1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ጥቃትና የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት

ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2008

የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል «አሚሶም» አሸባብ ዛሬ የጣለዉን ጥቃት መመከቱን አስታወቀ። ጥቃቱ የተጣለዉ በማዕከላዊ ሶማልያ ከመቃዲሾ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ሃላጋን ከተማ በሚገኝ የጦር ሰፍር ላይ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከ100 በላይ ሚሊሽያዎች መግደላቸዉን ተናግሮአል።

https://p.dw.com/p/1J3w2
Somalische Friedensmission
ምስል picture-alliance/dpa/Amisom Photo /T. Jones

«አሚሶም» በሰጠዉ መግለጫ ጥቃቱን ሲመክት የሶማልያን መንግሥትን የሚወጋዉን የአሸባብ አክራሪ ደፈጣ ቡድን 101 አባላትን መግደሉን አስታውቋል። ቀደም ሲል አሸባብ ባወጣዉ መግለጫ በ«አሚሶም» ስር የዘመቱ 43 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድያለሁ ሲል አስታዉቆ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ዘገባውን ሃሰት ሲል አስተባብሎአል።

በሶማልያ የሚንቀሳቀሰዉ ሽምቅ ተዋጊቡድን አሸባብ የጣለበትን ጥቃት መመከቱን የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል «አሚሶም» ያስታወቀዉ ጽንፈኛ ቡድኑ በአሚሶም ስር የዘመቱ 43 የኢትዮጵያ ወታደሮችን፤ በአጠቃላይ 60 የአሚሶም አባላትን ገድያለሁ ብሎ ይፋ ካደረገ በኋላ ነዉ። የሶማልያ ባለስልጣናት ቆየት ብለዉ በሰጡት መግለጫ በጥቃቱ 30 የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸዉን ገልፀዋል። ዶይቼቬለ ዛሬ ጠዋት ያነጋገረው መቃዲሾ የሚገኝ ጋዜጠኛ መሀመድ ኦዶ በአሚሶም ኃይል ጥቃት መጣሉን አረጋግጦ፣ሆኖም ተገደሉ ስለተባለው ወታደሮች ቁጥር ግን የተረጋገጠ መረጃ እንዳላገኘ ተናግሯል።

Äthiopien Minister Getachew Reda
የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ረዳምስል DW/G. Tedla

«ከማለዳ ጀምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደገደሉ እየተናገሩ ነዉ። ይንን ማረጋገጥ አንችልም። የበለጠ መረጃ ለማግኘት እየሰራን ነዉ»

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አልሸባብ ሙከራ አደረገ እንጂ አንድም ጉዳት አላደረሰም ይላል። የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ረዳ

« አልሸባብ የመግደል ፍላጎት ነበረዉ። ሃላጋን የሚባል ቦታ ጥቃት ሞክሮ፤ አንድም እዚህ ግባ የሚባል ጥቃት ሳያደርስ 101 የአሸባብ አባላት በኢትዮጵያ ሰራዊት ተገድለዋል። ከአስር በላይ ከባድ መሳርያዎች ፤ ከዘጠና በላይ ቀላል መሳርያዎች፤ እንዲሁም አንድ ከባድ ተሽከርካሪ በሙሉ ከጥቅም ዉጭ ተደርገዋል። ለማምለጥ የሞከሩት በየመንደሩ ተለቅመዋል። ለማጥቃት የመጣዉም ኃይል ሙሉ በሙሉ ተደምስሶአል።»

Somalia al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Sheikh Nor

በሶማልያ የአሚሶም ቃል አቀባይ ለሮይተር በሰጡት መግለጫ፤ አሚሶም በጥቃቱ ላይ የነበሩ የአሸባብ ኃይላትን መገደላቸውን ተናግረዋል። አሸባብ በጥቃቱ 60 ገድያለሁ ማለቱን አሚሶም ሃሰት ሲል አስተባብሎአል። የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ረዳ፤ በኩላቸዉ አሸባብ የአደጋ ሙከራ ሲያደርግ ጉዳት አድርሻለሁ ማለቱ የተለመደ ነዉ።

በሶማልያ 22 ሺህ ወታደሮችን ያቀፈዉ የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል «አሚሶም» ከኢትዮጵያ ከኬንያ ከዩጋንዳ ከብሩንዲ የመጡ ወታደሮችን አካቶ ይዞአል። «አሚሶም» ሶማልያን ለማረጋጋትና ፀጥታ ለማስፈን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም ታኅሣሥ ወር ከፀደቀ በኋላ የሰላም ጓዱ በሶማልያ ከጎርጎረሳዉያኑ 2007 ዓ,ም መጨረሻ ጀምሮ መሰማራቱ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ