1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት ሩስያ እና የዩክሬን ውዝግብ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1 2006

በሁለቱ የምሥራቃዊ ዩክሬይን ከተሞች ሉጋንስክ እና ዶንትሴክ ከዩክሬይን መገንጠል በሚፈልጉ ወገኖች እና በዩክሬይን ፀጥታ ኃይላት መካከል ግጭቱ አሁንም ቀጥሎዋል። ተገንጣይ ቡድኖች አሁንም የመንግሥቱን ጽሕፈት ቤቶችን ካለፈው እሁድ ወዲህ ይዘዋል።

https://p.dw.com/p/1Be2K
Ukraine Unruhen in Donezk 09.04.2014
ምስል picture-alliance/dpa

የዩክሬንና የሩስያ ውዝግብ ተባብሷል ። በሩስያ ስር መሆን እንፈልጋለን የሚሉ ኃይሎች ካለፈው እሁድ አንስቶ በአንዳንድ የምሥራቅ ዩክሬን ከተሞች ነፃነታችንን አውጀናል እያሉ ነው ። በነዚህ ኃይሎች ላይ ዩክሬን እርምጃ እንዳትወስድ ሩስያ እያስጠነቀቀች ነው ።

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በማባባስ የሚወቅሳት ሩስያና ዩክሬን እንዲነጋገሩ ዳግም ጥሪ አቅርቧል ። በዩክሬንና በሩስያ መካከል የሰፈነው ውጥረት በዚህ ሳምንት ተባብሶ ቀጥሏል ሁለቱ መንግስታት መበቃቀል መወቃቀሳቸው አልቆመም ። በምስራቅ ዩክሬኖቹ ከተሞች በክሃርኪቭ በሉጋንስክ እና በዶኔትስክ ሩስያን የሚደግፉ ኃይሎች አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ህንፃዎችን በቁጥጥራቸው አድርገው ነፃነታችንን አውጀናል እያሉ ከሩስያ ጋር መቀላቀል እንደሚፈልጉ ማሳወቅ ከጀመሩ ወዲህ ውዝግቡ ከሯል ። የዩክሬን የኢንዱስትሪ እምብርት የሆኑትና ሩስያኛ ተናጋሪዎች የሚያመዝኑባቸው የነዚህ ከተሞች የወደፊት እጣ ፈንታ እንደ ደቡብ ምሥራቅዋ ክሪሚያ ይሁን አይሁን ከወዲሁ ለመገመት ያዳግታል ። መንግሥት ግን አሁን በነዚህ ከተሞች የሚካሄዱ የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን በክሪሚያ እንዳደረገው ያለ የኃይል እርምጃ እንደማያልፍ እያስጠነቀቀ ነው ። የዩክሬን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ኦሌክሳንድር ቱርቺኖቭ አውቶማቲክ ጠመንጃዎች የታጠቁ ተገንጣዮችና አሸባሪዎች ያሏቸውበእነዚህን ኃይሎች ላይ ህገ መንግስቱና ህጉ በሚፈቅደው መሠረት እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል ዛሬ ።በትናንትናው እለት የዩክሬን ባለሥልጣናት አካሄድን ባሉት ፀረ ሽብር ዘመቻ ካርኪቭ በተባለችው ከተማ የተያዘ ህንፃ አስለቅቀዋል ።

አንድም የጥይት ድምፅ ሳይሰማ በተወሰደው በዚሁ እርምጃ ህንፃውን ይዘው የነበሩ 70 ሰዎችንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል ። ካርኪቭ ና ዶኔትስክ የሚገኙ ህንፃዎችን የያዙት ወገኖች ክሪምያ የተካሄደው ዓይነት ከሩስያ ጋር መቀላቀል አለመቀላቀል ላይ ድምፅ የሚሰጥበት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ነው የሚጠይቁት ። ኦሌክሳንድር ሬልከ ራሳቸውን የደቡብ ምሥራቅ ጦር ሲሉ የሰየሙት የዩክሬን ኃይሎች መሪ ናቸው ። ርሳቸው እንደሚሉት ርሳቸውና በርሳቸው የሚመሩት ኃይሎች ህዝበ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጠዋል ።

Ukraine Proteste Anti Terror Operation
ምስል Reuters

«ህዝበ ውሳኔው በእርግጠኝነት ይካሄዳል ። ለህዝበ ውሳኔው ራሳችንን ለመሰዋት ዝግጁ ነን ። ይህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምናሳውቀው ግልጽ ቃላችን ነው »

በዩክሬን እምነት በነዚህ ከተሞች የሚካሄዱት የእንገንጠል እንቅስቃሴዎች በሩስያ የተቀነባበሩ ናቸው ። ክየቭ እንደምትለው ይህ በሩስያ የሚመራ ዩክሬንን የመበታተን እቅድ ነው ። የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር አርስኔይ ያትሴንዩክ ፀረ ዩክሬን ያሉትን ይህ እቅድ የውጭ ኃይሎች የዩክሬንን ድንበር እያቋረጡ የሃገሪቱን ግዛቶች እንዲይዙ የሚደርግበት ዘመቻ ብለውታል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ኃይሎች ሲሉ በደፈናው ቢናገሩም ተወቃሽዋ ከዚህ እንቅስቃሴ በስተጀርባ እንዳለች የሚገመተው ሩስያ መሆኗ ግልፅ ይመስላል ። በአንፃሩ ሩስያ ውዝግቡ ከተጀመረ አንስቶ የምትለውን ነው አሁን ደግማ ደጋግማ ዩክሬን የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ከሁሉም ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው የምትናገረው ። በነዚህ ኃይሎች ላይ እርምጃ ከተወሰደም ዩክሬን ወደ ርስ በርስ ጦርነት ማምራቷ አይቀርም ስትል አስጠንቅቃለች ። የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዩክሬን ከማናቸውም ወታደራዊ ዝግጅት እንድትቆጠብ አስጠንቅቋል ። ሩስያ እንደምትለው ዩክሬን የፀጥታ ኃይሎችንን በጎ ፈቃደኛ የብሄራዊ ዘብ አባላትን ወደ ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን እያዘመተች ነው ።

Ukraine Pro Russisch Protest Demonstranten Kharkiw
ምስል Reuters

ከዚህ በተጨማሪም የዩክሬንን ወታደር መለዮ ያጠለቁ የአሜሪካን የግል የደህንነት ኃይሎችን አስማርታለች ስትልም ዩክሬንን እየከሰሰች ነው ። ክሱና መወቃቀሱ እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አቴንስ ግሪክ ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዩክሬንና በሩስያ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸው አልቀረም ። የ27 የህብረቱ አባል ሃገራት የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሃገራት መካከል የተነሳው ውዝግብ በውይይት እልባት እንዲያገኝ ዳግም ጥሪ አስተላልፈዋል ። ሞስኮ በዚህ ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆነችና በዩክሬን ላይ የጣለችውን የኤኮኖሚ እገዳ ካላላች በጎረቤቷ በዩክሬን ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር ለራሷም ቢሆን እንደማይበጃት አስጠንቅቀዋታል ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሩስያ ይህን ጉዳይ በቅጡ ልብ እንድትል ነበር ለሁለት ቀናት ከተካሄደው የአቴንሱ ጉባኤ በኋላ ያሳሰቡት ። በርሳቸው አሰተያየት በዩክሬን መውደቅ ሩስያ የምትታገኘው ጥቅም እንደማይኖር መገንዘብ ይኖርባታል ።

«ሩስያም ብትሆን በጎረቤትዋ በዩክሬን በመንኮታኮት ላይ ያለ የፖለቲካ ስርዓት መፈጠሩ እንደማይጠቅማት መረዳት እንደሚገባት ማሳመን እንችላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። »

ሩስያ ዩክሬንን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጫነች ባለችበት በዚህ ወቅት ላይ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ። ምንም እንኳን ሩስያ ቀድሞ በዩክሬን ስር የነበረችውን ክሪምያን በግዛቷ ስር ለማጠቃለል በመወሰኗ የአውሮፓ ህብረት በሩስያ ላይ ማዕቀብ እርምጃዎችን እስከ መውሰድ ቢደርስም ዩክሬን የገባችበት ችግር እንዲፈታ ለማድረግ ግን ከሩስያ ጋር መነጋገር እንደሚገባም ሽታይንማየር አስገንዝበዋል ። የአውሮፓ ህብረት ሩስያ የዩክሬንን ችግር ከመፍታት ይልቅ ክሪሚያን በመጠቅለል ይበልጡን በማወሰሰቧ በተወሰኑ የሩስያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ከመጣል ባለፈ በሩስያ ላይ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጫና ሊያሳድር የሚችል የኤኮኖሚ ማዕቀብ ከመጣል እንደተቆጠበ ነው ። ህብረቱ እንደሚለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ በሩስያ ላይ ሊጣልባት የሚችል ሶሶተኛው ደረጃ ቅጣት ነው ። ይህ ግን አሁን ተግባራዊ የሚሆን አይደለም ። ያም ቢሆን የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊሊያም ሄግ ለዚህ እርምጃም ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል ይላሉ ።

« ይህ ወቅት ሶስተኛው ደረጃ ማዕቀቦች የሚጣሉበት ወቅት አይደለም ። ሆኖም ዝግጁ መሆን አለባቸው ። ምክንያቱም ሁኔታው በጣም አደገኛ ነው ። ውጥረት በእጅጉ የሰፈነበት ነው ። በጣም ብዙ የሩስያ ኃይሎች በዩክሬን ምሥራቃዊ ድንበር ላይ ይገኛሉ ። እነዚህ ኃይሎች ከአካባቢው መልቀቃቸው ለይስሙላ የሚነገር ብቻ ነው ። »

ሄግ እንዳሉትም ሩስያ ቢክሬን ድንበር አቅራቢያ ወታደሮችዋን እንዳሰፈረች ነው ። በዚህ የተነሳም ውጥረቱ ይበልክጥ ከሯል ። ይህ ደግሞ ሄግ እንዳሉት ህብረቱን ዘና ሊያደርገው የሚችል ተግባር አይደለም ።

Ostukraine Krise 07.04.2014 Donezk
ምስል Alexander Khudoteply/AFP/Getty Images

«ከሩስያ በኩል ውጥረቱን ለማርገብ እስካሁን በተጨባጭ ያየነው ነገር የለም ። አውሮፓ ሶስተኛው ደረጃ ማዕቀብ ለማዘጋጀት እና የተጠናከረና የተባበረ ምላሽ መስጠቱን መቀጠሉን ለማረጋገጥ ዘና ማለት የለበትም ። »

አውሮፓውያን ሩስያ ላይ ከዛሬ ነገ እንጥላለን እያሉ የሚያስፈራሩበትን የኤኮኖሚ ማዕቀብ መቼ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለአሁኑ አይታወቅም ። በመካከሉ ሩስያ ዩክሬንን በንግድ እገዳ መቅጣቷን ቀጥላለች ። ትንንት ብቻ ከዩክሬን 6 የወተት ተዋጽኦ ድርጅቶች የምታስገባቸውን ምርቶች አግዳለች ። ሩስያ እርምጃውን የወሰደችው ዩክሬን ባለፈው ሳምንት 7 የሩስያ የምግብ ኩባንያዎች ዩክሬን ውስጥ ምርቶቻቸውን እንዳይሸጡ ላሳለፈችው እገዳ አፀፋ ነው ። ጋዝ ፕሮም የተባለው የሩስያ የተፈጥሮ ጋዝ አምራች ኩባንያም ዩክሬን በጊዜ ያልከፈለችው 2.2 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ የጋዝ እዳ እንዳለባት ዛሬ ይፋ አድርጓል ። ኩባንያው በዩክሬን ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ ግን አላሳወቅም ። በነዚህ የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን በውይይትም ይሁን በሌላ ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ መገኘቱ ያጠራጥራል ። ሩስያ ከወዲሁ በዩክሬን የርስ በርስ ጦርነት እንዳይነሳ እያስጠነቀቀች ነው ። ወዝግቡ ና የተካረረው ውጥረት ወዴት ያመራል ? ወደፊት የምንመለስበት ይሆናል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል ለዝግጅቱ አስተያየት ጥቆማ ወይም ዝያቄ ካላችሁ በSMS በኤምል በፌስቡክ ጻፉልን

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ