1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረትና የ ACP የኤኮኖሚ ውል ድርድር

ረቡዕ፣ ግንቦት 22 1999

የአውሮፓ ሕብረት በአሕጽሮት ACP በመባል ከሚታወቀው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ መንግሥታት ስብስብ ጋር አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን የሚያካሂደው ድርድር በተጣለው የጊዜ ገደብ፤ ማለት እስከያዝነው 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ስኬት ማግኘቱ ገና ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ አይደለም።

https://p.dw.com/p/E0ct
ምስል AP

በዓለም ንግድ ድርጅት ውሣኔ መሠረት ታዳጊዎቹ አገሮችም ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ የሚያደርገው ውል አብዛኞቹን በ ACP ውስጥ የተጠቃለሉትን መንግሥታት ስጋት ላይ መጣሉን እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሣምንት ብራስልስ ላይ የተገናኙት የሁለቱ ወገን ተጠሪዎች እስከ ዓመቱ መጨረሻ የነጻ ንግዱን ውል ለማስፈን እንደሚጥሩ ገልጸዋል። ጥያቄው የአውሮፓው ኮሚሢዮን ግፊት ለዝቦ አስታራቂ መፍትሄ በጊዜው ይገኛል ወይ ነው። ካልሆነስ ምን ዓይነት አማራጭ አለ?

የአውሮፓው ኮሚሢዮን 78 በአብዛኛው የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች የነበሩ ሃገራትን የሚጠቀልለው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ ስብስብ የሁለት ወገን ገበያ ከፈታን ግድ የሚያደርገውን አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል እንዲፈርም ግፊት ሲያደርግ ነው የቆየው። ከታዳጊው ዓለም ስብስብ በርከት ያሉት የድሃ ድሃ የሚባሉ ሃገራት ውሉ እስካሁን ወደ አውሮፓ ገበያ ለመዝለቅ ተሰጥቷቸው የቆየውን ልዩ የንግድ አስተያየት ከንቱ የሚያደርግ ከሆነ ለመፈረም ዝግጁ አለመሆናቸውን ባለፈው አርብ ብራስልስ ላይ ግልጽ አድርገዋል። አውሮፓውያን መንግሥታት ለስጋታችን ትክረት ሊሰጡ ይገባል ባዮች ናቸው።

የቦትሱዋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞምፓቲ ሜራፌ ብራስልስ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የመጣንበት አካባቢ በድህነት የተጠመደ እንደመሆኑ መጠን ልንቀበለው የምንችለውን የንግድ ስምምነት ለማስፈን መጣራችን አስፈላጊ ነው ብለዋል። አጠቃላዩ ዝንባሌ ይህ ሲሆን የአውሮፓ ኮሚሢዮን በበኩሉ ውሉ የታዳጊዎቹን አገሮች ልማት ለማፋጠን እንደሚረዳ ዕምነቱ ነው። የወቅቱን የሕብረቱን የመንፈቅ ርዕስነት የያዘችው የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል የኤኮኖሚው ሽርክና ውል የ ACP አገሮች ወደ አውሮፓ የሚያደርጉትን የውጭ ንግድ እንደሚያዳብርና አፍሪቃ ውስጥ የአካባቢ የኤኮኖሚ ትስስርን የሚያበረታታ እንደሚሆን ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

ቪቾሬክ-ሶይል ከብራስልሱ ንግግር በኋላ ለጋዜጠኞች ሲያስረዱ ስምምነቱ ልማትን የሚያራምድ መሆኑን ማረጋገጡ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ የጀርመናዊቱ የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል የኤሪካ ማን አመለካከትም ነው። “ድርድሩ እርግጥ እስከ ዓመቱ መጨረሻ መጠናቀቅ አለበት። እኛ በተወሰኑ ነጥቦችና፤ የጊዜውን ገደብ በተመለከተም ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ መደራደሩ አስፈላጊ ነው ብለን ነው የምናምነው። ምክንያቱም ውሉ እስከ ዓመቱ መጨረሻ መገባደድ ያለመቻሉ አደጋ አለና” ብለዋል። ኤሪካ ማን አያይዘው እንዳስረዱት ሃቁ ይህ በመሆኑ ከፓርላማው አንጻር የአውሮፓ ኮሚሢዮን አስተማማኝ አቋም መያዙ፤ ማለት ለ ACP አገሮች ወደፊትም በገበዮቹ ልዩ የንግድ አስተያየቶችን የሚፈቅዱ መንገዶችን ማጤኑ አስፈላጊ ነው። ኮሚሢዮኑ በዚህ በኩል የፓርላማው ድጋፍ እንዳለውም አመልክተዋል።


የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሢፊክ ስብስብ ሊቀ-መንበር የሌሶቶው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሕላቢ ሴኮዋ በበኩላችው የሁለቱ ወገኖች ድርድር ምንም እንኳ ፈታኝ ቢሆንም አውሮፓውያኑ ለታዳጊዎቹ አገሮች ስጋት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ብዙ መጣራቸውን ነው የሚናገሩት። ሁለቱ ወገኖች ድርድሩን በተጣለው የጊዜ ገደብ እንደሚያጠቃልሉም ያምናሉ። በዚህ አባባል የብራስልሱ ኮሚሢዮን ታላቅ ዕርካታ እንደሚሰማው አንድና ሁለት የለውም። ምክንያቱም ከተለያየ አቅጣጫ ተቃውሞና ጥርጣሬ ገጥሞት የቆየ መሆኑ ነው።

ከመንግሥታት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የአውሮፓ ሕብረት ለማስፈን የሚፈልገው ውል ታዳጊዎቹ አገሮች በቀላሉ ሊቀበሉት የሚከብድ ነው፤ ድህነትን ለመታገልም አይበጅም ይላሉ። ውሉ ታዳጊዎቹ አገሮች ኤኮኖሚያቸውን ብዙ-ወጥ በማድረግ እንዲለሙ የሚረዳ ሆኖ የታሰበ ነው ቢባልም በዓለም ንግድ ድርጅት ውሣኔ መሠረት ገበዮቻቸውን ለአውሮፓ ምርቶችና አልግሎቶች እንዲከፍቱ የሚያደርግ መሆኑ እነዚህን ወገኖች አልተዋጠላቸውም። በዓመቱ መጨረሻ የሚያከትመውና እስካሁን ሲሰራበት የቆየው የኮቶኑ ውል ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ የሚጠይቅ አልነበረም።
በአንጻሩ የተወሰኑት ድሆች አገሮች በልዩ የንግድ አስተያየት ምርቶቻቸውን ለአውሮፓ ገበዮች እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸው ቆይቷል። ብዙዎቹን እነዚህን አገሮች ስጋት ላይ የጣለውም ይሄው ልዩ የንግድ አስተያየት የመቅረቱ ሃሣብ ነው። የቆየው ውል የሚያበቃበት የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ መሄድ በያዘበት በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ሕብረት ከስኳርና ከሩዝ በስተቀር በመላው የ ACP ምርቶች ላይ ጥሎ ያቆየውን ኮታና ቀረጥ ጨርሶ እንደሚያስወግድ ቃል በመግባት ድርድሩን ለማነቃቃት ሞክሯል። ሃሣቡ በአብዛኛው ተቀባይነት ቢያገኝም የስኳር ምርት ተለይቶ መቀመጡ ይሄው ዋነኛ የውጭ ንግድ የገቢ ምንጫቸው የሆነውን ባርቤዶስን፣ ፊጂንና ሞሪሺየስን የመሳሰሉትን ደሴቶች ግን ማስከፋቱ አልቀረም።

ውሉ ለታዳጊዎቹ አገሮች ልማት ከመበጀቱ ይልቅ የእስካሁኑን ስምምነት ሕገ-ወጥ ያደረገውን የዓለም ንግድ ድርጅትን የጊዜ ገደብ ለማክበር ተብሎ ከተፈረመ ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች እንደሚሉት ፈሩን የሣተ ነው የሚሆነው። ታዳጊዎቹ አገሮች በተለይ ለአውሮፓ የአልግሎት ዘርፍና የመዋዕለ-ነዋይ ኩባንያዎች ገበዮቻችውን በመክፈታቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ድሃ ሕዝባቸው የኑሮ መሠረቱን ሊያጣ ይችላል። እ.ጎ.አ. ከ 1975 ዓ.ም. የሎሜ ውል ጀምሮ የነበረው ለታዳጊ አገሮች የአውሮፓን ገበዮች ከፍቶ የቆየው ልዩ የንግድ አስተያየት በአንድ መንገድ ቀጣይነት ካላገኘ ስጋቱ፤ ችግሩ በቀላሉ ወደጎን መገፋቱ ቢቀር በወቅቱ ጥቂትም ቢሆን ያጠራጥራል።
በመሆኑም የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል ኤሪካ ማን እንደሚሉት የተለያዩ አማራጮችን አጣምሮ መመልከቱ የሚጠቅም ነው። በርሳቸው አመለካከት “በጉዳዩ ፈታ ያለ አቋም ለመያዝ የሚያበቃ ሁኔታ አሁንም አለ። በወቅቱ ጀኔቫ ላይ የዓለም ንግድ ድርጅት ሊቀ-መንበር ከሆኑት ከፓትሪክ ላሚ ጋር በፓርላማችን ባደረግነው ንግግር ድርድሩ እስከ ዓመቱ መጨረሿ በተሟላ ሁኔታ ባይጠናቀቅ ምን እንደሚያደርጉ ጠይቀናቸዋል። እርሳቸውም የተወሰነ መፈናፈኛ ሁልጊዜም መኖሩን ነው ያመለከቱት። እርግጥ ይህ መፈናፈኛ ጊዜ ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ በወቅቱ በትክክል ለመናገር አይቻልም። የኔ የግል አስተሳሰብ ድርድሩ ለ ACP ሃገራት አስተማማኝ ፖሊሲ፤ ወደ አውሮፓ ገበዮች የመዝለቅ አስተማማኝ ሁኔታ ኖሮ መጠናቀቅ ይኖርበታል የሚል ነው”

ግን ጥያቄው ይህ ይሆናል ወይ ነው። ለማንኛውም የአውሮፓ ሕብረት ታዳጊዎቹን አገሮች ለማግባባት ወይም ስጋታቸውን ለማለዘብ አንዳንድ ሃሣቦችን ማፍለቁ አይቀርም። የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል ለምሳሌ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ ስብስብ አገሮች በተወሰኑ ምርቶች ረገድ የነጻውን ንድግ መርሃ-ግብር ለማስፈን እስከ 25 ዓመት የሚዘልቅ መሸጋገሪያ ጊዜ እንደሚኖራችው ተናግረዋል። ሆኖም ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች ታዳጊ አገሮች በተቻኮለ ሁኔታ ለአውሮፓ ምርቶች ገበዮቻቸውን በመክፈት ገበሬዎቻቸውንና ጨቅላ ኢንዱስትሪያቸውን እንዳይጎዱ ነው የሚያስጠነቅቁት።

ከአውሮፓው ኮሚሢዮን በኩል የታዳጊዎቹን አገሮች ስጋት ለማለዘብ እስካሁን የተባለው ሁሉ ተብሎ እንግዲህ ውሉ በጊዜው መፈረሙ ገና ያልለየለት ጉዳይ ነው። የታሰበው ካልተሣካ ኤሪካ ማን እንደሚሉት ምናልባት መሸጋገሪያ ጊዜ ሊያስፈልግም ይችል ይሆናል። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ አዲስ ውል እስኪፈረም ድረስ የታዳጊዎቹ አገሮች ምርት በልዩ የንግድ አስተያየት ወደ አውሮፓ ገበዮች መዝለቅ መቀጠሉን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ማለት ለሽግግሩ ጊዜ!