1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአናፖሊሱ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጉባኤ

ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2000

የእስራኤልና የፍልስጤም መሪዎች ለፍልስጤም መንግስት ምስረታ የሚያበቃ የሰላም ውል ላይ እ.አ.አ በሁለት ሺህ ስምንት መጨረሻ ለመድረስ እንደሚሞክሩ ቃል ገብተዋል ።

https://p.dw.com/p/E87T
ቡሽና አባስ በዋይት ሀውስ
ቡሽና አባስ በዋይት ሀውስምስል AP

ዛሬ በይፋ የሚጀመረው አዲሱ የእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ድርድር ፍልስጤማውያን ወደፊት የተሻለ ህይወት ሰላምና መኖሪያ ማግኘት የሚያስችላቸው አማራጭ ራዕይ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ አስታወቁ ።
ድምፅ ቡሽ
« ራሱን ችሎ በነፃነት የሚንቀሳቀስ መንግስት ህልማቸው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚካሄድ የሰላም ድርድር ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ለፍልስጤማውያን ማሳያ ጊዜው አሁን ነው ። በፍልስጤም አክራሪዎች የሚሰበከው ሽብርና ብጥብጥም የፍልስጤም መንግስት እንዳይመሰረት ዋነኛ ጋሬጣ ነው ። » ፕሬዝዳንት ቡሽ የስልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት አናፖሊስ ውስጥ በመስተናገድ ላይ ባሉት የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጉባኤ ትናንት የእስራኤልና የፍልስጤም መሪዎች ለፍልስጤም መንግስት ምስረታ የሚያበቃ የሰላም ውል ላይ እ.አ.አ በሁለት ሺህ ስምንት መጨረሻ ለመድረስ እንደሚሞክሩ ቃል ገብተዋል ። አርባ አራት መንግስታት በተገኙበት በዚሁ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ይህን ቃል በገቡ በማግስቱ ዛሬ በይፋ አዲስ ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ይጀምራሉ ። ዛሬ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ቡሽ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልሜርትና የፍልስጤሙን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን በተናጠል ያነጋግራሉ ። ከዚያም ሁለቱ መሪዎች ባሉበት የሰላም ንግግሩ በይፋ መጀመሩ ይነገራል ። የእስራኤእልና የፍልስጤም መሪዎች የዚህ ዓይነቱን ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ካካሄዱ ሰባት ዓመት ሆኗቸዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊሳ ራይስ እንዳስታወቁት የአናፖሊሱ የሰላም ጉባኤ የሰላሙ ሂደት መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም ። ብዙ መስዋዕትነትም ይጠይቃል ።
«የአናፖሊሱ ጉባኤ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ለማስፈን የሚደረጉት የአዳዲስ ተከታታይ አጋዥ ጥረቶች መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም ። ስራው ከባድ ነው የሚሆነው ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ አደጋ ሊቃጣባቸው ይችላል መስዋዕትነትም ይጠብቃቸዋል ። »
ራይስ ይህን ቢሉም ለእስራኤእል ፍልስጤም ውዝግብ ዘላቂ መፍትሄ በመሻት ረገድ ከሁሉም ወገኖች በኩል ቁርጠኝነቱ መኖሩን የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች መጠራጠራቸው አልቀረም ። የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ማርክ ሬጌቭ እንደሚሉት ግን አሁን ችግሩን ማቃለያው ዕድል ያለበት ወቅት ነው ።
«ጥርጣሬ አለ ። በፍልስጤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል ጥርጣሬ ያለ ይመስለኛል ። ሆኖም አሁን ዕድሉ ያለበት ወቅት ነው ብዮ አምናለሁ ።አሁን የሰላሙን ሂደት በአፋጣኝ ማንቀሳቀስ አለብን ። የጨዋታው ዓላማ በመጪዎቹ ዓመታት ከፍልስጤማውያን ጋር ታሪካዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ መሞከር ነው ። »
ቃል አቀባይ ሬጌቭ ታሪካዊ ስምምነት ያሉት የፍልጤምን መንግስት ምስረታ ዕውን ሊያደርግ የሚችለውንና የዛሬ ዓመት ይፈረማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ውል ነው ። እንደ ፍልስጤም ዋነኛ ተደራዳሪ ሳኤብ ኤሬካት ውሉን ተግባራዊ ለማድረግ ያን ያንያህል ጊዜ መጠበቅ የለበትም ።
« ዛሬ ፍልስጤማውያንና እስራኤላውያን ውሳኔ ነው የሚያስፈልጋቸው ። ድርድሮቹ የተካሄዱ ይመስለኛል ። ካምፕ ዴቪድ ነበርን ጉዳዮቹን እናውቃቸዋለን ። የድርድሮቹን ውጤትም እናውቃለን። ሁለቱ አገሮች ጎን ለጎን በሰላም የሚኖሩበትን ስምምነት ላይ መድረስ የኛ ፈንታ ነው ። ይህ ከተደረገ እና ውሳኔ ላይ ከተደረሰ ውል ለመፅደቅ ከሶስትና ከስድስት ወራት በላይ አያስፈልግም »
ከአስራ አምስት ቀን በኃላ በሚቀጥለው የእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ንግግር ላይ የድንበርና የሰፋሪዎች ጉዳይ የእየሩሳሌም እና የፍልስጤም ስደተኞች ዕጣ ፈንታ ድርድር ይካሄድበታል ። አንዳንድ ተንታኞች አስተያየታቸውን እንደሰጡት በስራኤላውያን መራጮች ዘንድ ብዙም ተቀባይነት የሌላቸው ኦልሜርትም ሆኑ የጋዛ ሰርጥን ያጡት አባስ የተሳበውን የሰላም ውል ማሳካት መቻላቸው ያጠራጥራል ። ቡሽም ቢሆኑ በስድስት ዓመታት የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ዞር ብለው ያላዩትን የእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ከልብ መያዛቸው በከፊል አጠራጣሪ ነው የተባለው ።