1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ባንኮች ስጋት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 6 2008

በጣልያን፤ጀርመንና ብሪታኒያ የሚገኙ ባንኮች የቀውስ ሊገጥማቸው እንደሚችል ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። የጀርመኑ ዶይቼ ባንክ ቀውስ እስካሁን መፍትሔ ያልተገኘለት ሲሆን ጣልያን ባንኮቿን ለመታደግ ጭንቅ ውስጥ ገብታለች።

https://p.dw.com/p/1JOOI
27.10.2014 DWiItalien, Monte dei Paschi, Banken

የአውሮጳ ባንኮች ስጋት

የጣልያኑ ባንኮ ሞንቴ ዴ ፓስኪ ዲ ሳያና የአክሲዮን ዋጋ 14 በመቶ አሽቆልቁሎ ባለፈው ሳምንት አንድ አክሲዮን በ0.29ሳንቲም እየተሸጠ ነበር። በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ይህ ባንክ ከአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ተገቢ ላልሆነ ብድር ያለውን ተጋላጭነት እንዲያስወግድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።

በጎርጎሮሳዊው 1472 ዓ.ም. የተመሰረተውና እድሜ ጠገቡ ባንኮ ሞንቴ ዴ ፓስኪ ዲ ሳያና 46.9ቢሊዮን ዩሮ (55.2 ቢሊዮን ዶላር) የማይንቀሳቀስ ብድር አቅርቧል። የአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ይህ የገንዘብ መጠን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 32.6ቢሊዮን ዩሮ ዝቅ እንዲል በባንኩ ላይ ጫና እያሳደረ ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF)በበኩሉ በጣልያን ባንኮች ላይ እያንዣበበ የሚገኘውን የቀውስ ስጋት ለማስወገድ አገሪቱ ኤኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለባት ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም የጣልያን ኢኮኖሚ ከጎርጎሮሳዊው 2008ዓ.ም. የኤኮኖሚ ቀውስ በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2020አጋማሽ መታገስ እንዳለበት አስታውቋል።

Italien Unicredit-Gebäude in Mailand
ምስል picture-alliance/dpa/D. Dal Zennaro

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በአውሮጳ ኅብረት ሦስተኛ ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት ለሆነችው ጣልያን ከዚህ ቀደም ያስቀመጠውን ቅድመ-ትንበያም ከልሷል። በጎርጎሮሳዊው 2016ዓ.ምየጣልያን ዓመታዊ የምርት መጠን እድገት1.1% ይደርሳል ብሎ የነበረው ተቋም አሁን ግን ከአንድ በመቶ በታች ይሆናል ሲል ከልሷል። ለጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም የተሰጠው ቅድመ ትንበያ አንድ በመቶ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ነው።

የኤኮኖሚ ባለሙያዎችም ይሁኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጣልያን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ግሪክ በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም የነበረችበትን ይመስላል እያሉ ነው። ጀርመናዊዉ ፕሮፌሰር ሐንስ ፒተር በርግሆፍ በሖኸንሐየም ዩኒቨርሲቲ የባንክ ባለሙያ ናቸው።

«ችግሩ ያለው ተገቢ ባልሆኑ ብድሮች ላይ ነው። በባንኮቹ የአክሲዮን ዋጋ ላይ አይደለም። ይህ ደግሞ በጣልያን ኩባንያዎች ላይ ይንጸባረቃል። ጣልያን በታሪኳ ግዙፍ እና ጠንካራ ኩባንያዎች ያሏት አገር ነች። ኩባንያዎቹ ደግሞ እንደ ሙስና ያሉ የመንግስት አስቀያሚ ተግባራትን ተቋቁመው መዝለቅ ችለዋል-በተለይም በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል። ባለፉት ጥቂት አመታት ግን እነዚህ ኩባንያዎች እጅጉን እየተዳከሙ በመሄድ ላይ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ ሲዳከሙ ደግሞ ብድሩን ባቀረቡት ባንኮች ላይ ጫናው ተመልሷል።»

የጣልያን ባንኮች የቆሙበት የቀውስ አፋፍ ለአገራቸው መንግስት ብቻ ሳይሆን ለመላው አውሮጳ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። ቀውስ የሚያሰጋቸውን ባንኮች ለመታደግ አውሮጳ 150ቢሊዮን ዩሮ ወይም 166 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያውፈልጋት የዶይቼ ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ባለፈው እሁድ ተናግረው ነበር። ዴቪድ ፎልከርትስ ላንዳው ቬልት አም ሶንታግ ከተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ «አውሮጳ እጅጉን ታሟል። በአፋጣኝ ለችግሮቹ መፍትሔ ማፈላለግ ይኖርበታል። አለበለዚያ አደጋ ይኖራል።»ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ኤኮኖሚስቱ የአውሮጳ ባንኮችን ለመታደግ የሚያስፈልገው ገንዘብ አብዛኛው ለጣልያን መሆኑንም አልሸሸጉም። እስካሁን ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁትን የግሪክ ባንኮች በገንዘብ ሲደግፍ ለቆዩት አውሮጳውያን ጣልያንን ማገዝ ቀላል የሚሆን አይመስልም። አሁንም

«እኔ እጅግ በጣም አደገኛ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ጣልያን በጣም ግዙፍ አገር ነች። በግሪክ የተፈጠሩ በርካታ ነገሮችም በይሁንታ ተቀብለናል። ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ አድርገናል። ምንም ነገር ሳንቀይር የባንክ አገልግሎቱን ታድገናል። ያ ግን እጅግ አነስተኛ የባንክ አገልግሎት ነበር።» የሚሉት ፕሮፌሰር ሐንስ ፒተር በርግሆፍ «ጣልያን ግዙፍ ኩባንያዎች እና ግዙፍ የባንክ አገልግሎት ያሉት ትልቅ አገር ነው። እናም አውሮጳውያን ያንን ለሚያክል አገር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ዋጋው የከፋ ይሆናል።»ሲሉ ያክላሉ።

ለመሆኑ የጣልያን ባንኮችን ማን ሊታደጋቸው ይችላል? የአውሮጳ ኅብረት በቅርቡ ሥራ ላይ ያዋለው ሕግ የከሰሩ ባንኮችን መታደግ ያለባቸው አበዳሪዎቻቸው እንጂ ግብር ከፋዩ አይደለም ሲል ደንግጓል። ከዚህ ቀደም የአውሮጳ ኅብረት እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋማት ለግሪክ ለሦስት ጊዜ እንዲሁም አየርላንድ፤ ፖርቱጋል፤ ቆጵሮስ እና የስፔን ባንኮችን በገንዘብ መርዳታቸው አይዘነጋም። ጣልያን ባንኮቿን ከቀውስ መታደግ ብትሻም ያን ማድረግ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ያላት አይመልም።

«አገሮች የመንግስት እዳን በአግባቡ ማስተዳደራቸው እርግጠኛ መሆን አለብን። የአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክም ይህን ከፍተኛ የመንግስት እዳ መሸከም እንዲችሉ ሲያግዛቸው ቆይቷል።» የሚሉት የባንክ ጥናት ባለሙያው « ጣልያን መንግስት እጅግ ከፍተኛ እዳ ካለባቸው አገሮች አንዷ ናት። ይህንን ለመክፈል የሚያስል የገንዘብ አቅም በመንግስት ግምጃ ቤት የለም። የአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ይህንን ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። በጥንቃቄ መመልከት ያለብን ይህ ለአውሮጳ ምን ማለት ነው የሚለውን ነው። አሁን የምንሄድበት መንገድ ካሁን በፊት ወደ ተከሰተው የኤኮኖሚ ቀውስ አይነት መልሶ ሊመራን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በጣልያን የሚከሰት የባንኮች ቀውስ ለአህጉሩ በመላአስጊ ይሆናል።»በማለት ያስጠነቅቃሉ።

Deutschland Deutsche Bank Schriftzug Symbolbild Verluste
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

በአንድ ወቅት የጀርመን የኩራት ምልክት የነበረው ዶይቼ ባንክም ከገባበት የቀውስ ቁልቁለት አልተመለሰም። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለመላው ዓለም የገንዘብ ተቋማት ስጋት ሆኗል ሲል አስጠንቅቋል። ባንኩን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በአክሲዮን ገበያዎች የባንኩ ድርሻ ያለው ዋጋ አልተሻሻለም። ዶይቼ ባንክ አሁን በብሎምበርግ 100 ምርጥ ባንኮች ውስጥ የለበትም። ይህ ለጀርመን ብቻ ሳይሆን ለአውሮጳ ኅብረት የገንዘብ ተቋማትም አሳሳቢ እንደሆነ ፕሮፌሰር ሐንስ ፒተር በርግሆፍ ይናገራሉ።

«የጀርመን ግዙፍ ኩባንያ ነው። ይህ ደግሞ በአውሮጳ ኤኮኖሚ ቁልፍ ሚና አለው ማለት ነው። ከመላው ዓለም የገንዘብ ተቋማት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። በጀርመን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፍ አላቸው። አዲስ የተሾሙት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆን ክራየን ከአሮጌው አሰራር ጋር የተሳሰሩ አይደሉም። የባንኩ የመዋዕለ-ንዋይ ሥራ ከፈጠራቸው ስህተቶች ጋርም ግንኙነት የላቸውም። ስለዚህ ለባንኩ መጻዒ ጊዜ ብቻ ሲሉ ካለው አሰራር ጋር ትግል ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። ባንኩን ለመታደግ የሚሰሯቸው ስራዎች ቆራጥ መሆን አለባቸው። ስራዎቹም በፍጥነት ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል። የሚከተሉት ሥልት ግን ምርጥ አይደለም። የድርጅቱን ግዝፈት እና የሥራውሎች መቀነስ አለባቸው። ሰራተኛም መቀነስ ይኖርባቸዋል። ይህ ቀላል አይደለም።»

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚነጉዱ ቱጃሮች እና ድርጅቶቻቸው ገንዘብ ትርፋ የሆኑት የብሪታኒያ ባንኮችም ስጋት ገብቷቸዋል። ባንኮቹ ከብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ በኋላ ሌሎች የአውሮጳ ከተሞችን በመቀመጫነት ሊመርጡ ይችላሉ።

በጣልያን ቀውስ ያሰጋቸዋል የተባሉት ዩኒ ክሬዲት እና ባንካ ኢንቴሳ የኩባንያዎቻቸውን ድርሻ በመሸጥ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። ጣልያን በማንኛውም መንገድ ባንኮቿን ለመታደግ የምታደርገው ጥረት የአውሮጳ ኅግጋትን መጣስ አይኖርበትም። የጀርመኑ ዶይቼ ባንክ በበኩሉ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 7,800ክሶች ይጠብቁታል። የዶይቼ ቬለ የቢዝነስ አርታዒ ሔንሪክ ቦሒም ክሶቹን በሁለት ይከፍላቸዋል። አብዛኞቹ በቀላሉ መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ቅጣት የሚያስከትሉ በማለት። ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት መወሰኗ ለባንኩ የምሥራች ሳይሆን አይቀርም። ዶይቼ ባንክ የአውሮጳ ኅብረትን ፍላጎት መሙላት የሚችል ግዙፍ ባንክ ነውና።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ