1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረትና የልማት ዕርዳታ ፖሊሲው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 1998
https://p.dw.com/p/E0eF

እንግሊዝ ሊድስ ላይ ተሰብስበው የመከሩት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕብረቱ ሚኒስትሮች ለእያንዳንዱ የአፍሪቃ አገር ከሁኔታው የተጣጣመ የልማት ዕርዳታ መርህ ለማስፈንና ከዕዳ ስረዛው ባሻገርም ቀጥተኛ የገንዘብ ዕርዳታና የንግድ ልውውጥ ማቃለያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ተስማምተዋል። ዕርዳታው ይበልጥ ራስ ማስቻያ እንዲሆንም ነው የሚፈለገው።

“ብዙ መደረጉን እናውቃለን። ግን በቂ አይደለም። ለዚህም ነው እዚህ የመጣነው። ሚኒስትሮቹ ያድምጡን፤ ጥሪያችን ድህነትን እናጥፋ! የሚል ነው” ይህን ያሉት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በተካሄደበት ስፍራ ቲያትርና ሙዚቃ በመጫወት ብሶታቸውን ያሰሙት ቦንድ የተሰኘው የብሪታኒይ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባልደረቦች ሄለን ኦ-ኮኔልና አበሮቻቸው ነበሩ። ተቃዋሚዎቹን ቀረብ ብለው ያነጋገሩት የብሪታኒያ የልማት ዕርዳታ ሚኒስትር ሂላሪይ ቤን የአፍሪቃን የልማት ፖሊሲ ግብ በተመለከተ አንድነት አለ፤ ከሁለም በላይ ግን ድህነትን መታገሉ ግድ ነው ሲሉ ለማግባባት ሞክረዋል። ሚኒስትሯ አያይዘው እንዳሉት ልዩነቱ ከዚያ በሚደረስበት መንገድ ላይ ብቻ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ለአፍሪቃ የሚሰጠውን የልማት ዕርዳታ እስከ 2010 ማለት በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት በእጥፍ ለማሳደግ ባለፈው ግንቦት ቃል መግባቱ ይታወሣል። የሉክሰምቡርጉ ሚኒስትር ዣን-ሉዊስ-ሺልትስ ይህ ዕቅድ የአውሮፓ የኤኮኖሚ ዕድገት በወቅቱ ቢጓተትም የሚሳካ መሆኑን ያምናሉ።
“አሁን ያደረግነው ስምምነት ጠንከር ባሉ ቃላት የተደገፈ ነው። ከግቡ እንደምናደርሰው አልጠራጠርም። ገንዘብ በማቅረቡ በኩል ቁጥብነት ቢኖርም ይህ ግዴታውን የመወጣቱን ሃላፊነት አጠያቃቂ አያደርገውም” ብለዋል ሺልትስ!

አዲሱ የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪቃ ፖሊሲ ከሞሮኮ እስከ ሞዛምቢክ ሁሉንም አገር በአንድ ያስቀመጠ አይደለም። ይህን አፍሪቃን በጠቅላላው የውድቀት መለያ ማድረግ ብቻ ሣይሆን ዕድገት ያለባቸውን አካባቢዎችም ነጥሎ የሚመለከተውን አስተሳሰብ የጀርመን የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስትር የፖለቲካ ዘርፍ ሃሳፊ ሚሻኤል ሆፍማንም ይደግፉታል። በርሳቸው አመለካከት ለምሳሌ ሞዛምቢክ የልማት ዕርምጃ የሚታይባት አንዷ አገር ናት። በሌላ በኩል የምዕራባዊው አፍሪቃ ሁኔታ የሚያሰጋቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኮሚሢዮን በበኩሉ የሕብረቱን የአፍሪቃ ፖሊሲ ይበልጥ ማዕከላዊ ለማድረግ ይፈልጋል። ግን ይህን አመለካከት ስዊድንን የመሳሰሉ የቀድሞዎቹ ቅኝ-ገዥ መንግሥታት ፈረንሣይ ወይም ብሪታኒያ የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ በሕብረቱ የልማት ገንዘብ አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይችላሉ ሲሉ አይቀበሉትም።

የልማት ዕርዳታ ሚኒስትሮቹ በሊድሱ ስብለባቸው በዓለም ንግድ ድርጅት የድርድር ዙር ታዳጊ አገሮች የዕርሻ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ እንዲሸጡ የሚረዳ አስታራቂ መፍትሄ መስፈኑን እንደሚፈልጉም ገልጸዋል። እዚህ ላይ ተቃውሞው ጠንከር ብሎ የሚሰማው ከፈረንሣይ በኩል ብቻ ነው።

በሌላ በኩል በታዳጊዎቹ አገሮች በራሳቸው መካከል የሚካሄደው ንግድ ጠቃሚ መሆኑን ያስከነዘቡት የብሪታኒያ ሚኒስትር ሂላሪይ ቤን የደቡብ-ደቡቡን ንግድ ለማስፋፋት የአውሮፓ ሕብረት እስካሁን ከነበረው ይበልጥ ለመርዳት እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ሂላሪይ ቤን ይሁንና በአፍሪቃ የሚገኙ አምባገነን መንግሥታት የራሳቸውን ግዴታ እንዲወጡ በአውሮፓውያኑ ስም ሳያስገነዝቡም አላለፉም።

“ሰላምና እርጋታ የግድ አስፈላጊ ነው የሚሆነው። በጦርነት አካባቢ ገንዘቡን ለማፍሰስ የሚሻ ማንም የለም። ስለዚህም ትምሕርት ቤቶችን ለማነጽ፣ ሃኪሞችን በስራ ለማሰማራትና ጠቃሚ መድሃኒቶችን ለመግዛት ፈቃዱና ብቃቱ ያላቸው መንግሥታት ያስፈልጋሉ” ብለዋል አስተናጋጇ የብሪታኒያ የልማት ዕርዳታ ሚኒስትር!