1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረትና የጀርመን የአፍሪቃ ወታደራዊ ተልዕኮ

ረቡዕ፣ ጥር 14 2006

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ብራሰልስ ቤልጅየም ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚካሄደውን ግጭት ለማስቆም የሚያግዙ ወታደሮችን ለመላክ ተስማምተዋል ። የአውሮፓ ህብረት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዘመቻና የጀርመን የአፍሪቃ ወታደራዊ ተልዕኮ የዛሬው አውሮፓ ና ጀርመን ዝግጅታች ትኩረት ነው ።

https://p.dw.com/p/1AuW5
ምስል Getty Images

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሃይማኖት ግጭት ሰበብ አስከፊ ቀውስ ውስጥ በወደቀችው በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደሮቻቸውን ለማዝመት የወሰኑት ብራሰል ቤልጀየም ትናንት ውስጥ በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ነው ። ሚኒስትሮቹ በተስማሙት መሠረት በአሁኑ ጊዜ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለሚገኙት የአፍሪቃ ህብረትና የፈረንሳይ ወታደሮች ድጋፍ የሚሰጡ ከ500 እስከ 1000 የሚደርሱ የአባል ሃገራት ወታደሮች ይዘምታሉ ። ወታደሮቹ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የዘመቻው ዓላማ 6 ወራት የሚቆይ ጊዜያዊ ድጋፍ መስጠት ሲሆን ወታደሮቹ የሚሰማሩትም በዋና ከተማይቱ በቦንግዊ ና በአካባቢው ይሆናል ። የህብረቱ የማዕከሉ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደሮች ዘመቻ የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርል ቢልድት ከትናንቱ ውሳኔ በኋላ እንደተናገሩት ዘመቻው ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ። « ከመጠን በላይ የተወሳሰበ ሁኔታ ነው ያለው ። ቦንግዊ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የመንግሥት መዋቅር ቢኖርም ከባንግዊ ውጭ ያለውን ግን አናውቅም ፤ወይም በጥቂቱ ነው የምናውቀው ። በደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው ግዙፍ ሰብዓዊ ቀውሶች ውስጥ የሚገኙ በመውደቅ ላይ ያሉ መንግሥታት ናቸው ። ከፊታችን እጅግ ብዙ ሥራ የሚያስፈልጋቸው የሃገር ግንባታዎች ይጠብቁናል ። »የአውሮፓ ህብረት ሚኒስትሮቹ የትናንቱ ውሳኔ ላይ የደረሱት የቀድሞዋ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ አውሮፓውያን አጋሮቿ በሃገሪቱ የተጠናከረ ወታደራዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ባቀረበችው ተደጋጋሚ ጥሪ መሠረት ነው ። ፈረንሳይ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ የርስ በርስ ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ ነበር ወታደሮቿን ወደ ሃገሪቱ ያዘመተችው።

Bundeswehr soll familienfreundlicher werden
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ወታደሮች ሲጎበኙምስል picture-alliance/dpa

በአሁኑ ጊዜ 1600 የፈረንሳይ ወታደሮች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ ይገኛሉ ። ወታደሮቿ የገቡትም የአፍሪቃ ህብረት ኃይል በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እስኪዘምት ወታደሮችዋን ለማሰማራት ለተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ካቀረበች በኋላ ነው ። 4 ሺህ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ የዘመቱት በዚሁ የውሳኔ ሃሳብ መሠረት ነው ። የፈረንሳይ ተደጋጋሚ ጥሪ ትናንት መልስ ቢያገኝም አንዳንድ የህብረቱ አባል ሃገራት ወታደር በመላክ ሳይሆን ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ለመሳተፍ ነው የተስማሙት ። ለምሳሌ ፈረንሳይ ወታደሮቿን በማዘምት ለባረከተችው አስተዋጽኦ የምታወድሳት ጀርመን ወታደሮቿን ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ አታዘምትም ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይይን ማየር እንዲሁም የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዛይበርት ጀርመን በውጊያ በአጥታ እንደማትካፈል ተናግረዋል ። ከዚያ ይልቅ ጀርመን በህብረቱ ወታደራዊ ዘመቻ የማጓጓዣ እንዲሁም አየር ላይ ነዳጅ የሚሞሉ አውሮፕላኖችን ለማቅረብ ነው የተስማማችው ። ከአፍጋኒስታን ውጭ በሚካሄዱ ዓለም ዓቀፍ ዘመቻዎች ውስጥ ጀርመን ተዋጊ ጦር አሰልፋ አታውቅም ። እጎአ በ2011 በሊቢያ ላይ ጣልቃ ገብ ጦር አንዲዘምት የፀጥታው ምክር ቤት በ2011 በወሰነበት ወቅት ጀርመን ድምጿን በማቀብ የድጋፍ ባለመስጠት የቅርብ ወዳጇቿን ቅር ብታሰኝም እስካሁን ድረስ ታዋጊ ጦር አላዘምትም የሚለውን አቋሟን አልቀየረችም ። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዘመቻ ላይ የያዘችው አቋም ከዚህ የተለየ አይደለም ። ስለማዕከላዊው አፍሪቃው ወታደራዊ ተልዕኮ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ቮን ዴር ላየን እንደተነገሩት ጀርመን የምትሳተፈው ትራንስፖርት በማቅረብና ና የህክምና እርዳታ በመስጠት ነው ።

EU Deutschland Außenminister Frank-Walter Steinmeier in Brüssel
ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርምስል DW/B. Riegert

ሚኒስትሯ እንዳሉት ጀርመን እነዚህን ድጋፎች ማቅረቧ ተፈላጊ ነው ። እርዳታዎቹ የጊዜ ገደብ ስይደረግባቸው ሊቀጥሉ ይችላሉ ። ይሁንና እስካሁን ጀርመን ቃል ስለገባችው እርዳታ ያን ያህል ፍላጎት አልታየም ። የጀርመን ፌደራዊ ሪፐብሊክ የስንቅና ትጥቅ እርዳታ ለመስጠት ለፈረንሳይ መንግሥት ቃል ከገባ ቆይቷል ። ከዚሁ ጋርም ዘማች ወታደሮችና ቁሳቁሶችን የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጎረቤት ወደ ሆኑ ሃገራት ለማድረስም ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል ። ጀርመን ፈቃደንነቷን ብታሳውቅም ለትብብሯ እስካሁን መልስ የሰጠ እንደሌለ የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል ። ሆኖም መንግሥት እስካሁን ድረስ ከፈረንሳይ ጋር የቅርብ ግንኙነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ይናገራል ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ደግሞ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጀርመን ወታደሮችን ታሰልፋለች ብሎ አይጠብቅም ፤ ሃገሪቱ ወታደሮቿ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ ለውጊያ እንድታሰማራ አልተጠየቀችም ። በአሁኑ ዘመቻ ፈረንሳይ ተጨማሪ ወታደሮች ታዘምታለች ። የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ራይነር አርኖልድ ፈረንሳይ ማገዙ ተገቢ መሆኑን ነው የሚናገሩት ።

« የአውሮፓ ህብረት ማሊ በመሰማራቱ ሃገሪቱ ተረጋግታለች ። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ኃይሎች ጋር የሚዘምቱት አጋሮቻችን ፈረንሳዮች እፎይታ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርብናል ። »

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ደግሞ በማሊ ወታደራዊ ድጋፍ የምትሰጠው ጀርመን በዚያ የሚታበረክተው አስተዋፅኦ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የተሻለ መሆኑን ነው አስረድተዋል ።

« በማሊ እገዛ አድርገናል ። እዚያ ሁኔታው አሁን ተረጋግቷል ሆኖም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አልተፈታም ። ማለቴ ከጀርመን አኳያ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ይልቅ በዚያ ይበልጥ እርዳታ ልንሰጥ እንችላለን ። »

ማሊ የተሰማራው የፈረንሳይ ጦር አምፅያኑን ከሰሜን ማሊ ትላልቅ ከተሞች እንዲያፈገፍጉ አድርጓል ። ጀርመን ደግሞ የማሊ ወታደሮችን በማሰልጠን የአየር ትራንስፖርት በማቅረብና በአየር ላይ ነዳጅበመሙላት እያገዘች ነው ። በአሁኑ ጊዜ ለዚሁ ተግባር 170 የጀርመን ወታደሮች ማሊ በግዳጅ ላይ ይገኛሉ ።

Deutsche Bundeswehr Transall C-160
የጀርመን C-160 ወታደራዊ አውሮፕላኖችምስል Getty Images

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ መንግሥትን የሚወጋው የሴሌካ አማፅያን ኅብረት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፐሬዝዳንት ፍራንሷ ቦዚዜን ከስልጣን ካስወገዱበት እጎአ ከመጋቢት 2013 ዓም አንስቶ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ግጭቱ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው ። የቦዚዜ ሥልጣን ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ የተረከቤት ጊዜያዊው ፕሬዝዳንት ሚሼል ጆቶድያም

የቦዚዜ ሥልጣን ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ የተረከቡት ጊዜያዊው ፕሬዝዳንት ሚሼል ጆቶድያም ትናንት በአዲሷ ፕሬዝዳንት በካትሪን ሳምባ ፓንዛ ተተክተዋል ። ሆኖም የሃገሪቱ ፕሬዝዳንቶች መለዋወጥ ግን የህዝቡን ሞት ና ስደት አልገታም ። በእሰከዛሬው ግጭት የሴሌካ ዓማፅያን በፈፀሙት ጥቃት ከአንድ ሺህ የሚልቅ ሰው ሲገደል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ። ግጭቱ ከ 5 ሚሊዮን በላይ ከሚገመቱት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዜጎች ከግማሽ የሚልቁትን የእርዳታ ጥገኛ አድርጓል ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የገባውን ቃል ካልጠበቀ ሃገሪቱ ወደ ዘር ማጥፋት እልቂት ውስጥ መግባትዋ አይቀርም ሲል አስጠንቅቆ ነበር ። ክርስታሊና ጊዮርጌቫ የአውሮፓ ህብረት የዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ኮሚሽነር ግጭቱን ለረዥም የተዘነጋ ይሉታል ። ጂርግዮቫ እንዳሉት ህብረቱ ወታደሮቹ ወደ አካባቢው ከማዝመት ሌላ ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የእርዳታ ገንዘብ ለመስጠትም ቃል ገብቷል ።

« ወደ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማለትም 496 ሚሊዮን ዶላር ቃል ተገብቷል ። ከዚህም ውስጥ 200 ሚሊዮኑ ለአስቸኳይ እርዳታ የሚውል ነው ። 296 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ሰብዓዊውን ሁኔታ ለማረጋጋት ለሚወሰዱ እርምጃዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ቀድሞው ቦታቸው ለመመለስ ለሚከናወኑ ተግባራት ይመደባል ። »

የአውሮፓ ህብረት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን የርስ በርስ ግጭት ለማስቆም ወታደሮቹን ማሰማራቱ ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል ከዚሁ ጋርም ሃገሪቱን ያረጋጋሉ ተብለው የሚታመኑ ሌሎች ሙከራዎችም በመደረግ ላይ መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሃፊ ቫለሪ አሞስ ያስረዳሉ ።

« የእርቀ ሰላም ጥረቶች ና የማህበረሰቡን ግንኙነቶች ማስከን ፍፁም አስፈላጊ ነው ። ስለዚህ አሁን ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ። በሃገር ውስጥ የሃይማኖት መሪዎችና ማህበረሰቡ ከቁጥጥር ውጭ ለሆነው ግጭት በጋራ መፍትሄ እየፈለጉ ነው ። »

ኂሩት መለሰ

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ