1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴታ ውል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 2009

3.6 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዋሎንያ ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አውሮጳውያን ከካናዳ ጋር የሚያደርጉትን ስምምነት መግታት መቻሏ አስገራሚም አነጋጋሪም ሆኖ ነበር የከረመው።

https://p.dw.com/p/2RyoI
Belgien EU Kanada Gipfel CETA Unterschrift
ምስል picture alliance/AP Photo/T. Monasse

የአውሮጳ እና የካናዳ የንግድ ውል አንድምታ


የአውሮጳ ኅብረት እና ካናዳ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በእንግሊዘኛው ምህፃር ሴታ «CETA» የተባለውን አወዛጋቢውን «አጠቃላይ የኤኮኖሚ እና የንግድ ስምምነት»ከትናንት በስተያ ተፈራርመዋል። በአንድ የቤልጂግ ግዛት ተቃውሞ ምክንያት የዘገየው ይኽው ስምምነት እና አድምታው ሲያነጋግር ቆይቷል።  የአዉሮጳ ኅብረት እና ካናዳ ባለፈው እሁድ የተፈራረሙት ሴታ የተባለው ውል ፣ ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ከተፈራረማቸው የንግድ ስምምነቶች አንዱ ነው። ኅብረቱ እንደሚለው ስምምነቱ ከ99 በመቶ በላይ ቀረጥ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎችን በማስቀረት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደውን ንግድ በዓመት በ12 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ ያደርጋል። በህብረቱ አባባል ስምምነቱ ፣ከአትላንቲክ ወዲህ እና ወዲያ ማዶ የሚገኙትን የነዚህ ሀገራት ኤኮኖሚ ያሳድጋል የሥራ እድሎችንም ይፈጥራል። ይሁን እና ከመፈረሙ በፊት በ28 ቱም የአውሮጳ ኅብረት አባላት መጽደቅ የነበረበትን ይህን ስምምነት የቤልጂግዋ የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ደቡባዊቷ ግዛት ዋሎንያ አጥብቃ በመቃወምዋ  የቤልጂግ መንግሥት ስምምነቱን ማጽደቅ ተስኖት ከህብረቱ ጋር ለዓመታት ድርድር የተካሄደበት ውል ተገቶ ቆይቷል። 3.6 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዋሎንያ ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አውሮጳውያን ከካናዳ ጋር የሚያደርጉትን ስምምነት መግታት መቻሏ አስገራሚም አነጋጋሪም ሆኖ ነበር የከረመው። የዋሎንያ ግዛት ተቃውሞ በጥቅሉ ሲታይ ውሉ የግዛቲቱን ገበሪዎች ጥቅም ይጎዳል፤  ሉዓላዊነት የሚጋፋ አስገዳጅ ህጎችንም ይጭናል የሚል ነው ። ይህን የምትለው ደግሞ የሃብታዋ ምንጭ የነበሩት ኢንዱስትሪዎቿ እየተዳከሙ የሄዱት እና ከሌላው የቤልጂግ ግዛት ጋር ሲነጻጸር ኤኮኖሚዋ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዋሎንያ ብቻ አይደለችም ። ውሉ የሸማቾችን ማህበራዊ ጥቅሞች አያስከብርም ለአካባቢ ጥበቃ ከለላ አይሰጥም የሚል ስጋት ያደረባቸው አውሮጳውያን ጥቂት አይደለሉም ። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ የዋሎንያዎች እና የሌሎችም የስምምነቱ ተቃዋሚዎችን ጥያቄዎች በሁለት ይከፍላቸዋል።ቀረጥ እና ሌሎች ወጪዎች ውሉም ባይኖር በጣም ዝቅተኛ ናቸው የሚሉት የስምምነቱ ተቃዋሚዎች ስምምነቱ የምግብ ደህንነትን ጨምሮ የአውሮጳ ሸማቾችን መብቶች ይጋፋል ፣ ሲሉ ይከራከራሉ ።ከዚሁ ጋር  ፣ኪሳራን ፣ሥራ አጥነትን እና ግለሰቦች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉዳቶችን በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚጋብዝ ነው ሲሉም ይተቹታል። የአውሮጳ ኅብረት ግን ይህን አይቀበልም። የህብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ የችግሩ መንስኤ የነጻ ንግድን ትርጉም በደንብ የተረዳው ጥቂት ብቻ መሆኑ ነው ይላሉ ።
«ነፃ ንግድ እና ዓለም ዓቀፍ የምጣኔ ሀብት ትስስር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት እና ከረሀብ ጠብቋል ። ችግሩ ይህን የሚያምኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው ነፃ ንግድ እና ዓለም ዓቀፍ የምጣኔ ሀብት ትስስር ሰብዓዊነትን እና ግጭትን ይከላከላል። ችግሩ  ይህን የሚረዱት ጥቂቶች ናቸው። በሴታ ስምምነት ላይ የተነሳው ውዝግብ ፣ነፃ ንግድ ስለሚያሳድራቸው ትክክለኛ ተጽእኖዎች ለህዝቡ ሀቀና እና አሳማኝ መረጃዎችን መስጠት ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያሳያል።»የውሉ ዓላማ የትላልቅ የንግድ ድርጅቶች እና የድንበር ዘለል ኩባንያዎችን ጥቅም ማስጠበቅ ነው  የሚል ተቃውሞም ይቀርብበታል። የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እንዳሉት ግን ስምምነቱ ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ለአንዱ ወገን በተለይም ሀብታሞችን ብቻ ለመጥቀም ያለመ አይደለም።   « ሰፊ የገበያ እድል ፣ ተጨማሪ የኤኮኖሚ እድገት እና ጠንካራ የስራ እድል ፈጠራ ለካናዳ መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል እና ለሌላውም ህብረተሰብ መልካም ዜና ነው ። ካናዳውያን እና አውሮጳ ውያን ከዚህ በተጨማሪ እድገታችን ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት ሲሉ ይስማማሉ። ከእድገቱ የሚገኙት ጥቅሞች ለሀብታሞቹ ዜጎቻችን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም መዳረስ አለበት። እኛ ለካናዳውያን እና ለአዉሮጳውያን ሠራተኖች ተጨማሪ እድሎችን በመፍጠር፣ይበልጥ አሳታፊ እና ተራማጅ ኤኮኖሚ ላይ የሚያደርስ ጎዳና ነው የያዝነው ።የዋሎንያ ተቃውሞ የአውሮጳ ኅብረት እና የካናዳ የንግድ ውል ሳይፈረም ለሁለት ሳምንታት እንዲዘገይ አድርጓል። በዚህ ጊዜ ውስጥም ዋሎንያ ከየአቅጣጫው ሲሰነዘርባት የቆየውን ጫና በመቋቋም አጥብቃ የተሟገተችለትን የገበሪዎችዋን ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት ላይ መድረስ ችላለች። ዓለም ዓቀፍ ባለሀብቶችም ፣መንግሥታት ህጎችን እንዲቀይሩ እንዳያስገድዱ የሚከለክሉ ዋስትናዎችም ተሰጥተዋታል። በድርድር አግባቢ ሀሳብ ላይ በተደረሰ በሦስተኛው ቀን ማለትም ባለፈው እሁድ ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች ተፈርሟል ። የዋሎንያ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ፖል ማኜት መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ በሰጡት መግለጫ ውጤቱ የዋሎኖችን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ አይደለም ብለዋል።
«ጥቂት ጊዜ ብንወስድም የደረስንበት ውጤት ለኛ ለዋሎኖች ብቻ ሳይሆን ለመላ አውሮጳውያን ጠቃሚ ነው ።እኛ በትክክል የምንፈልገው ፣ምን ዓይነት ዓለም እንደሆነ ማወቅ መሠረታዊ ጥያቄ ነው ።ደንቦች ያሏት ወይስ የሌሏት ዓለም ነው የምንፈልገ ? ገበያውን በህግ መቆጣጠር እና መምራት እንዲሁም ለዜጎቻችንም ጥበቃ ማድረግ ነው የምንፈልገው። ለዚህም ነው የታገልነው እናም የድካማችንን ዋጋ አግኝተናል ብዬ አምናለሁ ። ምክንያቱም ተሰምተናል አመሰግናለሁ »የዋሎንያዎች ጥያቄ በድርድር መፍትሄ ማግኘቱ ዋልንያዎችንም ሆነ የአውሮጳ ኅብረትን አስደስቷል ። ይሁን እና የውሉ ፊርማ መዘግየቱ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ማስነሳቱ አልቀረም ። የአውሮጳ ኅብረት ከአሁን በኋላ ትላልቅ የንግድ ስምምነቶች ላይ መድረስ መቻል አለመቻሉ እያነጋገረ ነው ። የህብረቱ አሠራር ለወደፊት በታቀዱ ሌሎች ውሎች ላይ ሊያስድር የሚችለው ተጽእኖም እንዲሁ። ገበያው የዋሎንያዎች ተቃውሞ እና ውጤቱ በሁለት መንገድ የሚታይ ነው ይላል።

Belgien Namur CETA Debatte Paul Magnette
ምስል AFP/Getty Images/J. Thys
Flaggen von Kanada und der EU
ምስል picture alliance/dpa/M. Gambarini
Belgien EU Kanada Gipfel Proteste
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/G. Vanden Wijngaert

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ