1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደህንነት ስጋት ወደ ኢትዮጵያ አልመለስም ብሏል

Eshete Bekeleእሑድ፣ ነሐሴ 15 2008

በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድርን በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ እጁን ከፍ አድርጎ በማጣመር የተቃውሞ ምልክት ያሳየው ፈይሳ ሌሊሳ የኢትዮጵያ መንግስትን ተቸ

https://p.dw.com/p/1JmYA
Brasilien Olympische Spiele Rio 2016 21 08 - Marathon Feyisa Lilesa
ምስል Getty Images/AFP/O. Morin

በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሌሊሳ የማራቶን ውድድርን በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ እጁን ከፍ አድርጎ በማጣመር በኢትዮጵያ ተቃውሞዎች በብዛት የሚስተዋለውን ምልክት አሳየ። ፈይሳ የማራቶን ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2:09:54 የፈጀበት ሲሆን ኬንያዊው ኢልዩድ ኬፕቾጌ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። ፈይሳ ከውድድሩ ካጠናቀቀ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ-ምልልስ የኢትዮጵያ መንግስትን ተችቷል። «በእስር ላይ የሚገኙ ዘመዶች አሉኝ።» ያለው ፈይሳ «ስለ ዴሞክራሲ ካወራህ ይገድሉኃል።» ሲል አክሏል። የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ፈይሳ ሌሊሳ«ወደ ኢትዮጵያ ብመለስ ምን አልባት ይገድሉኝ ወይም ያስሩኝ ይሆናል።» ሲል ሥጋቱን ገልጧል። ፈይሳ የተቃውሞ ምልክቱን ከውድድሩ በኋላ ከአሸናፊዎቹ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ከጋዜጠኞች ፊት ደግሞታል። ውድድሩን ካጠናቀቀም በኋላ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን ይዞ አልታየም።

«በአገሬ ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው። ምን አልባት ወደ ሌላ አገር መሔድ ይኖርብኝ ይሆናል።» ያለው ፈይሳ «የተቃወምኩት በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ ነጻነት ለሌላቸው ሰዎች ነው።» ብሏል። ፈይሳ እጁን ያጣመረው በኢትዮጵያ በመንግስት ለሚገደሉ ተቃዋሚዎች ያለውን ድጋፍ ለማሳየት እንደሆነም ተናግሯል። «በእዚያ ተመሳሳይ ምልክት ያሳያሉ» ያለው ፈይሳ «እየተደረገ ባለው ነገር እንደማልስማማ ማሳየት እፈልጋለሁ፤በእስር ላይ የሚገኙ ዘመዶች እና ጓደኞች አሉኝ።» ብሏል። ፈይሳ የኢትዮጵያ መንግስት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎችን እየገደለ ነው ሲልም ወቅሷል።

ፈይሳ ዓለም አቀፍ ትኩረት በሚስበው የማራቶን መድረክ ያሳየው የተቃውሞ ምልክት ፌስቡክና ትዊተርን በመሰሉ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተቸሮታል። ኢትዮጵያውያኑ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነውን የማራቶን አትሌት «ጀግና» ሲሉ አወድሰውታል።

«ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች አሏት። አንዳንዶቹ በመንግስት መሬታቸውን ተቀምተዋል፤ተገድለዋል።» ብሏል የማራቶን አትሌቱ። «ሰላም እና ዴሞክራሲ እንፈልጋለን።» ያለው ፈይሳ ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለስ ተናግሯል። በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ቤተሰቦቹ ደህንነት ስጋት እንደሚሰማውም ገልጧል።

ትውልደ ሶማሊያዊው ሞሐመድ ፋራህ በሪዮ ኦሎምፒክ የ5000 ሜትር የሩጫ ውድድርን በ13:03.30. በመፈጸም በድጋሚ በኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ላይ የበላይነቱን ተቀዳጅቷል። ኢትዮጵያውያኑ ደጀን ገብረመስቀል እና ሐጎስ ገብረ ህይወት ዙሩን በማፍጠን ሞሐመድ ፋራህን ለማድከም ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ውድድሩን በሶስተኛነት በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ሐጎስ ገብረ ህይወት በውድድሩ ሙሉ ትኩረቱ በሞ ፋራህ ላይ እንደነበር እና በመጀመሪያዎቹ ስድስት ዙሮች እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩም አለመሳካቱን ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግሯል። አሜሪካዊው ፓል ኪፕኬሞይ ቼሊሞ ውድድሩን በሁለተኝነት አጠናቋል። ኢትዮጵያዊው ሙክታር ኢድሪስ ውድድሩን በአራተኝነት ቢያጠናቅቅም ከመሮጫ መም ውጪ ሮጠሃል በሚል ውጤቱ ተሰርዞበታል። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እንደ አሜሪካ እና ካናዳ አቻዎቻቸው አቤቱታ ባለማቅረባቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተተቹ ነው። ኢትዮጵያ እስካሁን በውድድሩ አንድ የወርቅ፤ሁለት የብር እና አምስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ