1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአባይ ዉሐ፥ ኢትዮጵያና የግብፅ ዉዝግብ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2005

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት የአባይን ውሐ ፍሰት እንዳይቀንስ ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች ከመውሰድ እንደማትቆጠብ ግብፅ አስጠነቀቀች ።

https://p.dw.com/p/18nwM
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images
Merowe Staudamm im Sudan
ምስል picture-alliance/Photoshot

 የግብፅ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ስለ አወዛጋቢው የአባይ ግድብ ለደጋፊዎቻቸው ትናንት ማምሻውን ባሰሙት ንግግር ከአባይ ወንዝ አንድ ጠብታ ውሐ እንኳን ቢጎድል ፣ የምንወስደው አማራጭ ደማችንን ማፍሰስ ይሆናል ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP ዘግቧል ። ጦርነት ናፋቂዎች አይደለንም ሆኖም ደህንነታችንን ማንም አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈልግም  ሲሉም ሙርሲ አስጠንቅቀዋል ። አንድ የሙርሲ አማካሪ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ የግድቡን ሥራ እንድታቆም ግብፅ ትጠይቃለች ብለው ነበር ።  የግብፅን አቋም ለማስረዳትም የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ከማል አመር  በመጪዎቹ ቀናት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሻም ካንዲል ተናግረዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር  ካንዲል  ለግብፃውያን ወሐ የሕይወትና የሞት ጥያቄ እንዲሁም የሃገሪቱ  ብሔራዊ ደህንነት ዋስትና እንደሆነም አስታውቀዋል ።  ስለ ግብፅና ኢትዮጵያ የአባይ ወሐ አጠቃቀም ውዝግብ የተጠየቁት የታንዛንያ የውሀ ህብት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ሱዲ ምኔቴ ውዝግቡ በሰለማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳስበዋል ። እንደ ባለስልጣኑ የውሐው አጠቃቀም በትብብር መከናወን ይኖርበታል ።

«ግጭትን ለማስቀረት ሠላማዊ የሚመስለኝ ብቸኛው መፍትሄ የተፋሰሱ አገራት በመተባበር በጠረጵዛ ዙሪያ መወያየታቸው ነው ። ይህ ነው ብቸናው መንገድ ምክንያቱም የውሐ ሃብት አስተዳደር የተፋሰሱን ሃገራት ትብብር ይሻል ። ለብቻ መሥራት አይቻልም ። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የውሐ ሃብት አስተዳደሩን ብቻየን መሥራት እችላለሁ የሚያስብ ከሆነ በጣም ስህተት ነው ። የውሃ ሃብቱን እንዴት በጋራ መጠቀም እንደሚችሉ መነጋገር አለባቸው ። »በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ና የግብፅ ውዝግብ ግብፅ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ችግር መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በእንግሊዘኛው ምህፃር UNHCR አስታውቋል ። ኮሚሽኑ እንዳለው ግብፅ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸውና ከመንግሥት አስተዳደር በኩል ጥቃት ና  ወከባ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል ። ግብፅ ለሚገኙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ደህንነትና መብቶቻቸውም እንደከበሩ አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸም  ዓለም አቀፉ ድርጅት አሳስቧል ።

Bildergalerie : Arbeitslosigkeit in Ägypten
ምስል picture-alliance / Rainer Hackenberg

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታሥገነባዉ የኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጫ ግዙፍ ግድብ ሠበብ ከግብፅ ጋር የገጠመችዉ የቃላት አተካራ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። ግድቡ ወደ ግብፅ የሚፈሠዉን የዉሐ መጠን ይቀንሳል ብለዉ የሰጉት የግብፅ ባለሥልጣናት የግድቡ ሥራ እንዲቆም እስከ መጠየቅ ደርሰዋል። የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሥለ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ባለሥልታናት ጋር ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ እንደሚሔዱ ባለፈዉ ዕሁድ ቢያስታዉቁም ከካይሮ የሚሠማዉ ማሳሰቢያ ግን እንደቀተለ ነዉ። የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ትናንት በሠጡት መግለጫ ግብፅ ወደ ሐገሯ ከሚፈሰዉ የአባይ ዉሐ መጠንም አንዲት ጠብታ እንኳ እንዲቀንስ አትፈቅድም። ነጋሽ መሐመድ ኢትዮጵያዊዉን የአፍሪቃ ጉዳይ የፖለቲካ አጥኚ አቶ ዩሱፍ ያሲንን በስልክ አነጋግሯቸዋል። «አተካራዉ ወዴት ያመራ ይሆን» ለሚለዉ ጥያቄ ከሰጡት መልስ ይጀምራሉ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ