1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረትና የግሪክ የዕዳ መዘዝ

ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2003

የአውሮፓ ሕብረት በበጀት ኪሣራና በቀውስ የተጠመዱ ዓባል ሃገራቱን ከችግር ለማውጣት ድጎማ መስጠቱ የተለመደ ነገር እየሆነ ሲሄድ ከነዚሁም አንዷ ግሪክ ናት።

https://p.dw.com/p/RSUR
ምስል fotolia/DW

ግሪክ ቀደም ሲል ባገኘችው ድጋፍ ከበጀት ቀውሷ መላቀቅ አለመቻሏ ባለፉት ሣምንታት እንደገና ሲያነጋግር ነው የቆየው። እናም አገሪቱ ቀውሱን ለመቋቋም እጅግ የሚያስፈልጋትን ተጨማሪ 12 ሚሊያርድ ኤውሮ እንደምታገኝ ባለፈው አርብ ሲገለጽ ዜናው በተለይ የአቴንን መንግሥት እፎይ ማሰኝቱ አልቀረም። ከዚህ የተደረሰው ቀደም ሲል ገንዘቡን የሚያቀርቡት የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ መርማሪዎች የግሪክን መንግሥት የፊናንስ ሰነዶች ከፈተሹ በኋላ ነበር። ብድሩ ባይሰጥ ግሪክ የቁጠባ ዕቅዷን ገቢር ማድረግ ካለመቻሏም በላይ የሚቀራት ከለየለት መንግሥታዊ ክስረት ላይ መውደቅ መሆኑ ታምኖበታል። ይህ የግሪኩ የፊናንስ ሚኒስትር ጊዮርጊዮስ ፓፓኮንስታንቲኑም ከጥቂት ቀናት በፊት የተናገሩት ነበር።

“የሠራተኞችን ደሞዝና የጡረታ አበል ለመክፈል፤ በጥቅሉ ማንኛውንም የመንግሥት የፊናንስ ግዴታ ሁሉ ለማሟላት አንችልም። እንበል በአገርአቀፍ ደረጃ መጋረጃ መዝጋት ነው የሚቀረን”

የግሪክ የፊናንስ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ብድር የመፍቀዱ የተቆጣጣሪዎቹ ውሣኔ የተመሠረተው በመጀመሪያ ደረጃ በቁጠባ ረገድ በወቅቱ በሚታየው ዕርምጃ፣ በአማካይ ጊዜ ባለው የፊናንስ ዕቅድ፤ እንዲሁም ዕድገትንና የፉክክር ብቃትን ለማስፈን በታቀደው መዋቅራዊ ለውጥ ላይ ነው። በሌላ በኩል ግን ግሪክ ጠንካራ የቁጠባ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅባታል። ጭብት አሃዝን ለመጥቀስ የፓፓንድሬዉ መንግሥት እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በራሱ አቅም 78 ሚሊያርድ ኤውሮ መቆጠብ አለበት። ከዚሁ 50 ሚሊያርዱን ለማግኘት የሚታሰበው የመንግሥትን ቋሚ ንብረትና ድርሻዎች ወይም ሼር በመሸጥ ነው። እርግጥ ይህን ዓይነቱ ዕርምጃ በአቴኑ ፓርላማ ድጋፍ ማግኘቱ በወቅቱ ያጠያይቃል። የተቃዋሚው ወግ አጥባቂው ኔያ-ዴሞክራቲያ ፓርቲ መሪ አንቶኒስ ሣማራስ ለምሳሌ ቁጠባውን ደግፈው ድምጽ ከማይሰጡት መካከል አንዱ ናቸው።

“የኤኮኖሚው መንኮራኩር ሞተር ቁልፉን አዙረን እስካልለኮስነው ድረስ አይንቀሳቀስም። ለዚህ አዲስ ጅማሮ ቁልፉ ደግሞ ግብርን መቀነስ ነው። ስለዚህም አዲሱን ጅማሮ ማድረጉ እንዲያው ለመናገር ብቻ አይደለም በተጨማጭ ምክንያቶች የተነሣ ግድ ነው የሚሆነው”

የአቴን መንግሥት ከሁሉም አቅጣጫ ቀላል ነገር አይጠብቀውም። ሰሞኑን ከሕብረተሰቡም አንጻር ቢሆን የመንግሥቱን የቁጠባ ዕቅድ በመቃወም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ነው አደባባይ የወጣው። መንግሥት ሁለተኛ የቁጠባ ዙር ለማድረግ ቢገደድም ግብር እንደገና መጨመሩ ለብዙዎች የሚዋጥ ነገር አልሆነም። የአውሮፓ ሕብረትና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ቀውሱን ለመቋቋም ቀደም ሲል ከአንድ ዓመት በፊት ለግሪክ የሰጡት 110 ሚሊያርድ ኤውሮ ሊበቃ አልቻለም። ስለዚህም ተጨማሪ 65 ሚሊያርድ ኤውሮ እንደሚያስፈልግ ነው የፊናንስ አዋቂዎች የሚናገሩት። ይህ ለዘለቄታው ይበቃል አይበቃም ግን ዛሬ ቀድሞ ለመናገር በጣሙን ያዳግታል። ግልጽ ነገር ቢኖር ግሪክ ቢፈጥን ቢፈጥን በ 2014 ዓ.ም. ከካፒታል ገበዮች ገንዘብ በራሷ መበደር ብትችል ነው። በዚያው ገንዘቡ በሚገኝበት በፊናንሱ ገበያ ላይ ደግሞ የባደር ባንክን ባልደረባ ሮበርት ሃልቨርን የመሳሰሉት የፊናንስ ባለሙያዎች ግሪክን ለማዳን የቀረበው የሚሊያርድ ፓኬት ፍሬ በመስጠቱ ተጠራጣሪዎች ናቸው።

“በዚህ ዕርምጃ ጥቂት ፋታ ማግኘት ብቻ ነው የምንችለው። ለነገሩ ለግሪክ ለሚቀጥሉት ዓመታት አንድ ዕቅድ ያስፈልገናል። የእርሻ ልማት፣ ቱሪዝም፣ የጸሃይ ኤነርጂና ለመካለኛው ምሥርቅ የውጭ ንግድ ዋና መተላለፊያ መሆን መቻል ድንቅ የኤኮኖሚ ዕቅድ ነው ብዬ አስባለሁ። እንዲያው በደፈናው ገንዘብ ማሸከሙ ብቻ መፍትሄ ሊሆን አይችልም”

የግሪክ ችግር ከባድ ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት የአውሮፓ ሕብረት የመረጠው ወደ ውጭ ተሥፋን ማንጸባረቁን ነው። የኤውሮው ምንዛሪ ቡድን ሃላፊ ዣን-ክላውድ-ዩንከር ቢቀር በአውሮፓ ፓርላማ ፊት ያሣዩት ገጽታ ከዚህ የተለየ አልነበረም።

“ግሪክ ለያዝነው 2011 ዓ.ም. ያላትን የበጀት ቁጠባ ግብ ታሳካለች። አገሪቱ አሁን የዕድገት አቅሟን ከፍ ለማድረግ የሚያስፈልጋትን መዋቅራዊ ለውጥ እንደምታካሂድ አምናለሁ። ግሪክ ንብረትን በሰፊው ወደ ግል ዕጅ የማዛወር ተግባርም ትጀምራለች”

ዩንከርና የኤውሮው ምንዛሪ ኮሜሣር ኦሊ ሬህን ይህን ተሥፋ ሲያጠነክሩ በሌላ በኩል የዕርዳታው ጉዳይ አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። ውስጥ ውስጡን ስሎቫኪያ ተጨማሪ የዕርዳታ ፓኬትን ለመግታት መነሣቷ እየተነገረ ነው። በጥቅሉ የግሪክ የወደፊት ጉዞ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

የዓባል ሃገራቱ የበጀት ኪሣራ በሌላ በኩል የአውሮፓው ሕብረት ንቁ ክትትል እንዲያደርግ ቀስቃሽ መሆኑም አልቀረም። የሕብረቱ ኮሚሢዮን የ 27ቱን ዓባል ሃገራት የመጪውን ዓመት የበጀት ዕቅድ መርምሮ የመጀመሪያ ውጤቱን ይፋ አድርጓል። ዘገባው ለእያንዳንዱ አገር የኤኮኖሚና የፊናንስ ፖሊሲ የለውጥ ሃሣብንም የሚጠቀልል ነው። የአውሮፓ ሕብረት ሃገራት የበጀት ሁኔታ የፊናንስ ይዞታቸውን በሚገባ ከሚቆጣጠሩት ጀምሮ መቆጣጠር እስካቃታቸው ድረስ ሁሉንም በያይነቱ ያቅፋል። ዓባል መንግሥታቱ የበጀት ረቂቃቸውን ወደ ብራስልስ የላኩት ባለፈው መጋቢት ወር ነበር። የሕብረቱ ኮሚሢዮንም ረቂቆቹን በብሄራዊ ም/ቤት ከመጽደቃቸው’ በፊት ተቀብሎ ሲመረምር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

የብራስልሱ ኮሚሢዮን በዚህ አሠራር ወደፊት የዕዳ ችግርን ዘግይቶ ከመጋተር ቀድሞ ለመታገል እንደሚቻል ያምናል። በምርምሩ ላይ ስናተኩር አብዛኞቹ የበጀት ዕቅዶች በዛም አነሰ የሕብረቱን መርህ የተከተሉ መሆናቸውን ነው የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ያረጋገጡት።

“አንዳንዶቹ የበጀት ዕቅዶች ጠንካሮች ሲሆኑ ሌሎቹ በአንጻሩ ገና ጭብጥ መልክ መያዝ ይኖርባቸዋል”

የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮን ጥናቱን ያካሄደው ዓባል ሃገራቱን በሶሥት በመመደብ ነው። በሕብረቱ ሃገራት ከክስረት የተረፉት ግሪክ፣ አየርላንድና ፖርቱጋል አንዱ ቡድን ውስጥ ናቸው። እነዚሁ አሁን የተስማሙበትን የቁጠባና የለውጥ ዕቅድ ገቢር ማድረግ አለባቸው። ቀጥሎ ደግሞ ሰፋ ያለ መሃል ሰፋሪ ቡድን አለ። በዚህ ውስጥ የተጠቃለሉት የዕዳ ችግራቸውን ገና መቆጣጠር ያልቻሉ ናቸው። ሌሎች አውስትሪያን፣ ፊንላንድንና ጀርመንን የመሳሰሉ የሚገኙባቸው ዕዳቸውን በሰፊው መቆጣጠር የሆነላቸውም አሉ። ግን እነዚህ በአርአያነት ሊታዩ የሚችሉ አገሮችም ቢሆን በጥናቱ መሠረት በብዙ ዘርፎች የተሻለ መሆን የሚጠበቅባቸው ናቸው። የሕብረቱ የምጣኔ-ሐብት ኮሜሣር ኦሎ ሬህን እንደሚሉት በተለይም በሥራ ገበዮች ላይ ገና ብዙ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው።

“የሥራ ሃይል አቅርቦት ሴቶች የሙያውን ዓለም በቀላሉ እንዲቀላቀሉ በማድረግ መሻሻል ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ከሰሜን አውሮፓ ልምድ መማር ያለባቸውን ጀርመንን፣ አውስትሪያንና ኔዘርላንድን የመሳሰሉት ሃገራት የሚመለከት ነው”

በተለይ ጀርመንን በተመለከተ ሃገሪቱ በሕገ-መንግሥቷ ውስጥ የተቀመጠው የመንግሥትን ዕዳ ጣራ የሚወስን አንቀጽ ፍቱንነት ማረጋገጥ ይኖርባታል። ይህ ፌደራል ክፍለ-ሐገራትን ጭምር የሚጠቀልል ሲሆን የየአካባቢው ባንኮችም የለውጥ ተሃንጾን የሚጠይቁ ናቸው። በመሠረቱ በሥራ ገበዮች ላይ ዕርምጃ እንዲከተል ሁሉም አገር ፍቱን ዕርምጃ መውሰድ አለበት። በአንዳንድ አገሮች ደሞዝ ከምርታማነት ፈጥኖ ማደግ መያዙ እንደቀጠለ ነው። የጡረታው ስርዓት ከሕብረተሰቡ የማርጀት ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እንዲለወጥ በቂ ዕርምጃ አልተወሰደም። ግትር የሥራ ሕግም እንዲሁ ሥራ አጦች መልሰው እንዳይቀጠሩ መሰናክል ሲሆን ይታያል። የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን የሥራ ኮሜሣር ላሢዮ አንዶር እንደሚያስረዱት ይህ ካልተለወጠ የድህነት አደጋ ሊቀንስ መቻሉ ዘበት ነው።

“63,5 በመቶው ሥራ አጦች ዛሬ ለድህነት አደጋ የተጋለጡ ናቸው። እናም መሥራት የሚችሉ ሰዎች በሥራው ገበያ ላይ እንዲቆናጠጡ ማገዝ ይኖርብናል። ይህ የግድ አስፈላጊ ነው”

የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች በያዝነው ወር መጨረሻ ሲሰበሰቡ የኮሚሢዮኑን የለውጥ ሃሣብ ተቀብለው ያጸድቃሉ። እናም የለውጡ ሃሣብ ይህንኑ ተከትሎ አሣሪ ይሆናል ማለት ነው። የሚከተለውን እንድግዲህ ሰንበት ብሎ መታዘቡ ግድ ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ