1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት የድርድር መመሪያ ጸደቀ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21 2009

ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ዛሬ የተገናኙት 27ቱ የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትወጣበትን የመደራደሪያ ሐሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።

https://p.dw.com/p/2c8ZL
Brüssel EU Gipfel Brexit Verhandlungen
ምስል Reuters/V. Mayo

Q&A EU deal on Brexit - MP3-Stereo

ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ዛሬ የተገናኙት 27ቱ የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትወጣበትን የመደራደሪያ ሐሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።  የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ ባለፈው መጋቢት ያቀረቡት የድርድር መመሪያ  ከ15 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዛሬ መፅደቁ ተሰምቷል። በዛሬው የኅብረቱ ጉባኤ ላይ ግን ፈታኝ ድርድር የሚጠብቃቸው የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒሥትር ቴሬሳ ሜይ አልተገኙም። ብሪታኒያ ከምታደርገው ምርጫ በኋላ ወዲያውኑ ይጀመራል የተባለው ድርድር ከሁለት አመት ገደማ በኋላ በጎርጎሮሳዊው መጋቢት 29 ቀን 2019 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ ውጥን ተይዞለታል። መሪዎቹ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሥምምነት ሳይደረስ ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ወደ ፊት በሚኖራት ግንኙነት ላይ ምንም አይነት ውይይት አይኖርም ብለዋል። «ስለወደፊቱ ከመምከራችን በፊት ያለፈውን መልክ ልናበጅለት ይገባል» ያሉት ዶናልድ ቱስክ ድርድሩን «በቀና ልብ ነገር ግን በከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን» ብለዋል።

Brüssel EU Gipfel Brexit Verhandlungen Tusk
ምስል picture-alliance/dpa/M. Meissner

ዛሬ የጸደቁት መመሪያዎች ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት ላይ ከድርድሩ ጎን ለጎን ለመወያየት የነበራት ተስፋ ላይ ውሀ የሚቸልስ ነው ተብሏል። የቤልጅየሙ ጠቅላይ ሚኒሥትር ቻርለስ ሚሼል የብሪታኒያ መንግሥት 27ቱን አባል አገራት ለመከፋፈል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ሊያደርግ ስለሚችል ሊፈጠር የሚችለውን ወጥመድ ልናስወግድ ይገባል ብለዋል። መሪዎቹ የብሪታኒያ ግዛት የሆነው ሰሜናዊ አየርላንድ በሕዝበ-ውሳኔ ከአየርላንድ ሪፐብሊክ ጋር ከተቀላቀለ ወዲያውኑ የአውሮጳ ኅብረት አባል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል። በጉባኤው የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒሥትር ኤንዳ ኬኒ ሰሜናዊ አየርላንድ ከአየርላንድ ጋር ከተዋሐደች የአውሮጳ ኅብረት  አባልነቷ እንዲጸድቅ ከመሪዎቹ መተማመኛ ጠይቀዋል።

ብሪታንያ ሕዝበ-ውሳኔ ካደረገች በኋላ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት ጥያቄ  ያቀረበችው የኅብረቱን አንቀጽ 50 በመጥቀስ ነበር። ይኽ ጥያቄ ከቀረበ በኋላ ብሪታንያ ከኅብረቱ እንዴት ነው መውጣት የምትችለው?  የመደራደሪያ ሐሳቦቹ ምንድን ናቸው? ብሪታንያ እና  የአውሮጳ ኅብረት ሲፋቱ በምን ጉዳዮች ላይ መደራደር አለባቸው የሚሉ ነጥቦች ሁለቱ ወገኖችን ሲያነጋግሩ ሰንብቷል።

ኅብረቱ የመደራደሪያ ሐሳቡን ለአባል ሃገራቱ አቅርቦ ከተወያዩበት በኋላ ዛሬ በተደረገው ስብሰባ 27ቱም አባል ሃገራት ከ15 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መመሪያውን ተቀብለው አጽድቀዋል። ለመኾኑ የመደራደሪያ ሐሳቦቹ ምንድን ናቸው? 

ገበያው ንጉሤ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ