1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ ምሥረታ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2006

የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ መርሃግብር ከተቋቋመ ረዥም ዓመታት አስቆጥሯል። በዚህ ጊዜ ዉስጥ እንደድርጅቱ የበላይ ኃላፊ እምነት የአካባቢ ተፈጥሮን የሚመለከቱ ጉዳዮች በቂ ነዉ ባይባልም ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።

https://p.dw.com/p/1CU4C
Nairobi - erste Sitzung der neu eingerichteten Umweltversammlung der Vereinten Nationen UNEA
ምስል picture-alliance/Landov

ዘላቂ ልማት ሲታሰብ ምድር ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ከግምት ያስገባ መሆን እንደሚኖርበት የሚሟገቱት ለተፈጥሮ ሃብት ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስቡት ወገኖች ግን የተጮኸዉን ያህል ዉጤት አላየንም በሚል የተቃዉሞ ድምፃቸዉን ዛሬም አልገቱም። የተለያዩ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች መካሄዳቸዉ ባይታበልም የፖለቲካዉ መሪዎች በየግል ጉዳያቸዉ በመጠመዳቸዉ አለያም በተለያየ አካባቢ በየጊዜዉ በሚከሰተዉ የፀጥታ መደፍረስና ያለመረጋጋት ስጋት ቀልባቸዉ በመያዙ የተፈጥሮ አደጋዎችና ጥፋቶችን ችላ ያሏቸዉ ይመስላል በሚል የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች በየጊዜዉ ይተቻሉ። የሁሉንም ትኩረት ይስብ እንደሁ በሚል ይመስላል ባለፈዉ ሳምንት ናይሮቢ ኬንያ ከሰኞ ዕለት አንስቶ በተካሄደዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉባኤ አንድ ሌላ ከፍተኛ አካል እንዲመሠረት ሆኗል።

ባለፈዉ ሳምንት ከሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የዘለቀዉ በናይሮቢ የተካሄደዉ የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ UNEA በዓይነቱ የተለየ እና ኬንያም ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችዉ ታላቅ ጉባኤ ነበር። ከ150 በላይ ከፍተኛ ልዑካን የአካባቢ ተፈጥሮ ዘላቂነት እንዳይኖረዉ የገጠሙ ተግዳሮቶችን የዘረዘሩበት ይህ ጉባኤ የሞንጎሊያን የአካባቢ ጥበቃና የአረንግዴ ልማት ሚኒስትር ኦዩን ሳንጃሱረን ለUNEA ፕሬዝደንነት መርጧል። UNEA በተመድ የአካባቢ ተፈጥሮን ጉዳይ የሚመለከት በድርጅቱ መዋቅር ከፍተኛዉ አካል እንዲሆን ነዉ በዚህ ጉባኤ ወቅት የተመሠረተዉ። ተመራጭዋ ባደረጉት ንግግር ለአካባቢ ተፈጥሮ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉ መመሪያዎችን ማዉጣት ማለት ልማትን ዘላቂነት ማረጋገጫዉ መንገድ መሆኑን አመልክተዋል። የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሃግብር UNEP ኃላፊ አኺም ሽታይነር በበኩላቸዉ በዓለም የሚታየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ፣ ብክለትና የመሬት ለምነት ማጣትን ጨምሮ ያለዉ የአካባቢ ተፈጥሮ መለወጥ፤ የሚያሳየዉ የዓለም ኤኮኖሚ እንዳዲስ መለወጥ እንዳለበት ነዉ ይህ ካልሆነ ግን የሚጠበቀዉ እድገት ላይሳካ እንደሚችል ነዉ። ሽታይነር እንደሚሉትም የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ከኤኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጋ በቀጥታ የተገናኘ እንደመሆኑ የአካባቢ ተፈጥሮን ለመጠበቅ መተባበር እንደሚገባ የዓለም መሪዎች በሚገባ ተረድተዋል።

Achim Steiner, Direktor des UN-Umweltprogramms UNEP
ምስል picture alliance/dpa

በዚህ ዉስጥም ለመጀመሪያ ጊዜ እያንዳንዱ የተመድ አባል ሃገር ይወከላል። ይህም ሕጋዊነቱን ከፍ በማድረግ የእያንዳንዱ ድምፅ የሚደመጥበት መድረክ እንደሚሆንም ተስፋ ተጥሎበታል።

በተመረጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግርም፤ የሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም ዘላቂ ልማትን ለማሳካት፣ የአየር ንብረት ለዉጥንና ሌሎች ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮችን በሚመለከት የግንዛቤ ለዉጥ ለማምጣት ለጉባኤዉ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን አመልክተዋል። በተለይ አሁን በምንገኝበት መሠረታዊ ነገሮች ማለትም በየቦታዉ የዉሃና ጥሬ ሃብቶች ፍላጎት በናረበት ጊዜ አንዲት ዓለም ብቻ ሳይሆን አምስት ፕላኔቶች ሊያስፈልጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ማሳየት የፈለጉትም ዓለም ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡና በጥንቃቄ የመጠቀሙ ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑን ነዉ። የኬንያ የአካባቢ ተፈጥሮ፣ የዉሃና የተፈጥሮ ሃብቶች ሚኒስትር ጁዲ ዋኩንጉም በበኩላቸዉ ስለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ሊደረጉ የሚገባቸዉ የመፍትሄ ሃሳቦች ከሁሉም አቅጣጫ መምጣት እንደሚኖርባቸዉ በማስገንዘብ የአባላትን ሙሉ ተሳትፎ ጋብዘዋል። በአካባቢ ተፈጥሮ ረገድ አሁን እየተባባሰ ለሚታየዉ ችግርም እንደአንድ ዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ በጋራ ለችግሮቹ ተገቢዉን መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የUNEP የበላይ ኃላፊ አኺም ሽታይነር የUNEA ምሥረታ ምንነትን እንዲህ ያስረዳሉ፤

Symbolbild - Kohlekraftwerk China
ምስል picture-alliance/dpa

«ዛሬ በ21ኛዉ ክፍለዘመን መጀመሪያ ስለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ማሰብ ማለት ወደፊት አስር ቢሊዮን ህዝብ ራሱን የሚመግብበትን ስልት መተለም ማለት ነዉ፤ ይህም ማለት ለአስር ቢሊዮን ህዝብ በአካባቢዉ ያለዉን ተፈጥሮ ሳናወድም የኤሌክትሪክም ሆነ ሌላ የኃይል ምንጭ ማቅረብ ማለት ነዉ። ይህም ኤኮኖሚያችንን በማሸጋገር ስለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆረዉን ማኅበረሰብ ስለኤኮኖሚዉ ይበልጥ እንዲያዉቅ ማድረግ ወይም በተመሳሳይ ያለዉን ግንዛቤ ይዞ ሰዎች የአካባቢ ተፈጥሮን በመጠበቅ ረገድ ሚና እንዳላቸዉ ማስገንዘብ ነዉ። የአካባቢ ተፈጥሮን ጉዳይ የሚመለከተዉን ማኅበረሰብ ስናስተባብር ይህ ነዉ ቅድሚያ የሚይዘዉ ጉዳይ።»

ምንም እንኳን ህዝቡ የአካባቢ ተፈጥሮን በመጠበቅ ረገድ ሚና አለዉ ቢባልም መንግስታት ብክለትን ለመቀነስ ብዙ ሲጥሩም ሆነ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት ወደአረንጓዴ የኃይል ምንጮች ፊታቸዉን ሲያዞሩ አለመታየቱ የሚካሄዱ ዉይይቶችም ሆነ የሚደረሱ ዉሳኔዎች ተግባራዊ ካልሆኑ እንዴት መሻሻል ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ መቁረጥን አያስከትል እንደሁ የተጠየቁት ሽታይነር ለዉጥ አልታየም ማለት እንደማይቻል ነዉ ያመለከቱት፤

Solarpark in China
ምስል picture-alliance/dpa

«ሳይንቲስት ወይም የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች ከሆንሽ በመሻሻሉ ርምጃ ማዝገም ምክንያት ተስፋ መቁረጥ ቢገጥምሽ ምክንያት አለሽ። አሁን ብለዉ ምናልባት ብናገዉ ትክክል ላይሆን የሚችል ነገር የሚመስለኝ እጅግም ለዉጦች እያየን አይደለም የሚለዉ ነዉ። በሌላ በኩል ባለፉት አስርት ዓመታት ብዙ ነገሮች ተለዉጠዋል። የአካባቢ ተፈጥሮን ከማፅዳት አንስቶ የኃይል ምንጮች አብዮትን ከአስርት ዓመት ተኩል ባነሰ ጊዜ ዉስጥ አይተናል። ባለፈዉ ዓመት ዓለም ከነዳጅ ዘይትና ድንጋይ ከሰል ይልቅ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ገንዘቡን አፍስሷል። እነዚህ ስለአካባቢ ተፈጥሮ በቂ ግንዛቤ በማግኘትና ለዚህ ምላሽ ከሚሰጥ ኤኮኖሚ የሚመጡ መሠረታዊ ለዉጦች ናቸዉ። በተመሳሳይ አሁን የተሰጡት ምላሾች በቂ ናቸዉ የማያስብል የተባባሰ እና የከፋ የአካባቢ ተፈጥሮ ለዉጥ ገጥሞናል።»

እንዲህ ቢሉም ግን አኺም ሽታይነር ለአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታትም ሆነ በአጠቃላይ ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚደረግ ክብካቤ የለም ማለት እንደማይቻል ነዉ ያሳሰቡም። እንደዉም 10 ቢሊዮን ሊሆን ይችላል ተብሎ ወደፊት የሚጠበቀዉ የዓለም ህዝብ ስለሁሉም ዓይነት የተፈጥሮ ሃብት እጥረት በሚወራበት በአሁኑ ወቅት እንዳለ አድርጎ ማሰብና ዕለተ ምፅዓት ነገ ነዉ እንደተባለ መቁጠር እንደማይገባም ጠቁመዋል። ትላልቅና ታዋቂ ከተሞቿ በከፍተኛ የአየር ብክለት እንደተጨነቁ ስለሚነገርላት ቻይና የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ መርሃ ግብር ባለስልጣን ሽታይነር እንዲህ ነዉ ያሉት፤

ENG Timeline Energiewende in Deutschland

«አንዳንዶችን ሊያስገርም ይችላል፤ በቻይና ያለዉ እዉነታ በጣም በከፍተኛ የተበከለ ኤኮኖሚ እና ሀገር ነዉ። በተለያየ መስክ የሚበዘበዙት የተፈጥሮ ሃብቶች፣ የፈጣኑ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በጤና ላይ የሚያስከትለዉ ተፅዕኖ፣ የከተሞች የአየር ብክለት ሁኔታ እና በቅሪተ አፅም ላይ የተመሠረተዉ የኃይል ምንጭ ኤኮኖሚ፤ እነዚህ ፍፁም የአረንጓዴዋ ቻይና ገፅታዎች አይደሉም። ሆኖም ቻይና ወደአረንጓዴ ኤኮኖሚ ለማምራት ያፈሰሰችዉ ሃብት፣ የዘርፉን ስፋትና ጥረቱን ስንመለከት ቻይና በመጪዎቹ ዓመታትና አስርት ዓመታት የፈጠራ ማዕከልነቷን ጨምሮ፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ አዳዲስ ቴክኒዎሎጂዎችና አዲስ ፖሊሲዎቿ ሲታዩ በዚህ ረገድ ከምር ልትወሰድ ይገባል። ባለፈዉ የቻይና ፓርቲ ምክር ቤት ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥንቃቄ ወደሚያደርግ ስልጣኔ መሻገር አለብን በሚል የተደረሰበዉ ስምምነት የማስታወቂያ ወይም የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም። እንደዋና ሃሳብና እንደቻይና ርዕዮተ ዓለም 1,4 ቢሊዮን ህዝብ ላላት ሀገር የልማት ማንቀሳቀሻ ራዕይ ነዉ። እናም በሚቀጥሉት ዓመታት በእርግጥም ቻይና ዘላቂ የልማት አቅጣጫን እንደሚከተል ሀገር ይህ ጉዳይ በኤኮኖሚዉያና በማኅበራዊዉ ፖለቲካ ማዕከላዊ ሥፍራ ይዞ እንደሚታይ እንጠብቃለን።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም ቻይናና ዩናይትድ ስቴትስ ለመቀነስ ቃል የገቡትን የብክለት መጠን ተግባራዊ ለማድረግም ሆነ ዉጤቱን ለማየት ጊዜ ይጠይቃል። ሁለቱ ሃገራት አንዳቸዉ ሌላኛቸዉን እየተፎካከሩ ቀጣዩ የብክለት መጠንን የሚወስነዉ የጋራ ስምምነት በመንግስታት መካከል እንዳይደረስ እንቅፋት መሆናቸዉ አይዘነጋም። የብክለት መጠንን በመቀነስም ሆነ ጽዱ የኃይል ምንጭን በመጠቀሙ ረገድ አዉሮጳ ግንባር ቀደምትነቱን ወስዶ ቢቆይም በኢንዱስትሪ በበለፀጉት ሃገራት መካከል ባለዉ ፉክክር ምክንያት ርምጃዉ አዉሮጳ በመሪነቱ የመቀጠሉ ነገር ማጠያየቁ አልቀረም። ሽታይነር እንደሚሉት ግን አዉሮጳ ልዩ ልዩ ቴክኒዎሎጂን በመፍጠርና ወደገበያዉ በማምጣት ራሱ ተጠቅሞ ሌላዉም እንዲገለገልበት ያደረገበት ጥረቱ እንዳለ ሆኖ በፋይናንስ ቀዉስ ምክንያት ርምጃዉ በመጠኑ መጎዳቱን እሙን ነዉ። ያም ቢሆን ግን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አዉሮጳ ለአረንጓዴ የኃይል ምንጭ ያሳየዉ ዝንባሌና ተግባራዊነቱ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ