1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ሥጋት-ሶማሊያ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13 2008

ከዕለተ-እሁድ ጀምሮ የሶማሊያ ጦር ጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን አሸባብ እና በአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ስር የሚገኙት የኬንያ ወታደሮች አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን እየተናገሩ ነው። በዛሬው ዕለት 65 የጽንፈኛ ቡድኑ የደፈጣ ተዋጊዎች በሶማሊያ ጦር መገደላቸውን አዣንስ ፍራን ፕሬስ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1IHjQ
ምስል Reuters/M. Dalder

[No title]

ስምንተኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ከነሐሴ 27-ጳጉሜ 1/2005 ዓ.ም.በሞቅዲሹ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንቶቻቸውን፤የአፍሪቃ ሕብረት እና ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ሰብስበው አንድ እቅድ ይፋ አደረጉ። ለአገራቸው እና ለመንግስታቸው የሰነቁትን ውጥን በጉባዔው መገባደጃ ይፋ ያደረጉበትንም ሰነድ 'ርዕይ 2016' ሲሉ ሰየሙት። በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2016 ዓ.ም. በአገሪቱ ሊካሄድ ከታቀደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስያሜውን የተዋሰው ሰነድ ይፋ የተደረገበት ጊዜ አክራሪው የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የተዳከመበት ማዕከላዊ መንግስቱ የመጠናከር ተስፋ ያሳየበት ነበር። የፀጥታ ጥናት የተሰኘዉ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት ግን ከሶስት አመት በፊት የተነደፈውን እቅድ ተግባራዊነት የሚገዳደሩ በርካታ ቅራኔዎች በሶማሊያ ዛሬም አሉ።

ይህ ርዕይ «ጠንካራ የሆነ፤ሁሉንም የሚያካት፣አሳታፊ የሆነ ህገ-መንግስት ማርቀቅ እና ማጽደቅ፤ ጠንካራ የሆነ ማዕከላዊነት ላይ ያላተኮረ ለተለያዩ የሶማሊያ ክልሎች ስልጣን የሚሰጥ ፌዴራል መዋቅርን ማስፈን፤ጠንካራ የሆኑ የአስተዳደር፣የፍትሕ የአገልግሎት ተቋማትን ማጠናከር እና ነሐሴ ላይ (2016 ዓ.ም.) ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የማካሄድ» እቅድ እንዳለው አቶ ሐሌሉያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እቅድ ግን በርካታ እንቅፋቶች ተደቅነውበታል።

Karte Somalia: Politische Aufteilung DEU

«በፓርላማው ውስጥ በፕሬዝዳንቱ እና በተወሰኑ የፓርላማ አባላት መካከል መሰረታዊ ቅራኔዎች» መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ሐሌሉያ እንደ ፑንት ላንድን የመሰሉ ጠንካራ የራስ አስተዳደር ያላቸው ግዛቶች በመጪው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሰራር እና አካሄድ በተመለከተ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ቁርሾ ውስጥ መግባታቸው ሌላኛው ሥጋት መሆኑን አስረድተዋል።

የአሸባብ ታጣቂዎች ከሞቅዲሹ በ40 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኘው የላንታ ቡሮ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት በፈጸሙ ማግስት ዛሬ የአገሪቱ ጦር 65 የጽንፈኛው ታጣቂዎችን ገደልኩ ማለቱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። በትናንትናው ዕለት የአሸባብ ታጣቂዎች በጦር ሰፈሩ የነበሩ 73 የሶማሊያ መንግስት ወታደሮችን መግደላቸውን ለጽንፈኛ ቡድኑ ቅርበት ያለው አናዱሉ ራዲዮ ዘግቧል። በዕለተ እሁድ የኬንያ ወታደሮች ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ውጊያ 34 መግደላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቦ ነበር። «አሸባብ ለሶማሊያም ይሁን ለቀጣናው አገራት ትልቅ የደህንነት እና የሰላም ስጋት» ሆኖ ቀጥሏል የሚሉት የጸጥታ ተንታኙ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ በአገሪቱ በሚታየው ድርቅ እና ድህነት የሚፈተኑት እና የትምህርት እድል፤ስራ እና ተስፋ ያጡ ወጣቶች የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን የመቀላቀል እድላቸውን እንደሚያሰፋው አስረድተዋል።

Anschlag Mogadishu Somalien
ምስል picture-alliance/dpa/S. Y. Warsame

አቶ ሐሌሉያ ሉሌ 22,000 ወታደሮች ያሉት የአፍሪቃ የሰላም አስከባሪ ጦር የሶማሊያ ተልዕኮ የበጀት እና ደሞዝ በተገቢው ጊዜ የመክፈል ችግር እንዳለበት ተናግረዋል። ከምዕራባውያን የሚደረገው ድጋፍ «በጣም የተጋነነ አይደለም» ያሉት የጸጥታ ተንታኙ የሚገኘው የገንብ ድጋፍም ቢሆን «ለሚገባው ዓላማ በሚገባው ሁኔታ ይውላል ወይ? የሚለው ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ» መሆኑንም ተናግረዋል። አሸባብ ከ60 በላይ የቡሩንዲ እንዲሁም ከ100 በላይ የኬንያ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በመግደል እና የአህጉራዊውን ሰላም አስከባሪ ጦር ሰፈር በመቆጣጠር በተልዕኮው ላይ ስነ-ልቦናዊ እና ሥልታዊ የበላይነት አግኝቶ ነበር። የሥነ-ልቦና የበላይነቱን ለመመለስ የአጸፋ እርምጃዎች መወሰዳቸው አልቀረም። አቶ ሐሌሉያ በአገሪቱ የሚታዩት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሁኔታዎች ለአሸባብ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ