባቸው ተገድለዋል »ይላል አምነስቲ። የድርጅቱ የናይጄሪያ ተጠሪ ማክሚድ ካማራ ይህን መረጃ በደንብ የተጠና ስለመሆኑ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።«መረጃዎቹን የዐይን እማኞች በማነጋገር አጣርተናል። ከጦር ሠራዊት ዉስጥ ማንነታቸዉ እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሰዎችም ወታደሮቹ የተዉጣጡበትን ክፍል እና ዘርፍ አረጋግጠዉልናል። »ይላሉ ካማራ።

Nigerianischer Militärsprecher Chris Olukolade
የናይጄሪያ ጦር ቃል አቀባይ ክሪስ ኦሉኮላደምስል DW/A. Kriesch

ይሁንና ይህን ፈፀሙ ተባዮቹ ቦርኖ የተመደቡ የ81ኛው ክፍለ ጦር አባላት ናቸው። አምነስቲ ተፈፀመ የሚለው ግድያ ደግሞ የተካሄደው ማይድጉሪ ክፍለ ከተማ አካባቢ የምትገኘው ጊዳሪ በተባለች ስፍራ ነው። ይህ በሆነበት ዕለት ማለትም መጋቢት 5 ቀን ደግሞ ቦኮ ሀራም አንድ የጦር ካምፕ ሰርጎ ገብቶ በመቶ የሚቆጠሩ ታጋቾችን አስለቅቋል። ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ይህ ሲሆን ወታደሮች 600 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለው ወደፍርድ ሳያደርሱ ገድለዋል። በናይጄሪያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ወቀሳ ሲቀርብም የአምነስቲ የመጀመሪያው አይደለም። ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የመከላከያ ሠራዊቱ አብሮ ተጠያቂ እንደሆነ ያመለክታሉ። የናይጄሪያ ጦር ግን የአምነስቲን ወቀሳ ጨምሮ ሌሎች ወቀሳዎችን ሁሉ እንዳጣጣለ ነው። ነገር ግን ይህን ጉዳይ እንደሚያጣራ አመልክቶዋል። የጦሩ ቃል አቀባይ ክሪስ ኦሉኮላደ ለወቀሳው ምላሻቸዉን እንዲህ ይገልፃሉ። «በርግጥ የሚያሳዝን ነው። ነገር ግን ከግባችን የሚያደናቅፈን አይሆንም። ጦሩ ለሀገሩና እና ለሕዝቡ ኃላፊነት አለበት። ከውጭ የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን በሁለተኛ ደረጃ ነው የምናያቸዉ። በቅርቡም ሆነ ዘግይቶ ጦሩ ተልዕኮዉን ሲያጠናቅቅ እውነታው ይወጣል።»

ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ በሰሜን ናይጄሪያ ከተሞች ቦርኖ፣ ዮቤ እና አዳማዋ ፍፁም መረጋጋት የለም። በዚያው በግንቦት ወር የናይጄሪያ ጦር አዲስ የመከላከያ ርምጃ በቦኮ ሀራም ላይ ወስዶ ተግባራዊ ማድረጉን ገልፆም ነበር። ስለሆነም ይላሉ ኦሉኮላደ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በህገ ወጥ መንገድ የተጨመሩት ግብሮች እንዲስተካከሉ የጦሩ ርምጃ ሚና ተጫውቷል። በዚህ የአምነስቲ ድርጅት የናይጄሪያ ተጠሪ ካማራ በፍፁም አይስማሙም።«በፍፁም፤ በሰብዓዊ መብት ይዞታዉ ላይም ይሁን የህዝቡን ደህንነትን በማስከበሩ ረገድ በቦርኖ፣ ዮቤ እና አዳማዋ የአደጋ ጊዜ ጥሪ ከተደረገ በኃላ እንኳን ምንም መሻሻል አላየንም። ይልቁንም በሁለቱም በቦኮ ሀራም ተዋጊዎችም በኩል ቢሆን ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የኃይል ርምጃዎች መጨራቸውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መበራከታቸዉን አይተናል። »

ምንም እንኳን ይህ ቦኮ ሀራም የሚፈጽመዉን ወንጀል ትክክል ባያደርገውም የናይጄሪያ የመከላከያ ኃይል ቦኮ ሀራምን ለማዳከም በሚወሰደዉ ርምጃ የዓለም አቀፍን ሕግ ተከትሎ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት ካማራ አክለው ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ አምነስቲ ያነሳውን ወቀሳ አስመልክቶ የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስቴርም ጉዳዩን እንደሚያጣራ ቢያስታውቅም፤ ኃላፊነቱ ለጦሩ ብቻ ሳይተው ሌላ ገለልተኛ ቡድን ጉዳዩን ማጣራት እንዳለበት አሳስበዋል።

Karte Nigeria

ፊሊፕ ሳንደር / ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ