1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአረብ ቱጃሮች ጠብ

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 2009

አራቱ መንግሥታት በቀጠር ላይ ለማደማቸዉ የሰጡት ምክንያት የዶሐ ገዢዎች አሸባሪዎችን ይደግፋሉ፤ ከኢራን ጋር ይተባበራሉ የሚል ነዉ።የመገናኛ ዘዴ ዘገባ፤ መግለጫ፤ የኢሜል ጠለፋ የሚል «ማድመቂያ» ተደብሎበታልም።ቀጠር ዉንጀላዉን መሠረተ-ቢስ ብላዋለች።

https://p.dw.com/p/2eD1O
Riad Treffen Donald Trump Tamim Bin Hamad Al-Thani Emir Katar
ምስል Getty Images/AFP/M. Ngan

Qatar - MP3-Stereo

              

የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ መንግሥታት  የገጠሙትን የዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ ለማስወገድ የተለያዩ መንግሥታት ሽምግልና ለመግባት ፈቀደኛ መሆናቸዉን እየገለፁ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ፤ ባሕሬን፤የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ግብፅ ከቀጠር ጋር ያላቸዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጠዋል።የቀጠር አየር መንገዶች አዉሮፕላኖች ወደየሐገሮቻቸዉ እንዳይበሩ አግደዋል።የአረቦቹን ጠብ ለማስወገድ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ፈረንሳይና ሱዳን ሽምግልና ለመግባት ፈቃደኛ መሆናቸዉን ሲያስታዉቁ፤ የኩዌቱ አሚር የሳዑዲ አረቢያ ንጉስን ለማነጋገር ዛሬ ወደ ሪያድ በርረዋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

የቀጠር አሚሮች የትንሽ ልሳነ-ምድራቸዉን «ብጣቂነት» በገንዘብ ጉልበት ለመሸፈን ከጋስ ሽያጭ የሚዝቁትን ዶላር ይረጩታል።አሜሪካኖች ኢራቅን መዉረር ሲፈልጉ ጦር ሠፈር አሠርተዉ ሰጡ።ፈረንሳይ-ብሪታንያና አሜሪካኖች ቃዛፊን የማስገደል ዕቅዳቸዉን በአረቦች ትብብር ለመሸፈን ሲሹ ዶሐዎች ከሪያዶች ቀድመዉ «አለሁ» አሉ።
ሊባኖሶችን በማስታረቅ ሰበብ ሥም-ዝና ሲከጅሉ ቤይሩት ላይ ጠንካራ ጡንቻቸዉን ያሳርፉ ለነበሩት ለሶሪያዉ መሪ ልዩ አዉሮፕላን ሸለሙ።የዶኻዎችን «አለሁ አለሁ» ማለት ሪያዶች አይወዱትም።የሪያዶች ቅሬታ ገደፉን ለቅቆ እንዳይፈስ ግን ዶሐዎች አንዳዴ ትልቅ ጎረቤቶቻቸዉን ተከትለዉ «ዉን ዉን» ማለታቸዉ አልቀረም።
ሳዑዲዎች  ደማስቆዎችን ሲያስወጉ ቀጠሮች ወዳጅነታቸዉን ሰርዘዉ የበሽር አል-አሰድ ጠላት ሆኑ።ሳዑዲዎች የመንን ሲወጉም አልቀሩም።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሪያድን ከጎበኙ ወዲሕ ግን የሪያድ ዶኻዎች «እያረሩ መሳቅ» አይነት ግንኙነት መሸፈኛዉን ጥሶ ወጣ።
                            
«የሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ ምንጭ እንዳስታወቀዉ፤ የሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዊ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕግ በተደነገገዉ መሠረት የሐገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፤ ብሔራዊ ደህንነትን ከአሸባሪነትና ከፅንፈኝነት ለመከላከል ከቀጠር ጋር ያለዉ ዲፕሎማሲያዊና ቆንስላዊ ግንኙነት  እንዲቋረጥ ወስኗል።በተጨማሪም ከቀጠር ጋር የምድር፤የባሕርና የአየር ግንኙነት እንዳይደረግ፤ በሳዑዲ አረቢያ የአየርና የባሕር ክልል ምንም  ነገር እንዳይተላለፍ ታግዷል።»
የሪያዶች ዉሳኔ ቀጠሮችን ከመቅጣት ይልቅ እራሳቸዉን «ትንሽ» እንደማድረግ ነዉ የተቆጠረዉ። ባሕሬን ግን ተከተለች።ዓረብ በሕዝባዊ አመፅ በሚናጥበት ወቅት ዙፋናቸዉ በሳዑዲ አረቢያ ታንክ የዳነላቸዉ ንጉስ ሐማድ ቢን ኢሳ አል ኸሊፋ ከንጉስ ሠልማን ቃል ሊወጡ አይችሉም።የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አሰለሰች።
የሁስኒ ሙባረክ ግብፆች ዶሐዎችን «ቅልብልብ» ነበር-የሚሏቸዉ።ሙባረክ ሲወገዱ ሙርሲን ደገፉ።ሙርሲ ሲወገዱ አልሲሲ ጠመዷቸዉ።በትረ-ሥልጣናቸዉ በሳዑዲ አረቢያ ዶላር የሚጠበቀዉ ጄኔራል ሌላ ሊሉ አይችሉም።ግን ቀጠር የሚሰሩ የ3 መቶ ሺሕ ግብፃዉያን ዕጣ-ፈንታ በዶኻዎች እጅ ነዉ።

Katar Doha Beamte Verteidigungsministerium
ምስል Getty Images/J. Ernst

አራቱ መንግሥታት በቀጠር ላይ ለማደማቸዉ የሰጡት ምክንያት የዶሐ ገዢዎች አሸባሪዎችን ይደግፋሉ፤ ከኢራን ጋር ይተባበራሉ የሚል ነዉ።የመገናኛ ዘዴ ዘገባ፤ መግለጫ፤ የኢሜል ጠለፋ የሚል «ማድመቂያ» ተደብሎበታልም።ቀጠር ዉንጀላዉን መሠረተ-ቢስ ብላዋለች።አረቦችን ለመሸምገል ከደከማዋ ሱዳን እስከ ልዕለ ኃያልዋ አሜሪካ፤ ከአረብዋ ኩዌት እስከ አዉሮጳዊቱ ፈረንሳይ ሰልፍ ይዘዋል።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲልርሰን።
                             
«ተቀናቃኝ ወገኖች ልዩነታቸዉን በድርድር እንዲፈቱ እናበረታታለን።ችግሮቹን ለማስወገድ እኛ የምናደርገዉ አስተዋፅኦ ካለ (ዝግጁ ነን)የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ምክር ቤት (GCC) አንድነት መጠበቅ አለበት ብለን እናምናለን።»
የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር «እንሸምግል» ማለታቸዉ እንደተሰማ፤ የተነበበዉ የፕሬዝደንታቸዉ መልዕክት ግን ጠቡን የሚያቀጣጥል አይነት ነዉ።«በቅርቡ ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ በተጓዝኩበት ወቅት» ፃፉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቲዊተር ገፃቸዉ ዛሬ « ፅንፈኛ አስተሳሰብን ገንዘብ መርዳት የለባችሁም አልኩ።መሪዎቹ ቀጠር ላይ ጠቆሙ-ተመልከቱ።» አሉ የታላቂቱ ሐገር ታላቅ መሪ።የእብድ ገላጋይ እንዲሉ።እስካሁን ሽምግልና የጀመሩት ግን የኩዊቱ አሚር ናቸዉ።ሼክ ሳባሕ አል አሕመድ አ ሳባሕ ወደ ሪያድ በርረዋል። 
ቀጠር፤ እስራኤልና ምዕራባዉያን አሸባሪ የሚሉትን የፍልስጤም ነፃነት ድርጅት ሐማስንም፤ የማሕሙድ አባስን መስተዳድርንም እኩል ትረዳለች።እስራል ትጠላታለች።አሜሪካ ትገላምጣታለች።አረቦች ይናደዱባታል።ግን አይጨክኑባትም።ሐብቷ።

Katar nach dem Boykott
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Mizban

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ