1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ተከታይ ጥቃት በኬንያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 23 2007

የሶማልያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የአሸባብ ታጣቂዎች ኬንያ ዉስጥ 36 ድንጋይ አዉጪዎችን ገደሉ። ታጣቂዎቹ በሰሜናዊ ምስራቅ ኬንያ ማንዴራ ከተማ አጠገብ ዛሬ ሲነጋጋ በከፈቱት ጥቃት የገደሏቸዉ አብዛኞቹ ሰዎች የቀን ሰራተኞች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/1DyHE
Kenia Massaker in Mandera 2. Dezember 2014
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/STR

ታጣቂዎቹ አንዳንዶቹን ሰዎች የገደሉት በጥይት ብቻ ሳይሆን አንገታቸዉን እየቀሉ መሆኑን የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ ዘግቦአል።በጥቃቱ ሰበብ የኬንያዉ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትር እና የፖሊስ ዋና አዛዥ ከሃላፊነታቸዉን ተስተዋል።

ተጠርጣሪ የአሸባብ ታጣቂዎች በሶማልያ አዋሳኝ በሆነዉ ማንዴራ ከተማ ላይ ዛሬ ማለዳ የቀን ሰራተኞች ተኝተዉበት በነበረዉ ድንኳን ዉስጥ ዘልቆ በመግባት ነዉ በጥይት እና አንገልት በመቅላት የገደሉዋቸዉ። እንደ ፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ዘገባ ፕሪስ ታጣቂዎቹ ግድያዉን የፈፀሙት ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን እየመረጡ ነዉ። ይህ ዛሬ 36 ሰዎች የተገደሉበት ኬንያ ማንዴራ ከተማ ላይ የተጣለዉ ጥቃት የተከሰተዉ፤ ታጣቂዎች ኬንያ ዉስጥ ይጓዝ የነበረ አዉቶቡስን አስቁመዉ 28 ሰዎችን መርጠዉ ከገደሉና አሸባብ ለጥቃቱ ኋላፊነቱን ከወሰደ ከአንድ ሳምንት በኋላ መሆኑ ነዉ። የኬንያ መንግሥት የሰርጎገብ ጥቃት ችግር እየገጠመዉ ይሆን? በአፍሪቃ ስለሚታዉ የሽብር ጥቃት ጉዳይ ትንታኔ የሚሰጡት፤ በለንደን የደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጃስፐር ኩለን እንደሚሉት የኬንያ መንግሥት ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር ጠንካራ እጅ አለዉ፤ እንዲያም ሆኖ ጥቃቱ የደረሰዉ ሶማልያ ድንበር ላይ ነዉ፤
« እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የሚታየዉ በሶማልያ ድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ነዉ። በስፍራው በቂ የጥበቃ ኃይላት የሉም፤ ከዚህ ቀደም በናይሮቢ፤ ሞምባሳ ባህር ዳርቻ ለወራቶች ጥቃት አልደረሰም። ይህ የሚያሳየዉ የኬንያ ባለስልጣናት የተሻለ ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸዉ እና ጥቃት እንዳይደርስ መከላከላቸዉን ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ባለስልጣናቱ ከዩኤስ አሜሪካ ከብሪታንያ እንዲሁም ከእስራኤል ጦር ኃይላት ጋር የተሻለ ግንኙነት መፍጠራቸዉን ነዉ የሚያሳየዉ»

በሌላ ተመሳሳይ ጥቃት በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ በሶማልያ ድንበር አቅራብያ የምትገኘዉ ዋጂር ከተማ አንድ ታጣቂ በአንድ ቡና ቤት ላይ ባደረሰዉ ጥቃት አንድ ሰዉን ገድሎ 12 ሰዎችን ማቁሰሉ ተዘግቦአል። በኬንያ እየደረሰ ያለዉን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትሩ እና የሀገሪቱ የፖሊስ ዋና አዛዥ ከስራቸዉ ተነስተዋል። የሀገሪቱ ፕሪዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጥቃቱ ከደረሰ ከአንድ ሰዓት በኋላ በቴሌቭዥን ቀርበዉ ባደረጉት ንግግር የሃገሪቱ የፀጥታ ሃይላት በአሸባሪነት ላይ የተከፈተዉን የማጥቃት ዘመቻ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል። ይህንም ያሉት ኬንያ ዉስጥ በተደጋጋሚ ከአልቃይዳ ጋር ጥምረት እንዳለዉ የሚነገርለት የአሸባብ ታጣቂዎች ግድያን ከፈፀሙ በኋላ ነዉ።

የኬንያ መንግሥት የሶማልያዉን መንግስት በማገዝ አሸባብን ለማደንና በሶማልያ ጦሩን በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም ካስገባ ወዲህ አሸባብ ኃላፊነትን የወሰደበት ተከታታይ ጥቃት ኬኒያ ዉስጥ ማድረሱ ይታወቃል። የኬንያ መንግሥት ጦር አሁንም በሶማልያ የአፍሪቃ ጥምር ጦርን በመቀላቀል አሸባብን እያደነ መሆኑ ይታወቃል።

Uhuru Kenyatta Kenia Präsident
ምስል Reuters/Peter Dejong
Kenia Massaker in Mandera 2. Dezember 2014
ምስል DW/A. Kiti


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ