1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳው ኅብረት ኢንተርኔት-መረጃ አገልግሎት

ሐሙስ፣ የካቲት 11 1996

የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን ለሚደረጁት ሀገራት በየዘርፉ ከሚመድበው የልማት ርዳታ ጎንለጎን አሁን ለእነዚያው ሀገራት ሸቀጥ-ላኪዎች የአውሮጳውን ገበያ ሁኔታ የሚያሳይ የኢንተርኔት መረጃ አገልግሎትም ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል። ይኸው በኢንተርኔቱ መረብ አማካይነት የሚቀርበው መረጃ፣ የሚደረጁት ሀገሮች ላኪዎች የአውሮጳ ገበያዎችን ሁኔታና የጉምሩክ ሥርዓት አጣርተው እንዲገነዘቡ ለማስቻል ይረዳል።

https://p.dw.com/p/E0fx

የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን ማዕከላዊ መሥሪያቤቱ በሚገኝባት መዲና ብሩክሴል በይፋ የሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ወደፊት ለሚደረጁት ሀገሮች በሚመደበው የልማት ርዳታ ረገድ በይበልጥ የተፍታታ ሁኔታ ተፈጥሮ፣ በየጊዜው ለሚቀያየሩት ፍላጎቶችና አዳዲስ ዓለምአቀፍ የመፍትሔ ሐሳቦች፣ በየጊዜው ለሚከሰቱት ውዝግቦችም የተለየው ትኩረት የሚሰጥ ይሆናል። የአውሮጳው ኅብረት በልማት ርዳታ አሰጣጡ ሥርዓት ረገድ ያንቀሳቀሰው ይኸው አዲስ ሐሳብ፣ በመጭው ግንቦት ከልማት ትብብር ተጣማሪዎቹ የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(አከፓ) ሀገሮች ጋር በሚጀመረው ድርድር አኳያ ነው የሚታየው። በግንቦቱ የድርድር ጉባኤ ላይ የ”ኮቶኑ” ስምምነት ነው ፍተሻ የሚደረግበት። እ.ጎ.አ. በ፪ሺ ዓ.ም. በበኒን ርእሰከተማ ኮቶኑ ስለተፈረመ “ኮቶኑ-ስምምነት” ተብሎ የሚጠራው የትብብር ሠነድ፣ በየአምስት ዓመታት ነው ፍተሻና ግምገማ የሚደረገበት። የዚሁ ድርድር መጀመሪያ ዙር በየካቲት ፲፱፻፺፯(ወይም እ.ጎ.አ. በ2005) የሚያበቃ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። የአውሮጳው ኅብረት ሚኒስትሮች-ምክርቤት ይህንኑ ኮሚሲዮኑ ያንቀሳቀሰውን ሐሳብ ተወያይቶበት፣ ኅብረቱ ለግንቦቱ ድርድር የሚያቀርባቸውን ነጥቦች በቶሎ መወሰን አለበት።

የአውሮጳው ኅብረት የልማት ጉዳይ ተጠሪ ፓውል ኒልሶን እንደሚሉት፣ “ኮቶኑ ስምምነት” በአውሮጳው ኅብረትና በአከፓ-ሀገሮች መካከል ላለው ግንኙነት ዘመናዊና ጠንካራ መሠረት ነው የሚሰጠው፤ ከዚህም በላይ የአውሮጳው ኅብረት ለሚደርሳቸው ለሌሎቹ ዓለምአቀፍ ውሎች ዓይነተኛ አርአያ ነው የሚሆነው።
.-.
የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን፣ የሚደረጁት ሀገሮች የሚደርስባቸው የኤክስፖርት ገቢው ጉድለት በልዩ ድጎማ እንዲመዛዘን የሚደረግበትም ርምጃ እንዲሻሻል ነው የሚፈልገው። በኮሚሲዮኑ ዕቅድ መሠረት፣ በኤክስፖርቱ ገበያ ላይ በሚደርሰው የዋጋ ውዥቀት ምክንያት የኤክስፖርቱ ገቢ ለሚጓደልባቸው አዳጊ ሀገሮች ማካካሻውን ክፍያ መመደብ ይኖርበታል። ለዚሁ የኤክስፖርት ገቢ ድጋፍ አስፈላጊ የሚሆነውን ርምጃ ሠነድ ሁለቱ የኮሚሲዮን አባላት--ማለት የልማትና የንግድ ጉዳይ ተጠሪዎች ፓውል ኒልሶንና ፓስካል ላሚ ሰሞኑን ብሩክሴል ውስጥ በይፋ አቅርበውታል። በዚህም መሠረት፣ የኤክስፖርቱ ገቢ ርጉእ የሚሆንበት ሥርዓት ነው የሚፈጠረው። የኤክስፖርት ገቢውን ጉድለት ለማካካስ የሚያስችለው ይኸው የልዩ ክፍያ ሥርዓት፣ የአውሮጳው ኅብረት በአሕጽሮት “አከፓ” ከሚሰኙት የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ጋር በኮቶኑ የደመደመው ውል ካሰፈራቸው ነጥቦች አንዱ ነው።

የ”ኮቶኑው ስምምነት” ከተደረሰ ወዲህ፣ በዋጋ ውዥቀት ምክንያት ለደረሰባቸው የኤክስፖርት ገቢ ጉድለት ማካካሻውን ክፍያ ለማግኘት መሥፈርቱን አሟልተው የተገኙት አከፓ-ሀገሮች ስድስት ብቻ መሆናቸውንና ለዚሁ የድጋፍ ርምጃ ፴፭ ሚሊዮን ኦይሮ መመደቡን አስቀድመን የጠቀስናቸው የኮሚሲዮኑ የልማት ጉዳይ ተጠሪ ፓውል ኒልሶን ገልፀዋል። በአዲሱ መሥፈርት መሠረት ግን፣ ወደፊት ፶፩ የሚደረጁ ሀገሮች ለኤክስፖርቱ ገቢያቸው ጉድለት ማካካሻ ፪፻፶፭ ሚሊዮን ኦይሮ ሊያገኙ እንደሚችሉ ነው የሚታሰበው። ይኸው ማካካሻ ክፍያ በተለይም ከጥጥና ከሌሎችም የግብርና ውጤቶች ሽያጭ የሚገኘው የኤክስፖርቱ ገቢ ከውዥቀት እንዲድን ለማድረግ የሚያስችል ነው።

ሌላው የስምምነት ይዘት፣ አፍሪቃ ውስጥ የጥጥን ምርት ለማነቃቃት እንዲያስችል የተዘረጋውን የተግባር ዕቅድ የሚመለከት ነው። በዓለም የጥጥ ገበያ ላይ እየተቀነሰ የሄደው የዋጋው ደረጃ በተለይ በምዕራብና በማዕከላይ አፍሪቃ ከባድ ችግርን ነበር የፈጠረው። በግምት ፲ ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪቃውያን ናቸው ኑሮአቸውን በጥጥ ምርት ሽያጭ የሚደግፉት። እንደ ቤኒን፣ ማሊና ቻድ በመሳሰሉት እጅግ ኋላቀር ሀገሮች ውስጥ የጥጡ ወጭ-ንግድ ነው ዋና የገቢ
ምንጭ የሚሆነው። የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን የንግድ ጉዳይ ተጠሪ ፓስካል ላሚ እንደሚሉት ከሆነ፣ ኅብረቱ ከአፍሪቃ ለሚላኩት የጥጥ ሸቀጦች መላውን የንግድ ግደባዎች አስወግዷል፤ ግን የአፍሪቃ ጥጥ-ለኪዎች በመንግሥታዊ ድጎማ ከረከሰው ከአውሮጳው ጥጥ ጋር የገበያ ውድድር የሚያደርጉበት አቅም ያላቸው ሆነው አይታዩም። ስለዚህ ከንግድ ግደባው ውገዳ ጎን ለጎን ድጎማውም የሚወገድበት ርምጃ ነው እውን መሆን ያለበት።

.-.

የአውሮፃው ኅብረት ኮሚሲዮን አሁን በኢንተርኔቱም መረብ አማካይነት ነው የሚደረጁት ሀገሮች በአውሮጳው ገበያ ላይ ለሚያቀርቧቸው ምርቶቻቸው የሽያጭ ዕድል እንዲያገኙ ለመርዳት ዝግጁ የሆነው። የኮሚሲዮኑ የንግድ ጉዳይ ተጠሪ ፓስካል ላሚ እንደሚሉት፣ የሚደረጁት ሀገሮች በዚያው በኢንተርኔቱ መረብ አማካይነት ለምሳሌ ስለ ጉምሩክ ድንጋጌና ስለ ሸቀጦች ሁኔታ አስፈላጊውን መረጃ ያገኛሉ፤ ከዚህም በላይ ወደፊት ገቢውን ንግድ ስለሚመለከቱ ድንጋጌዎች--ለምሳሌ ስለ ንጽሕና አጠባበቅና ስለ እፀዋት እንክብካቤ የሚሰጡት መመሪያዎች በኢንተርኔቱ መረብ ግልጽ ሆነው እንዲቀርቡ ይደረጋል።

በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ያሉት ሸቀጥ-ላኪዎች በበኩላቸው፣ የኢንተርኔቱ መረብ ዝግጁ በሚያደርግላቸው መረጃ አማካይነት የአውሮጳውን ገበያ እንዲደርሱበት ዕድል ያገኛሉ። የንግዱ ተጠሪ ላሚ በሚሰጡት ማስገንዘቢያ መሠረት፣ የንግድ መድልዎው ድንጋጌ ባሁኑ ጊዜ ከሚደረጁት ሀገሮች ወደ አውሮጳው ገበያ ከሚሸጋገሩት ሸቀጦች መካከል ለግማሹ ብቻ ነው ጠቀሜታ የሚሰጠው። ወደፊት ግን፣ ሸቀጥ-ላኪዎቹ አዳጊ ሀገሮች በአውሮጳው ገበያ ላይ የትኛው የሽያጭ ዕድል እንዳላቸው ወይም ሊኖራቸው እንደሚችል መረጃ የሚያቀርበው የኢንተርኔቱ መረብ ግልጽ ያደርግላቸዋል ነው የሚባለው። በፓስካል ላሚ አመለካከት መሠረት፣ የሚደረጁት ሀገሮች በሥነቴክኒኩ እመርታ ረገድ አሁንም ኋላቀር እንደሆኑ የሚገኙ ቢሆንም ቅሉ፣ እዚያም ቢሆን መረጃውን በሰፊው አድማስ ለማሰራጨት የኢንተርኔቱ መረብ ነው ከፍተኛውን ዕድል የሚደቅነው።

የአውሮጳው ኅብረት ራሱ እንደሚለው ከሆነ፣ ወደ አውሮጳው ገበያ ከሚሸጋገሩት ሸቀጦች መካከል ፵ በመቶ ያህሉ ከሚደረጁት ሀገሮች የሚመጡ ናቸው። እ.ጎ.አ. በ2002 ከ፸፯ የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(አከፓ)ሀገሮች በ31 ሚሊያርድ ኦይሮ ወደ አውሮጳው ገበያ የተላኩት ሸቀጦች በብዛት ከጉምሩኩ ቀረጥ ነፃ ነበሩ ይላል የብሩክሴሉ መግለጫ። እጅግ ድሆች ከሚባሉት ፵፱ ሀገሮች ደግሞ፣ በዚያው ጊዜ ውስጥ 2.2. ሚሊያርድ ኦይሮ ያስወጡ ሸቀጦች ወደ አውሮጳ እንደተሸጋገሩም ነው የተመለከተው። ከእነዚሁ ከ፵፱ኙ እጅግ ኋላቀር ሀገሮች ለሚላኩት አብዛኞቹ ሸቀጦች የጉምሩክ ነፃነት እንዲኖር የአውሮጳው ኅብረት ከ፫ ዓመታት በፊት ነበር ድንጋጌውን የደረሰው። የአውሮጳው ኅብረት በኢንተርኔቱ መረብ ኣማካይነት ለላኪዎቹ አዳጊ ሀገሮች የሚጋብዘው የመረጃው አገልግሎት ለልማቱ ትብብር ከፍተኛ ክብደት የሚሰጠው ሆኖ ነው የሚታየው።