1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸደቀ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 10 2009

በኢትዮጵያ በቅርቡ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ዛሬ ጸደቀ። 7 አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞ መጽደቁም ተገልጧል። ፕሪቶሪያ የሚገኘው የጸጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ ያኪ ሲልየር፦ መርማሪ ቡድኑ «ነፃ እና ገለልተኛ ሊሆን ይገባል» ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2RUqk
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Ethiopian parlament aproves the state of emergency - MP3-Stereo

በኢትዮጵያ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት  የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቶ በመቶ የገዢው ፓርቲ እና ደጋፊዎቹን ባሰባሰበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጽደቁ ተገልጧል።  ምክር ቤቱ ሰባት አባላትን ያካተተ መርማሪ ቦርድ መርጦ ሥልጣናቸውን ማጽደቁንም አስታውቋል። ከመርማሪ ቦርድ አባላቱ መካከል አራቱ የምክር ቤት አባል ሲሆኑ፤ ሦስቱ ዳኞች መሆናቸው ተገልጧል። ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ የሚገኘው የጸጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ  ያኪ ሲልየር፦ መንግሥት ነፃ እና ገለልተኛ ሰዎችን  በመርማሪ ቦርድ ውስጥ ማካተት አለበት ይላሉ። 

«ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም አብዛኛው የምክር ቤት አባል የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው። ዳኞችም ቢሆኑ የሚሾሙት በመንግሥት ነው። እናም የኢትዮጵያ መንግሥት በእርግጥም ጉዳዮን በገለልተኛ ቡድን ማጣራት ከፈለገ ከሲቪል ማኅበረሰቡ አልያም ከምሁራን መካከል ማካተት አለበት። በእርግጥ እነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ናቸው።ግን በውጪ ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። ከነዚህ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች መካከል ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑትን በመርማሪ ቡድኑ ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል።»

ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመርማሪ ቦርዱ አባልነት የተመረጡት 4ቱ የምክር ቤት አባል ሲሆኑ፤ ሦስቱ የሕግ ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጧል። ያኪ ሲልየር እንደሚሉት አዋጁም ኾነ ቦርዱ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብረድ መጥቀሙ አጠራጣሪ ነው። 

Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

«ከግጭቱ በስተጀርባ ያለው ነጥብ በእርግጥ የሚያመለክተው ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዋነኞቹ ብሄሮች የመገለል ስሜት መኖሩን ነው። እናም ይኽ ጉዳይ መልስ ካላገኘ የተሰየመው የመርማሪ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር በእርግጥ ለመቃኘት እና መልስ ለመስጠት ይችላል ብሎ መመልከት በእውነቱ ይከብዳል።»

ያኪ ሲልየር ኅብረተሰቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች እና የቅያሜውን ሰበብ መርማሪ ቡድኑ በገለልተኝነት ማጣራት መቻል አለበት ብለዋል። ዘላቂ መፍትኄ ከተፈለገ ደግሞ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ ያስፈልጋል ይላሉ። 

«ኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት የምትሻ ከሆነ በዝግታ ሆኖም ያለምንም ማወላወል የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ምኅዳሩን መክፈት አለባት። የኅብረተሰቡ ሌሎች አካላትንም ማሳተፍ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ግን በሀገሪቱ ወደፊት ግጭቱ ሊጠናከር ምናልባትም መረጋጋት የሌለበት ማፃዔ ጊዜ ሊያስከትል ይችላል።»

መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም በመላው ሀገሪቱ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥልጣን የሰጠው የኮማንድ ፖስት ወይንም የእዝ ጣቢያ ባለፉት ጥቂት ቀናት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጧል። የዓለም አቀፍ  ጸጥታ ጥናት ተቋም ተንታኙ ያኪ ሲልየር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አሳሳቢ ብለውታል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ