1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ኅብረት እና አሚሶም

ሐሙስ፣ ግንቦት 25 2008

የአዉሮጳ ኅብረት ሶማሊያ ለሚገኘዉ የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል «አሚሶም» የመደበዉን በጀት ሰሞኑን መቀነሱ ተሰምቷል። የኅብረቱ የገንዘብ ድጋፍ የመቀነስ ዜና ቢሰማም «አሚሶም» የሶማሊያ ተልዕኮዉን በአንድ ዓመት አራዝሟል።

https://p.dw.com/p/1IySR
AMISOM - Soldaten in Somalia
ምስል picture alliance/AP Photo/Jones

[No title]

የአዉሮጳ ኅብረትይህን ርምጃ የወሰደዉ ማሊ ዉስጥ የሙስሊም ጽንፈኞች እንቅስቃሴ ፤ ናይጀሪያ እና በቻድ ሐይቅ አካባቢ ቦኮሃራም የሚያደርሰዉ ጥቃት በመጠናከሩ እንዲሁም በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ግጭት በመባባሱ መሆኑ ተገልጿል። ኅብረቱ ለ«አሚሶም» ከሚሰጠዉ የገንዘብ ድጋፍ 2o በመቶዉን በመቀነሱም ኬንያ ወታደሮቿን ከተልዕኮዉ ለማዉጣት ዝታለች።

የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ «አሚሶም» ከተፈጠረበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2007ዓ,ም አንስቶ የአዉሮጳ ኅብረት ከአንድ ቢሊየን ዩሮ በላይ መድቧል። ሆኖም አፍሪቃ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጠናከረ በመጣዉ የሙስሊም ጽንፈኞች እንቅስቃሴ ምክንያት ኅብረቱ ለ«አሚሶም» ተልዕኮ የደሞዝ ክፍያ ከመደበዉ 80 በመቶዉን ብቻ ለመስጠት ወስኗል። የአዉሮጳ ኅብረት ዉሳኔ በቀጥታ የአፍሪቃ ኅብረት ኃይሎችን ይነካል። በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች አንዳንዶቹ ወታደሮች ደሞዝ ሳያገኙ ወራት እንደሚያልፉ ያመለክታሉ። የሶማሊያ ጉዳይ ተንታኝ እና በጀርመን የዓለም አቀፍ ምርምር እና የፀጥታ ጉዳይ ጥናት ዘርፍ ኃላፊ አኔተ ቬበር ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ቀሪዉ 20 በመቶ በጀት በአፍሪቃ ኅብረት መሸፈን ይኖርበታል።

Afrika AMISOM Symbolbild African Standby Dorce
ምስል Reuters/A. Wiegmann

«በጣም ዉስብስብ ጉዳይ ነዉ፤ ምክንያቱም ወታደሮችን የሚያዋጡት ሃገራት ለአስተዳደር ወጪዎች በሚል ከወታደሮቹ ደሞዝ ላይ በፐርሰንት ይወስዳሉ። ደሞዛቸዉ ከተቀነሰ በእርግጥም ያ ለወታደሮቹ አስቸጋሪ ነገር ነዉ። ሆኖም ግን ዘመቻዉ እንደነበረዉ መቀጠል የለበትም ማለት አይደለም። በተጨማሪም ቀሪዉ 20 በመቶ ወይ በአፍሪቃ ኅብረት አለያም በተመድ መከፈል አይኖርበትም ማለትም አይደለም።»

በቅርቡ ወደ ሀገሯ ተመልሳ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ለመሆን ያለሙት እና በአሁኑ ጊዜ ፊንላንድ የሚኖሩት ፋዱሞ ዳይቦ በቬበር ሃሳብ ይስማማሉ። እንደእሳቸዉ ገለጻም የ«አሚሶም» በጀትን የመቀነሱ ጉዳይ ገና ፈር አልያዘም፤ የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ራሱንም ቢሆን በርካታ ወራትን ካለደሞዝ ሲያሳልፍ ይታያል።

«ይህ ሁኔታ ይበልጥ ፀጥታን ወደማጣትና ወደአለመረጋጋት ሀገሪቱን እንደሚመራት ይታወቃል። የአፍሪቃ ኅብረት እንዲህ ያለዉ ነገር እንዳይፈጠር የማድረግ አቅም ይኖረዋል ብዬ ከልብ ተስፋ አደርጋለሁ። እናም ይህ ነገር ሶማሊያን ወደአለመረጋጋት እንደማይከታትም ተስፋ አለኝ። ምክንያቱም ደሞዝ የማይከፈላቸዉ እና በአግባቡ ያልተበረታቱ ወታደዎች ካሉ፤ ሶማሊያ ዉስጥ ሊያከናዉኑ የመጡትን በአግባቡ ማከናወን አይችሉም።»

African Union Mission in Somalia
ምስል picture-alliance/dpa/S. Price/Au-Un Ist

ሶማሊያ የሚገኘዉ የአሚሶምጽሕፈት ቤት በተልዕኮዉ ሥር የሚገኙ ወታደሮች ለዘጠኝ ወራት ያለደሞዝ ቆይተዋል የሚለዉን ዘገባ አላረጋገጠም። ሆኖም ግን አንዳንዴ በገንዘብ ሽግግር እና ረዥም ጊዜ በሚወስድ የማጣራት ሂደት የክፍያ መዘግየት መኖሩን ይስማማሉ። የኬንያ ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታ በአፍሪቃ ኅብረት ተልዕኮ ሥር የሚገኙ ወታደሮቻቸዉን ከሶማሊያ ለማዉጣት ዝተዋል። የአዉሮጳ ኅብረት የገንዘብ ድጋፉን እንደሚቀንስ ከመሰማቱ አስቀድሞ ኬንያ በግዛቷ የሚገኘዉን ትልቁን የስደተኞች መጠለያ ዳዳብን ለመዝጋት መወሰኗን አሳውቃለች። ከዓለም ትልቁ መሆኑ በሚነገርለት ዳዳብ 300 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ይገኛሉ። አብዛኞቹም የሶማሊያ ዜጎች ናቸዉ። ፋዱሞ ዳይብ የኬንያ ዉሳኔ እንደረበሻቸዉ ይናገራሉ።

«ከለጋሾች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ይህን መደራደሪያ ማድረጋቸዉ ያሳዝናል። ከለጋሽ ሃገራት ገንዘብ ለማግኘት ሰብዓዊ ችግርን መጠቀም አሳዛኝ ነዉ። የኬንያ አስተዳደር እንዲህ ያለዉን የቅስቀሳ ስልት በተለይ ከለጋሾች ጋር ሲደራደር ያስወግደዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በአካባቢዉ ሰላም ለማስከበር በኅብረቱ የተፈጠረዉ በተመድ ይሁንታ ነዉ። ሲመሠረት የተሰጠዉ የስድስት ወራት ኃላፊነት ነበር፤ ሆኖም ግን ከአስር ዓመታት በኋላም አሁንም አለ። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሊያከትም የነበረዉ የ«አሚሶም» ተልዕኮ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተራዝሟል። ነገር ግን ለህልዉናዉ የሚያስፈልገዉ የበጀት ድጋፉ ጉዳይ መፍትሄ አላገኘም።

ፍሬድ ሙቩኒ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ