1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአባባ ተስፋዬ ዜና ኅልፈትና  የዶ/ር መረራ እስር

ዓርብ፣ ሐምሌ 28 2009

የአባባ ተስፋዬ ዜና ኅልፈት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከፍተኛ ትኩረት ስቧል። በእስር ላይ የሚገኙት የዶ/ር መረራ ጉዲና ነው በሚል በኢንተርኔት የተሰራጨ ምስል በተመሳሳይ ሰፊ ሽፋን አግኝቷል። ምስሉ የሐሰት ወይንስ የእውነት?

https://p.dw.com/p/2hf00
Äthiopien Beerdigung des Künstlers Tesfaye Sahlu
ምስል DW/G. Tedla

በበርካቶች የልጅነት የትዝታ ማኅደር ውስጥ ልዩ ስፍራ አላቸው፤ አባባ ተስፋዬ። የኅልፈታቸው ዜና  ብዙዎችን ወደ ትዝታ ማኅደራቸው መልሷል። ዶ/ር መረራ ጉዲና እጃቸው በብረት ታስሮ ፍርድ ቤት ቀረቡ በሚል ዐረፍተ ነገሮች የታጀቡ አስተያየቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በአንዳንድ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል።  «የለም እሳቸው አይደሉም፤ ታስረውም አልቀረቡም» የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል። ክርክሩ ያታከታቸውም አልታጡም። በቦታው ለዘገባ የተገኘው ዘጋቢያችን ዶ/ር መረራ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበረውን ሁኔታ ገልጦልናል።

ከፊትና ከኋላ ቡራቡሬ የወታደር መለዮና ሙሉ የደንብ ልብስ ያደረጉ ወታደሮች መሣሪያ እንዳነገቡ ይታያል። ከኋላ ከሚከተሉት ሁለት ወታደሮች አጠገብ ጥቁር ሰማያዊ ልብስ የለበሰ፤ ግን ደግሞ ኮፍያ ያላደረገ ታጣቂ አመልካች ጣቱን ወደ መሬት የተዘቀዘቀ ጦር መሣሪያው ላይ ቀስሮ ይታያል። በእጃቸው ተንቀሳቃሽ ስልክ የያዙ፤ ሲቪል የለበሱ ሁለት ሰዎች፤ ከመሀከላቸው እጃቸውን ወደኋላ ያደረጉ እስረኛ እንደቆሙ ከግራና ከቀኝ አቅጣጫ ይታያሉ። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ከመሀል የሚታዩት እስረኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው ሲሉ ጽፈዋል። 

በዕለቱ ስለ ፍርድ ቤቱ ውሎ ለመዘገብ በሥፍራው ተገኝቶ የነበረው የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የተባለውን ምስል እሱም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ መመልከቱን ገልጧል። በቦታው የተመለከተው ግን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከተሠራጨው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ መኾኑን ተናግሯል። 

ዶ/ር መረራ ጉዲና በስተቀኝ ከዶይቸ ቬለ መቅረጸ-ድምጽ ፊት ለፊት
ዶ/ር መረራ ጉዲና በስተቀኝ ከዶይቸ ቬለ መቅረጸ-ድምጽ ፊት ለፊትምስል DW/Y.Egziabhare

ተሰማ በላይ በትዊተር ገጹ የሚከተለውን አስተያየት በእንግሊዝኛ አስፍሯል። «ኢትዮጵያውያን ዶ/ር መረራ እጃቸው ታስሯል አልታሰረም የሚል ሞቅ ያለ ክርክር ውስጥ መግባታቸው ሐቁን ላለማየት ምን ያኽል የሞራል አቅጣጫችን መስመሩን እንደሳተ ይናገራል» ሲል ትዝብቱን አስፍሯል። 

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍለ ጊዜ በረዥም ዘመን ልዩ አገልግሎታቸው ይታወሳሉ፤ አባባ ተስፋዬ ወይንም አርቲስት ተስፋዬ ሣኅሉ። ከ14 ዓመት ለጋ ዕድሜያቸው አንስቶ አዲስ አበባ ውስጥ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ተወልደው ያደጉት በባሌ ክፍለ- ሀገር ከዶ በተባለ ስፍራ ነው። ዘመኑም በ1916 ዓ.ም። 

በአፍላ ዕድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት አባባ ተስፋዬ ከትወና፣ እስከ ሙዚቀኛ፤ ከውዝዋዜ እስከ ድምጻዊ ብሎም ከመድረክ መሪ እስከ የልጆች ተረት ውብ ተራኪነት ዘርፈ-ብዙ ሙያ ባለቤት ነበሩ። ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓም በ94 ዓመታቸው (አንዳንዶች በ96 ዓመታቸው ሲሉ ዘግበዋል) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በትዝታ ግን በሚሊዮኖች አዕምሮዎች ይመላለሳሉ።

«የልጅነት ዘመናችን ታላቁ የሞራል አቅጣጫ መሪና አዝናኛችንን አጥተናል። ሌላ አባባ ተስፋዬ አይኖርም። ሕዝባዊ ሥርዓተ-ቀብር ይገባቸዋል» ሲል በትዊተር ገፁ አባባ ተስፋዬን በትዝታ የዘከረው ሃሌሉያ ሉሌ ነው። 

ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ በ«ማለዳ ወግ» የፌስቡክ ጽሑፉ «ኢትዮጵያ ታላቁን ልጇን አጣች፤ አባባ ተስፋዬ በአንድ ትውልድ ኅሊና የማይጠፉ መካሪ አባት ናቸው» ሲል ዘለግ ባለ ጽሑፉ ሙያቸውን በመዘርዘር ዘክሯቸዋል። «'ጤና ይስጥልኝ ልጆች ፣ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች ...'ብሎ በሚጀምረው የአባባ የማይረሳ መካሪ ፣ ዘካሪና አስተማሪ ዝግጅት ከፊል ትውልድ ተጠቅሟል ። ከፊል ትውልድ ራሱን አንቅቶ ፣ ለተሻለ ራዕይ ተዘጋጅቶ ፣ ከፍ ላለ ደረጃ በቅቷል» ሲልም የልጅነት ትውስታውን አካፍሏል። 

Kinder in Äthiopien
ምስል UNO

ብስራት ተሾመ ደግሞ፦ «ይነግሩን የነበሩት ታሪኮች ዛሬም በትዝታ ማኅደራችን ፍንትው እንዳሉ አሉ። የልጅነት ዘመናችን የደስታ ምንጭ ነበሩ። በሠላም ይረፉ» ሲል በትዊተር ገፁ ጽፏል። 

የምሥጋና ረጋሳ የፉፌስቡክ እንግሊዝኛ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «አባባ ተስፋዬ እግዚአብሔር ነፍሶትን በአጸደ-ገነት ያኑርልን! ተረቶት እና የልጆች ፕሮግራሞት የዘመኔ ህፃናትን፤ ወላጆቻችንን፤ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን አስደምመዋል፣ አዝናንተዋል ብሎም አስተምረዋል።»

ሔዋን ዘ ስምዖን የአባባ ተስፋዬ ዜና-ኅልፈተ በተሰማበት ቀን በእንግሊዝኛ ባሰፈረችው ጽሑፏ እንዲህ ብላለች በትዊተር ገጿ ላይ፦ «አባባ ተስፋዬ ዛሬ አረፉ፡፡ በስመ አብ፡፡ ነፍስ ይማር። እጅግ ዝነኛው አባባ ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያውያን ትውልዶች አባት ዛሬ አረፉ» ስትል ሰኞ ዕለት ሐዘኗን ገልጣለች። 

«ከሰውነቴ አንዳች አካሌን ያጣኹ ያኽል ነው የተሰማኝ። በሰላም ይረፉ አባባ ተስፋዬ» ያለችው ደግሞ ያቢ በላይ ናት በእንግሊዝኛ የትዊተር ጽሑፏ። ከጽሑፏ ጋር የሚያነባ የፊት ገጽና ቀይ ጎላ ያለ የልብ ምስልም አያይዛለች።

በአበባ ጉንጉን የተሽቆጠቆጠ ጥቁር የአስክሬን ተሽከርካሪና የለቀስተኞች ምስልን ያያያዘው ዘላለም አባተ «እጅጉን እንናፍቆታለን» ሲል ረቡዕ እለት በትዊተር ጽፏል። «አባባ ተስፋዬ ኢትዮጵያ በቅድስት ሥላሤ ካቴድራል ተቀብረዋል። እናመሠግናለን ደህና ሁኑ አባባ!» ሲልም ጽሑፉን በናፍቆት ስንብቱ አጠቃሏል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ