1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ጥቃት በሞቅዲሾ

ሰኞ፣ ሐምሌ 20 2007

ትናንት በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቅዲሾ በተጣለው የቦንብ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 15 መድረሱ ተሰምቷል። የሀገሪቱ ባለስልጣናት እና ምዕራባውያን በሚያዘወትሩት የጀዚራ ሆቴል ላይ ፈንጂዎች በጫነ የጭነት መኪና ለተፈጸመው ጥቃት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ሃላፊነቱን ወስዷል።

https://p.dw.com/p/1G5Ok
Somalia Terroranschläge auf Hotels in Mogadischu
ምስል Reuters/F. Omar

[No title]

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በሶማሊያ ጉዳይ ሊመክሩ ከናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ሲጀምሩ ሞቅዲሹ በፍንዳታ ተናወጠች። ምራባውያን የሚያዘወትሩትና የተሻለ የጸጥታ ጥበቃ በሚደረግለት አካባቢ የሚገኘው የጀዚራ ሆቴል የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ዒላማ ነበር። ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን የጫነው ጭነት መኪና በአካባቢው የነበሩ የፍተሻ ኬላዎችን እንዴት እንዳለፈ ባይታወቅም በፍንዳታው እስካሁን 15 ሰዎች መገደላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቅዲሹ የሚገኘው የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ዑመር ሐሰን ፍንዳታው በከተማዋ ከተከሰቱት ሁሉ ከፍተኛ እንደነበር ይናገራል።

Somalia Mogadischu Sicherheitskräfte
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

«ፍንዳታው የተከሰተው ወደ አየር ማረፊያ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲሆን ዒላማው ዲፕሎማቶችና የመንግስት ባለስልጣናት የሚያርፉበት የጀዚራ ፓላስ ሆቴል ነበር። የቻይና ኤምባሲም በአካባቢው ይገኛል። በሶማሊያ ዋና ከተማ ከተከሰቱት ፍንዳታዎች ሁሉ ትልቁ ነው።»

በኢትዮጵያ በጉብኝት ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ «ጥቃቱ እንደ አሸባብ ያሉ አሸባሪዎች ከጥፋት በስተቀር የሚያበረክቱት ነገር ባለመኖሩ ሊገቱ እንደሚገባ ያመለክታል።» ሲሉ ተናግረዋል።

ዲፕሎማቶች፣ ጋዜጠኞችና ሶማሊያን የሚጎበኙ የአገር መሪዎች ለማረፊያነት ይመርጡት የነበረው ባለ አምስት ፎቅ ሆቴል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ከሟቾቹ መካከል የኬንያ ዲፕሎማት ይገኙበታል ተብሏል።

ከሞቅዲሹ ኤደን አዴ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ የሚገኘው የጀዚራ ሆቴልና አካባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ ቦምብ የጫነው መኪና እንዴት ማለፍ እንደቻለ መሐመድ ዑመር አሁንም ምሥጢር እንደሆነ ይናገራል።

«የመንግስት ወታደሮችና በሆቴሉ አቅራቢያ የነበሩ የጸጥታ ተቆጣጣሪዎች መኪናውን ለማስቆም ሞክረው ነበር። በጣም ትልቅ የጭነት መኪና ነው። ሊያስቆሙት አልቻሉም። በዚህ መካከል ፈነዳ። አሁንም ምሥጢር የሆነው በርካታ የፍተሻ ኬላዎች በመንገዱ ላይ ይገኛሉ። መንግስት መኪናው የፍተሻ ኬላዎቹን አልፎ እስከፈነዳበት የሆቴሉ መግቢያ እንዴት እንደመጣ እና ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ በማጣራት ላይ ይገኛል።»

በበርካታ ተቀጣጣዮች የተሠራው ቦንብ በሆቴሉ አቅራቢያ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ማፈራረረሱን የሶማሊያ ፖሊስ አስታውቋል። ጥቃቱን የኮነኑት የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሰላም ዑመር አገራቸው ሰላም ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት አያደናቅፍም ብለዋል።

በጥቃቱ የኬንያ ዲፕሎማት፤ የቻይና ኤምባሲ የጥበቃ ሠራተኛና ሶስት ጋዜጠኞች ጨምሮ አስራ አምስት ሰዎች ሲገደሉ ከአርባ በላይ ቆስለዋል ተብሏል።

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዷል። ታጣቂ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቅዳሜ የሶማሊያ ምክር ቤት አባልን ከነጠባቂያቸውና አሽከርካሪያቸው በደቡባዊ ሞቅዲሹ መግደሉ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ከፍተኛ ዘመቻ የተከፈተበት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በሶማሊያ በእስላማዊ ሕግጋት የሚተዳደር መንግስት ለመመሥረት ሲታገል አስር ዓመታት ሞላው። አሸባብ ከ7-9 ሺህ የሚደርሱ ሶማሊያውያንና የውጭ ታጣቂዎች እንዳሉት የጸጥታ ተንታኞች የሚገምቱ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ መሆኑ ይነገራል።

Symbolbild al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል Imago/Xinhua

አሸባብ ከሞቅዲሹና ኪስማዩ ተገዶ ከወጣ በኋላ የሚያስተዳድረውን ግዛት፤ ሰውና ገንዘብ በመነጠቁ የመዳከም አዝማሚያ ቢያሳይም በኬንያ የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ 148 ሰዎች ከመግደል ግን አልተመለሰም።

የሶማሊያን ፖለቲካና የታጣቂ ቡድኑን እንቅስቃሴ ለሚያጠኑ አሸባብ ተንበርክኮም አሰቃቂ ጥቃት ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም። ለሶማሊያ መረጋጋት የአሸባብ መጥፋት ሁነኛ መፍትሄ ነው ሲሉም ይደመጣሉ።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ