1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአተት በሽታ ድርቅ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2009

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቁን ተከትሎ የተከሰተዉ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት በሽታ በክልሉ ከሚገኙ 11 ዞኖች ዉስጥ በዘጠኙ ተከስቶ የነበረ መሆኑን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስታዉቋል። ጽሕፈት ቤቱ እንዳለው፣ መንግስት ባደረገዉ ርብርብ በሽታዉ በአሁኑ ወቅት 70 ከመቶ ቀንሷል።

https://p.dw.com/p/2bRj4
Äthiopien Frauen mit Kindern
ምስል Reuters/T. Negeri

Acut Diarrhea and Vomiting in somali Region . - MP3-Stereo

በሽታዉ በሶማሌ ክልል ቀነሰ ቢባልም ግን ፣ በሀገሪቱ  ድርቅ ባጠቃቸዉ ሌሎች ክልሎችም ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እየገለጸ ነዉ። 

በኢትዮጵያ ድርቅ ከተከሰተባቸዉ አካባቢዎች አንዱ በሆነዉ የሶማሌ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድርቁን ተከትሎ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት በሽታ በርካቶችን እያጠቃ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል። በክልሉ በሚገኙ አብዛኛወቹ አካባቢወች በሽታዉ የተዛመተ ሲሆን  በድርቁ ሳቢያ የተከሰተዉ የንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ችግር በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የክልሉ አርብቶ አደር ዉሃና  የግጦሽ ሳር ፍለጋ ወረርሽኙ  ቀድሞ  ወደ ተከሰተባቸዉና  ለክልሉ ቀረቤታ ወዳላቸዉ ወደ ሶማሊያና ሶማሌ ላንድን  በመሳሰሉ  ጎረቤት ሀገሮች  የሚያደርገዉ እንቅስቃሴም ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የሶማሌ ክልል የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ እንድሪስ እስማኤል አብራርተዋል።

እንደ ጽህፈት ቤቱ ገለጻ በሽታዉን ለመቆጣጠር ከተለያዩ ክልሎች የተዉጣጡ 500 የሚደርሱ  የጤና ባለሙያወች ወደ ክልሉ ተሰማርተዉ ባደረጉት ጥረት በአሁኑ ጊዜ  70 በመቶ ሊቀንስ ችሏል። በሽታዉ በተዛመተባቸዉ አካባቢወች የተቋቋሙ አብዛኛወቹ ጊዚያዊ የአገልግሎት መስጫ ኬላወችም እንደተዘጉ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል።

Äthiopien Schlimmste Hungersnot seit 30 Jahren
ምስል Reuters/T. Negeri

በክልሉ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በድርቁ ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊወች ናቸዉ።በዚሁ ሳቢያ በክልሉ በሽታዉ በተከሰተባቸዉ አካባቢች  የሚገኙ  ሰወች ቀደም ብለዉ በምግብ እጥረት በመጎሳቆላቸዉ  በበሽታዉ ክፉኛ መጎዳታቸዉንና ለህልፈተ ህይወት የበቁ መኖራቸዉንም  አንዳንድ አለም አቀፍ  ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።። ይሁን እንጅ በክልሉ እስካሁን በበሽታዉ የሞቱ ሰዋች ቁጥር በዉል አለመታወቁን የጽህፈት ቤት ሃላፊዉ አቶ እድሪስ ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል በሽታዉ በቁጥጥር ስር ዉሏል ቢባልም  በሀገሪቱ  ድርቅ በተከሰተባቸዉ  የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችም ለዚሁ በሽታ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ  የሚል  ስጋት  እያንዣበበ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ገልጿል።በመሆኑም ህብረተሰቡ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ