1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ኅብረት የአፍሪቃ የስልጠና ዕቅድ

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2007

የአዉሮፓ ኅብረት ለምሥራቅ አፍሪቃ የፀጥታ ተቋማት የፀረ ሽብር ስልጠና ለመስጠት ማቀዱን አመለከተ። በናይሮቢ ኬንያ የኅብረቱ የአፍሪቃ ልዑክ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ትናንት ይፋ እንዳደረጉት የሚሰጠዉ ስልጠና በተለይ ድንበር ዘለል ምርመራዎችና የሽብር ተግባር ተጠረርጣሪዎችን የመክሰስ ሂደት በተጨባጭ መረጃዎች ላይ መመሥረትን ይመለከታል።

https://p.dw.com/p/1Fo96
Europaflaggen vor dem Hauptquartier der Europäischen Kommission in Brüssel
ምስል Reuters/Y. Herman

[No title]

ሥልጠናዉ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ ወይም በመጪዉ ዓመት መባቻ ላይ እንደሚጀመር ይጠበቃል። ምሥራቅ አፍሪቃ ለአደገኛ የአሸባሪዎች ጥቃት የተጋለጠ መሆኑን በማመልከት ነዉ ለአካባቢዉ የፀጥታ ተቋማት የፀረ ሽብር ስልጠና ለመስጠት ያቀደዉ የአዉሮጳ ኅብረት። ሮይተርስ እንደሚለዉ ምዕራባዉያን ኃይሎች ቀደም ሲልም ፅንፈኛ ሙስሊምነት እንዳይንሰራፋ መከላከል ይችላሉ ያሏቸዉን የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የፀጥታ ኃይሎች አሰልጥነዉ አስታጥቀዋል። አዲሱ የአዉሮጳ ኅብረት የስልጠና መርሃግብር በተለይ ሕግ አስፈፃሚ ኃይሎች በሽብር ተግባር የሚጠረጠሩ ሰዎችን ጉዳይ ድንበር ዘልለዉ እንዴት መመርመርና ለክስ ማቅረብ እንደሚችሉ ለማሰልጠን ያቀደ ነዉ። በናይሮቢ የአዉሮጳ ኅብረት ተልዕኮ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዑቨ ቪሰንባህ ስለመርሃግብሩ ምንነት ያብራራሉ፤

«ይህ የአዉሮጳ ኅብረት በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራትና በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት በራሳቸዉ የፀረ ሽብርና ፅንፈኝነት ዘመቻ ይበልጥ ዉጤታማ መሆን እንዲችሉ የሚደግፍበት ጥቅል መርሃግብር አካል ነዉ። ይህ በያዝነዉ ዓመት ማለቂያ ወይም በሚመጣዉ ዓመት መጀመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን በዕቅድ የተያዘ የስልጠና መርሃግብር በተለይ የሕግ ተርጓሚና አስፈፃሚ አካላት በፍርድ ቤት ሽብርተኛን ለመክሰስ የሚያበቁ የተሻሉ ጠቃሚ መረጃዎችን መሰብሰብ እንዲችሉ ለማድረግ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የሕግ፤ እንዲሁም የጋራ ትብብሮችንና የመሳሰሉትን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ነዉ።»

Kenia Attentat in Garissa
የኬንያ ፖሊሶችምስል picture-alliance/AP Photo

አያይዘዉም የመርሃግብሩ ዓላማ በየሃገራቱ ያሉት የሕግ አስፈፃሚ ኃይሎች ዉጤታማ እንዲሆኑና ከሌሎችም ጋ በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ የሆነዉን የሽብር ተግባር ለመከላከል እንዲሠሩ ለማስቻል መሆኑን ያስረዱት ዑቨ ቪሰንባህ የደህንነት ኃይሎች የሚያገኙትን መረጃ ለምስክርነትእንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ተጨማሪ ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችልም አስተድተዋል።

«የስለላ ኃይሎች ወይም ፖሊሶች መረጃዎችን ያገኛሉ፤ ያን ያገኙትን መረጃን በፍርድ ቤት ሊጠቅም የሚችል ማስረጃ አድርገዉ ለማቅረብ ብዙዉን ጊዜ አቅሙ የላቸዉም። ይህ ማለት ደግሞ ተጠርጣሪን ለሕግ ማቅረብ ማለት ነዉ፤ ግን አብዛኛዉን ጊዜ ተጠርጣሪዉ በነፃ የሚሄድበት አጋጣሚ አለ፤ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ግለሰቡን ጥፋተኛ ብሎ እስር ቤት የሚያስገባበት በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ማለት ነዉ። ይህ ደግሞ የተለያዩ የሕግ አስፈፃሚ አካላትን ይመለከታል፤ ፖሊስን፤ የስለላ አገልግሎትን፤ አቃቤሕግን እንዲሁም ፍርድ ቤትን።»

የአዉሮጳ ኅብረት ያቀደዉ የስልጠና መርሃግብር በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ ወይም በመጪዉ 2016 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጀመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን የታቀደዉ በኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳና እንዲሁም በየመን ነዉ። ኅብረቱ ይህን ዓይነቱን የስልጠና መርሃግብር በተለይ በዚህ ወቅት በተጠቀሱት ሃገራት ለማካሄድ የፈለገበት የተለየ መነሻ ምክንያት ይኖረዉ ይሆን? ዑቨ ቪሰንባህ መለሱ፤

«አዎ ማለቴ የምናቀርበዉ መርሃግብር ሁሉ የሚመለከታቸዉን ሃገራት ፍላጎት መሠረት ያደረገ እንጂ የአዉሮጳ ኅብረት ብቻዉን በራሱ አቅዶ ወደአፍሪቃ የሚያመጣዉ አይደለም። በሚመለከታቸዉ ሃገራት ቁልፍ ጉዳይ በሚል ተለይቶ የተመረጠ ነዉ። ምክንያቱም እንዲህ ባለዉ ወንጀል ማለትም ሽብርን በሚመለከት ድንበር ዘለል መረጃ የመሰብሰብና ክስ የመመሥረት ልምድና አቅማቸዉ ዉሱን። አዉሮጳ ደግሞ እንደአህጉራዊ ድርጅት በድንበር ዘለል ትብብር ልምድ ያካበተ ነዉ።»

Selbstmordattentate auf Moscheen im Jemen
የሽብር ጥቃት በየመንምስል picture-alliance/dpa/Arhab

የአዉሮጳ ኅብረት ያቀደዉ የስልጠና መርሃግብር ሲጀመር ለሶስት ዓመት የሚዘልቅ ነዉ። ስልጠናዉ ይካሄድባቸዋል ከተባሉት ሃገሮች መካከል ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ለዓመታት በፀረ ሽብር ዘመቻዉ ተሳታፊ ሃገራት መሆናቸዉ ይነገራል። እስካሁን በሚያካሂዱት ዘመቻ ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል? አሁንም ዑቨ ቪሰንባህ፤

«ይህን ለመናገር አስቸጋሪ ነዉ። እኔ የደህንነት ጉዳይ ምሁር አይደለሁም። ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሃገራት ከሌሎቹ ይበልጥ የሽብር ጥቃትና የጥቃት ሙከራ ዒላማ ሆነዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የተለያዩ የጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ ችለዋል፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ። አንዳንዴ ዕድል ነዉ፤ አንዳንዴ ደግሞ በመጨረሻ ሰዓት እነዚህ ሃገራት ባላቸዉ ስልታዊ የሆነ ትብብር ተጠቅመዉ በድንበር አካባቢ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ሊደርሱባቸዉ ይችላሉ።»

በዚህ የስልጠና መርሃግብር ሶማሊያ ያልተካተተችዉ የተጠናከረ የሕግ አስፈፃሚ አካል ስለሌላት እንደሆነ ያመለከቱት በኬንያ የአዉሮጳ ኅብረት ልዑክ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፤ ከአፍሪቃ ተሻግሮ የመን የገባችበት ምክንያት ግን በድንበር ልዩነት ሳይሆን በሚታየዉ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ምክንያት መሆኑንም ጨምረዉ አስተድተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ