1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ጥቃትና ሥጋቱ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 30 2007

በጎርጎሮሳዊው 2011 ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በአመቱ ደግሞ ከኪስማዩ እንዲለቅ የተገደደዉ አል-ሸባብ ሰሞኑን እንደገና ያንሰራራ መስሏል።አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ባለፉት ሳምንታት በተከታታይ በከፈተዉ ጥቃት በርካታ የአፍሪቃ ሕብረትእና የሶማሊያ ወታደሮችን ገድሏል።የጦር ሠፈሮችንም አስለቅቆ፤ ተቆጣጥሯል።

https://p.dw.com/p/1Fu8d
Somalia Al-Shabaab Miliz (Symbolbild)
ምስል Stringer/AFP/Getty Images

አሸባብ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ባይካድም የጸጥታ ተንታኞች፤ ቡድኑ ከደፈጣ ጥቃት ባለፍ የመጠናከር እድል የለውም ይላሉ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአባታቸውን የትውልድ አገር ለመጎብኘት ዝግጅት በማድረግ ላይ በሚገኙበት ወቅት ዛሬ የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በሰሜናዊ ኬንያ ጥቃት ፈጽሟል።አሸባብ ኬንያ፤ ከሶማሊያና ከኢትዮጵያ የምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የማንዴራ ከተማ በጣለዉ ጥቃት 14 ሰዎች መገደላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ዘግቧል። በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ እና በሶማሊያ ጦር «ተሸንፏል፤ሊጠፋ ተቃርቧል» ሲባልበት የነበረው አሸባብ በቅዱሱ የጾም ወር-ረመዳን የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሯል። በአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ እና ተንታኝ የሆኑት አኔሊ ቦታ የአሸባብ-ታጣቂ ቡድን በሶማሊያ የሚቆጣጠረውን ግዛት ለማስለቀቅም ይሁን ተጽዕኖውን መቀነስ እንዲህ ቀላል አይደለም የሚል አቋም አላቸው።
«የሰርጎ ገብ ጥቃትን መዋጋት አመታት ይወስዳል። በአፍሪቃ ህብረትም ይሁን በአንድ አገር ፖለቲከኞች የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን ለማጥፋት ተቃርበናል በሚል የሚሰጥ አስተያየት እጅጉን አከራካሪ ነው። በሶማሊያ የሚሰሩ የጸጥታ ተንታኞች ግን የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን ከሶማሊያ ግዛት ለማጽዳት የሚቻለው ያንን ማድረግ የሚችል ሃይል ሲኖር መሆኑን ይናገራሉ። ሶማሊያ ለመቆጣጠር እጅግ በጣም ሰፊ አገር ናት። እንደ አለመታደል ሆኖ የሆነ ወቅት አሸባብ አንድ ግዛት ይቆጣጠራል መልሶ ደግሞ ያጣል። አሁን አሸባብ የተቆጣጠራቸውን ግዛቶች የሶማሊያ ጦር መልሶ ይይዛል። ይህ አሸባብ ተሸነፈ ማለት ነው? በፍጹም። ይህ ግዛትን የመቆጣጠር እና የመልሶ ማጣት ሂደት ሶማልያ በአጠቃላይ ግዛቷን ማስተዳደር እስክትችል ድረስ በተደጋጋሚ ይከሰታል። ይህ ደግሞ በጥቂት ወራት የሚሆን አይደለም።»
ሶማልያን ማረጋጋትም ይሁን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት ለዜጎቿም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈተና ሆኗል። የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ ሲፈርስ እንደ ጠንካራ ሐይል የወጣዉ አሸባብ የሶማልያን የጎሳ ፖለቲካና ወግ አጥባቂነት በመጠቀም ከፍተኛውን ጫና የፈጠረ ታጣቂ ቡድን መሆኑን የጸጥታ ተንታኞች ይናገራሉ። አኔሊ ቦታ ለአሸባብ እንቅስቃሴና አደረጃጀት ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾና ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርባት ኪስማዩ አስፈላጊ ቢሆንም ከተሞቹን የመቆጣጠር አቅም የለውም ባይ ናቸው።
«አሸባብ ኪስማዩን ወይም ሞቃዲሾን የመቆጣጠር አቅሙን እጠራጠራለሁ። መንግስት በእነዚህ አካባቢዎች ጠንካራ አቅም አለው። ለዚህም ነው አጥቅቶ የመሮጥ፤የፍንዳታ የሽብርተኝነት ጥቃቶችን የምንመለከተው። ይህ የተለመደ የሰርጎ ገብ ጥቃት መንገድን መከተል ነው።»
አሸባብ ከናይጄሪያው የቦኮሃራም ታጣቂ ቡድን እና በሰሜን አፍሪቃ የሰሐራ በርሃ ከሚገኘው የአልቃኢዳ ክንፍ ጋር ግንኙነት እንደነበረው የተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ያወጧቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ። አዲሱ የቡድኑ መሪ አህመድ ኡመርም ቢሆን አህመድ ጎዳኔ የጀመረውን የአልቃኢዳ ወዳጅነት ቀጥሏል። አሁን ግን በሶርያ እና ኢራቅ ከሚንቀሳቀሰው እና ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር የመወዳጀት ሃሳብ በአሸባብ ውስጥ ክርክር መፍጠሩን አኔሊ ቦታ ይናገራሉ።
«አሸባብ በአረብ ባህረሰላጤ ከሚገኘው የአልቃኢዳ ክንፍ ጋር የከረመ ግንኙነት አለው። በዚህም የአሸባብ ታጣቂዎች ድጋፍና ስልጠና በየመን ያገኛሉ። ከየመን የመጡ ታጣቂዎችም ከአሸባብ ጎን በመሆን በሶማሊያ ይዋጋሉ። ይሁንና ታማኝነታቸውን ከአልቃኢዳ ጋር የመቀጠል አሊያም ለአይሲስ (ISIS) የመቀየር ጉዳይ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ክርክር አለ። ለአሁኑ ግን የአሸባብ ታማኝነት ከአይሲስ (ISIS) ይልቅ ወደ አልቃኢዳ ያጋደለ ነው።»

AMISOM - Soldaten in Somalia
ምስል picture alliance/AP Photo/Jones
Somalia Mogadischu Sicherheitskräfte
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ