1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽ አዲስ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅታለች ተብሏል

ሰኞ፣ ሰኔ 19 2009

የዩጋንዳዋ ኢንቴቤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በአባይ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጉባኤ አስተናግዳለች፡፡ ጉባኤው በመሪዎች ደረጃ የሚካሄድ ነው ይባል እንጂ ከአስሩ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ስብሰባውን ለመታደም ወደ ኢንቴቤ የተጓዙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2fQof
Karte Ägypten mit Nil ENG

የአባይ ጉዳይ- ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ

የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በሶስት ነገሮች ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ በመቆየታቸው፣ በቀልድ አዘል ንግግራቸው እና ለተጋባዥ የሀገር መሪዎች ሳይቀር በኩራት በሚያስጎበኟቸው በርካታ የቀንድ ከብቶቻቸው፡፡ የ72 ዓመቱ አዛውንት የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ከተቆናጠጡ 31 ዓመት ቢሞላቸውም አሁንም በቃኝ አላሉም፡፡ በቀጣይ ምርጫ ስለመወዳደር ሁሉ ያስባሉ፡፡ ተሰሚነታቸው ከሀገራቸው ተሻግሮ በቀጠናው እና በአህጉር ደረጃ ይዳረስ ዘንድ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

ሙሴቬኒ የሀገራቸውን ወታደሮች ከሶማሊያ እስከ ደቡብ ሱዳን፣ ከኮንጎ እስከ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ድረስ አሰማርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማሸማገል ሞክረዋል፡፡ በአባይ ዙሪያ ለሚነሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ላይ ታች ሲሉ ቆይተዋል፡፡ የአባይ ጥረታቸውን ከግብ ለማድረስ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን በተጠናል ወደ ሀገራቸው ጋብዘው መክረዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ምክክር ለማድረግም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት መሪዎች የሚገኙበት ጉባኤ አዘጋጅተዋል፡፡

Yoweri Museveni Präsident Uganda
ምስል picture alliance/Kyodo

ከአንድም ሦስቴ የተራዘመው ይህ የመሪዎች ጉባኤ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 15 በዩጋንዳዋ ኢንቴቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ሆኖም እንደተጠበቀው ሳይሆን ከአስሩ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ መሪዎች የተገኙት አስተናጋጇ ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ብቻ ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንቶቻቸውን ሲልኩ ቡሩንዲ በበኩሏ ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንቷን አሳትፋለች፡፡ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ታንዛንያ ከውኃ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሚኒስትሮቻቸው ተወክለዋል፡፡ 

“ታሪካዊ” በሚል ቅጽል ሲጠራ የሰነበተው ይህ ጉባኤ በአባይ አጠቃቀም ዙሪያ “አዲስ የማዕቀፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ መንገዱን የሚጠርግ ነው” ሲባል ቆይቷል፡፡ ሆኖም በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ የታየው በተሳትፎ የተስተዋለው መቀዛቀዝ ነው፡፡ በጉባኤው ማብቂያ ተሳታፊዎቹን መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናትን በአንድ መድረክ ደረድረው ለጋዜጠኞች ቁጥብ ገለጻ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የሚታወቁበትን በቀልድ የተዋዛ ንግግር ጣል ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

“ለአባይ ተፋሰስ ሀገራት በርዕሳነ ብሔራት ደረጃ ይህ የመጀመሪያው ጉባኤ ነው፡፡ ከፈርኦኖቹ ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ጉባኤ አልነበረም፡፡ ይህ የመጀመሪያው ነው” ሲሉ ሙሴቬኒ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡   

ሙሴቬኒ የጉባኤውን ታላቅነት ለመግለጽ ቢደክሙም ስለውይይቱ ዝርዝርም ሆነ ውጤት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ከጋዜጠኞችም ምንም ዓይነት ጥያቄ እንደማይቀበሉም አሳውቀዋል፡፡ በጉባኤ ተነስቷል ብለው የጠቀሱትም ቢሆን ከወራት በፊት ፕሬዝዳንት አልሲሲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ወደ ዩጋንዳ በጋበዙ ወቅት የአባይን ችግር ለመፍታት በመፍትሄነት የጠቆሙትን የደገመ ነው፡፡ 

“በውይይቱ ወቅት የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን ከሀገራትም በላይ የመጀመሪያው ዓለም ሀገራት ለማድረግ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡ ምክንያቱም አሁንም ቢሆን እንደ ሦስተኛ ዓለም ሀገራት ነው የሚቆጠሩት፡፡ እያልን ያለነው የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን ወደ ሌላ ደረጃ ለማሸጋገር ተባብረን መስራት አለብን ነው፡፡”

Ägypten - Präsident Abdel Fattah al Sisi
ምስል picture-alliance/dpa

የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ተመሳሳይ መልዕክት ያለው ንግግር በስብሰባው ላይ አድርገዋል፡፡ “የናይል ወንዝ ሊያስተሳስረን እንጂ ሊከፋፍለን አይገባም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ሀገራችንን ለመገንባትና ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ እና የሰው ሃብቶቻችን ለመጠቀም ያለን የጋራ ፍላጎት፣ ከልዩነቶቻችን ይልቅ የገዘፈ እና በጣሙኑ ጠቃሚ ነው” ሲሉ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ትብብርን በንግግራቸው በተደጋጋሚ ቢያነሱም የሀገራቸውን አንገብጋቢ ጉዳይ አጽንኦት ከመስጠት ግን ቸል አላሉም፡፡ ግብጽ 97 ከመቶ የውኃ ፍላጎቷን ከናይል ወንዝ እንደምታገኝ አስታውሰው ሆኖም ከህዝቧ መጨመር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ችግር እንዳለባት አንስተዋል፡፡ ከህዝብ ብዛቱ የተነሳ ለአንድ ሰው የሚደረሰው የውኃ ድርሻ በዓመት ወደ 640 ኪዩቢክ ሜትር መውረዱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ በዓመት የ21.5 ቢሊዩን ኪዮቢክ ሜትር ውኃ እጥረት እንዳለባት አስረድተዋል፡፡ 

ግብጽ ያለባትን የውኃ  አቅርቦት ክፍተት ለመድፈን እስከ 80 ከመቶ የሚሆነውን አገልግሎት ላይ የዋለ ውኃ መልሳ በመጠቀም ላይ እንደትምገኝ ያብራሩት አልሲሲ “ለዚህም ነው የግብጽ ህዝብ በውኃ ደህንነቱ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ የሚያመጣ ማናቸውም ነገር በጣም በጥንቃቄ የሚይዘው” ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኢትዮጵያን ባይጠቅሱም መልዕክታቸው ግን በአባይ ላይ ግድብ እየገነባች ላለችው ኢትዮጵያ የተሰነዘረ እንደሆነ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡

የውኃ ደህንነት ጉዳይ ግብጽ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperative Framework Agreement) እየተባለ የሚጠራውን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት እንዳትፈርም ካደረጓት ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ በካይሮ ዩኒቨርስቲ የውኃ ሃብት መምህር የሆኑት ዶ/ር ናዴር ኑረዲን ለዶይቸ ቨለ ይናገራሉ፡፡ በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2010 ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት ሀገራት በኢንቴቤ የተፈረመው ይህ የማዕቀፍ ስምምነት ስለ ውኃ ደህንነት ራሱን የቻለ አንቀጽ መድቧል፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 14 የተፋሰሱ ሀገራት የውኃ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ዘላቂ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰሩ ግብጽ ጉዳዩን የምትመለከትበት መነጽር ግን የተለየ ነው፡፡ ዶ/ር ናዴር የግብጽን አተያይ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

“የኢንቴቤው ስምምነት እንደሚያስቀምጠው በላይኛው የናይል ተፋሰስ ያሉ ሀገራት የራሳቸውን የውኃ ደህንነት ቅድሚያ እንደሚሰጡ እና ቀሪውን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሊተው እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ ይህ መርህን ያልተከተለ እና ህጋዊ ያልሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም በተናጠል ውሳኔ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን የውኃ ደህንነት ካስጠበቀ ሁሉንም ውኃ ሊወስድ ይችላል፡፡ መሆን የነበረበት ግን በናይል ተፋሰስ ያሉትን ሁለንም የውሃ ሃብቶች በትብብር መጠቀም ነው፡፡” 

Ägypten Kairo
ምስል picture-alliance/Bildagentur-online

ግብጽ እና ሱዳን የውኃ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ተጨማሪ መተማመኛ በአንቀጽ 14 ካልተካተተ በሚል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ለመፈረም አሻፈረኝ ቢሉም ሁለት ሀገራት ዘግይተው በመቀላቀላቸው የፈራሚዎቹ ቁጥር ስድስት ደርሷል፡፡ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በአንቀጹ ይካተት የሚሉት ንዑስ አንቀጽ “የተፋሰሱ ሀገራት አሁን ያለውን የውኃ አጠቃቀምና መብት ላለመጉዳት መስማማት አለባቸው” የሚል ነው፡፡ ይህ ግብጽ እና ሱዳንን ከሌሎቹ ተፋሰስ ሀገራት ያለያያቸው ሁለተኛ ነጥብ እንደሆነ ዶ/ር ናዴር ይናገራሉ፡፡ 
በጎርጎሮሳዊው 1959 የግብጽ እና ሱዳን ገዢዎች በነበሩ ብሪታንያውያን የተፈረመው የአባይ ወንዝ ስምምነት “ፍትሀዊ አይደለም፣ ገዢም አይደለም” ሲሉ የሚከራከሩት ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ይህን የሁለቱን ሀገራት ጥያቄ አልተቀበሉትም፡፡ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ስምምነት ጽንሰ ሀሳብን ይጣረሳል ሲሉ ውድቅ ያደርጉታል፡፡ 

የትብብር የማዕቀፍ ስምምነቱ መሻሻል እንዳለበት ስትወተውት የቆየችው ግብጽ ከኢንቴቤው ስብሰባ በፊት ስምምነቱን የሚተካ አዲስ ሰነድ ማዘጋጀቷን የሀገሬው መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር፡፡ አል ሸሩቅ እንደተሰኘው የግብጽ ጋዜጣ ከሆነ ሰነዱ በዓለም አቀፍ ህግጋት ላይ ተመስርቶ የአባይን ወንዝ አጠቃቀም መርሆዎች፣ መብቶች እና ግዴታዎችን የዘረዘረ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ፍትሃዊ፣ ተመጣጣኝ እና በሌሎች ላይ ጉዳት የማያስከትል የውኃ አጠቃቀም እንደተካተተበት ጋዜጣው ገልጾ ነበር፡፡ 

የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ሀገሪቱ አዘጋጅተዋለች ያሉትን ሰነድ በዝርዝር ቢያቀርቡም በኤንቴቤው ጉባኤ እንደዚህ አይነት አዲስ እቅድ አለመነሳቱን ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የግብጽም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎች ይናገራሉ፡፡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አህመድ አቡዘይድ ግብጽ እንዲህ አይነት ሰነድ አለማቅረቧን ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ 

“ይህ ሀሰት ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ እኛ ምን ዓይነት ማዕቀፍም ሆነ ሌላ ነገር አላቀረብንም፡፡ እኛ የተወያየነው በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ስላለ ትብብር ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ሊኖር ስለሚገባው ትብብር ማለት ነው፡፡ ምንም ዓይነት አዲስ የህግ ማዕቀፍ አልነበረም፡፡ እንዲህ የሚመስል እንኳ አልነበረም፡፡” 

ግብጻዊው ዶ/ር ናዴር ግን አዲስ ሰነድ መዘጋጀቱን ከሀገሪቱ ባለስልጣናት መስማታቸውን ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል፡፡ ግብጽ ሰነዱን በኤንተቤ በተካሄደው ስብሰባ ወቅት ማስረከቧን የሚናገሩት መምህሩ የተፋሰሱ ሀገራት ሰነዱን ተመልክተው አስተያየት ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመናገራቸው ጉዳዩ በቀጣዩ ወር ለሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ መገፋቱን ያብራራሉ፡፡ ከሰነዱ ሌላ ትኩረት ሳቢ የነበረው ግብጽ Nile Basin Initiative ወደተሰኘው ተቋም ለመመለስ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ነው፡፡ 

ግብጽ የኤንቴቤው የትብብር ስምምነት መፈረምን በመቃወም የተፋሰሱ ሀገራት ከመሰረቱት Nile Basin Initiative የትብብር ተቋም ራሷን ለሰባት ዓመታት አግልላ ቆይታለች፡፡ ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ግን የአቋም ለውጥ ማድረጓን በተቋሙ ስብሰባ ላይ በመሳተፍ አሳይታለች፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢንቴቤ ተካሄዶ በነበረው ስብሰባ ላይም የግብጽ ወደ ተቋሙ መመለስ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ውይይት እንደነበር አልካዱም፡፡  

Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

“ግብጽ ከ Nile Basin Initiative አባልነት እና ተሳትፎ መታቀቧን በማስወገድ ላይ ተወያይተናል፡፡ የተወሰነ ውይይት ነበር ግን ምንም ዓይነት ውሳኔ አልተላለፈም፡፡” 

ግብጽ የ Nile Basin Initiative አባልነቷን እንደገና ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን የሚናገሩት አህመድ ነገር ግን ይህ የሚሆነው ቅድሚያ መሟላት የሚገባው ከተፈጸመ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል “ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ መግባባት” ካለ እና የ“ቅድሚያ ማሳወቅ” ስልትን አስመልክቶ ስምምነት ላይ ከተደረሰ ግብጽ ወደ ትብብር ተቋሙ ልትመለስ እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ “ቅድሚያ ማሳወቅ” የሚለው ግብጽን ከሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ከማያስሟሟት ሶስት ቁልፍ ጉዳዩች አንዱ እንደሆነ ዶ/ር ናዴር ይናገራሉ፡፡ 

ግብጽ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት እንደ ግድብ የመሳሰሉ ማንኛውንም ግንባታዎች በአባይ ተፋሰስ ላይ ሲያከናውኑ በቅድሚያ ማሳወቅ አለባቸው ባይ ነች፡፡ ይህ በትብብር የማዕቀፍ ስምምነቱ ላይ የተቀመጠውን ሀገራቱ ሌላውን በማይጎዳ መልኩ የየራሳቸውን ፕሮጀክት የማካሄድ መብት የሚጥስ ነው ሲሉ ሌሎች ሀገራት ይቃወሙታል፡፡ ግብጽ ወደ Nile Basin Initiative ለመመለስ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠች እንደማይቀበሉትም ግልጽ አድርገዋል፡፡

የኢንቴቤውን ስብሰባ አስመልክቶ የኢትዮጵያን አቋም ለማወቅ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ይፋዊ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት  በጉዳዩ ላይ መግለጫ ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንዳለ ግን ምንጮች ገልጸውልናል፡፡ ጉባኤው “ትብብር እና መተማመንን የመገንባት” አላማ ነበረው የምትለው ግብጽ ከዚህ አንጻር ስብሰባው “ውጤታማ ነበር” ብላለች፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ