1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንድነት ፓርቲ እና የሥልጣን ሽኩቻ

ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2006

አምስት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሃላፊነታቸው የለቀቁበት ምክንያት አልገባኝም ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝደንቱ አስታወቁ።የፓርቲዉ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እንደሚሉት ከሥልጣን የለቀቁት አምስቱ ሰዎች በደብዳቤ ከገለፁት በስተቀር የሚያዉቁት የለም።

https://p.dw.com/p/1Cwcn
Gambia Street in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል picture alliance/dpa

የስራ አስፈጻሚነታቸውን ከለቀቁት አባላት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ተክሌ በቀለ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጋር ለመዋሃድ ሙከራ በተደረገበት ወቅት የተፈጸመው ስህተት አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ።

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር ውህደት ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አምስት አባላት ከስራ አስፈጻሚነታቸው መልቀቃቸውን ለፕሬዝደንቱ ባቀረቡት ደብዳቤ አስታወቁ። ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሥዩምና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዳዊት አስራዱ ከስራ አስፈጻሚነታቸው የለቀቁበት ምክንያት አልገባኝም ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝደንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ተናግረዋል።የስራ አስፈጻሚ አባላቱ የለቀቁበትን ምክንያት በግልጽ አይታወቅም የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው ቢሆንም ከእርሳቸው ጋር ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ከደብዳቤያቸው ተረድቻለሁ ይላሉ።

Karte Äthiopien englisch

ራሳቸውን ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካገለሉት መካከል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ዳንኤል ተፈራ ‹‹በትግሉ በሚሰጡት አመራር ልዩነት አለን፡፡ ፕሬዚዳንቱ እየሰጡት ያሉት አመራር ወደፊት ያራምዳል ብለን አናምንም፡፡ በአመራራቸው ሳናምን ደግሞ መቀጠል አንችልም፡፡ ለዚህ ነው ራሳችንን ያገለልነው›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የአንድነት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ተክሌ በቀለ በበኩላቸው ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጋር ውህደት ለመፈጸም ሲሞከር የተፈጠረው ስህተት ከስራ አስፈጻሚነታቸው መልቀቅ አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ስዩም መንገሻም ከፕሬዝደንቱ ጋር በተፈጠረ ልዩነት ራሳቸውን ያገለሉት የስራ አስፈጻሚ አባላት በፓርቲ አባልነታቸውና በሌሎች የፓርቲ እንቅስቃሴዎች በተሳትፏቸው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

የፓርቲው ፕሬዝደንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የአምስቱ ስራ አስፈጻሚዎች በአንድ ጊዜ ከሃላፊነት መልቀቅ በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ሙሉዉን ዘገባ የድምፅ ማእቀፉን በመጫን ያድምጡ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ