1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረት የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ

ሐሙስ፣ ግንቦት 18 1997
https://p.dw.com/p/E0eg

የበለጸጉት የዓለም መንግሥታት ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0.7 በመቶ የምትሆነዋን ድርሻ ለታዳጊ አገሮች ልማት በተግባር ላይ ለማዋል ቃል ከገቡ 35ዓመታት አልፈዋል። ሆኖም ግን በ 1970 ዓ.ምቱ የተባበሩት መንግሥታት ውሣኔ መሠረት የገቡትን ቃል አክብረው በሥራ የተረጎሙት ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይና ሉክሰምቡርግ ብቻ ናቸው።

እንግዲህ የትናንት በስቲያው የአውሮፓ ሕብረት ስምምነት አንድ አዲስ ጅማሮ ሲሆን እስካሁን ያልተጠበቀው ቃል ወደፊትም መከበሩን ግን ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። እርግጥ የአውሮፓው ኮሚሢዮን፤ ማለትም የሕብረቱ አስፈጻሚ አካል የልማት ዕርዳታው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት እስከ 2015 እንዴት 0.7 በመቶ ከሆነው ግብ እንደሚደርስ ያረቀቀውን ሃሣብ የውጭ ልማት ሚኒስትሮቹ በፊርማ ያጸደቁት ቁርጠኛ መስለው በታዩበት ሁኔታ ነበር።

በሕብረቱ የልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሚሺነር በሉዊስ ሚሼል ረቆ በቀረበው ሃሣብ መሠረት ነባሮቹና ሃብታሞቹ 15 ዓባል ሃገራት ግዴታቸውን ለመወጣት በ 2010 ገደማ ከአጠቃላይ ምርታቸው ቢያንስ 0.51 የሚሆነውን ድርሻ ማቅረብ፤ በ 2015 ዓ.ምም ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት በፊት ተቀምጦ ከነበረው ግብ መድረስ ወይም ከዚያ ለመዝለቅ መጣር ይጠበቅባቸዋል።

ምሥራቅ አውሮፓውያን የሚያመዝኑባቸው አሥሩ የሕብረቱ አዳዲስ ዓባል ሃገራት ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ ቢያንስ 0.17 በመቶ ዕርዳታ ለማቅረብና በ 2015 ገደማም ድርሻቸውን ወደ 0.33 በመቶ ከፍ ለማድረግ እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል። መላው 25 የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት በጋራ የሚያቀርቡት የልማት ዕርዳታ በአማካይ ከብሄራዊ ምርታቸው አንጻር በ 2010 ዓ.ም ወደ 0.56 በመቶ የሚደርስ መሆኑ ነው። በሌላ አነጋገር ስምምነት የተደረሰበት የልማት ዕርዳታ ጭማሪ ሃያ ቢሊዮን ኤውሮ የሚጠጋ ይሆናል። ይህ ደግሞ ከነባሮቹ 15 የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት ግብር ከፋይ ነዋሪ አንጻር በዓመት የ 61 ዶላር ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።

የአውሮፓው ሕብረት ዕርምጃ ያለመው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሣኔ መሠረት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ መዋጮውን ወደ 0.7 በመቶ ለማድረስ የያዘውን ዓላማ ለማነቃቃትና በዚያው በ 2015 ዓ.ም. ከግቡ እንዲደርስ የተወጠነውን የሚሌኒየም ዕቅድ ገሃድ በማድረጉ ላይ ነው። እስካሁን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0.7 በመቶውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማቅረብ በ 1970 ዓ.ም. የገቡትን ቃል ዕውን ያደረጉት ሃብታም አገሮች ቀደም ሲል የጠቀስናቸው አራት አውሮፓውያን መንግሥታት ብቻ በመሆናቸው የተባለው ሁሉ ገቢር ይሆናል ብሎ ለመናገር እምብዛም አያስደፍርም።

ብዙዎቹ አገሮች ለነገሩ የሚገባውን ክብደት የሰጡ አይመስልም። ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይ፣ ፊንላንድ፣ አየርላንድ ቤልጂግና ስፓኝ መጪዎቹ አሥር ዓመታት ከመጠናቀቃቸው በፊት መስፈርቱን ለማሟላት ቃል በመግባት ሲወሰኑ ሌሎች ኢጣሊያንና አውስትሪያን የመሳሰሉ አገሮች ደግሞ ድህነትን ለመታገል የሰጡትን ተሥፋ እንዲያውም ከኋላ ሲከተሉ ነው የሚታየው።

ለማንኛውም ትናንት ብራስልስ ላይ የልማት ዕርዳታ ማሳደጊያውን ስምምነት ያስተዋወቁት በወቅቱ ተፈራራቂውን የሕብረቱን ርዕስነት ይዛ የምትገኘው የሉክሰምቡርግ የልማት ሚኒስትር ዣን-ሉዊስ-ሺልትስ የዕርዳታው ቃል የሚሌኒየሙ ዕቅድ በ 2000 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ይፋ ከሆነ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ውሣኔው ዓለምአቀፍ መተሳሰብ መኖሩን የሚያሳይ እጅግ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው፣ አውሮፓ ዛሬ ይህ ባዶ ቃል እንዳልሆነ በተግባር አስመስክራለች ሲሉ ነው አያይዘው ያስገነዘቡት። የብራስልሱ ስምምነት የአውሮፓን ሕብረት ዓለምአቀፍ የልማት ፖሊሲ ቀደምትነት ኒውዮርክ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ከሚካሄደው ጉባዔ በፊት እንደሚያስረግጥና ጃፓንና አሜሪካን የመሳሰሉት አሁን ከአውሮፓ ያነሰ ዕርዳታ የሚሰጡት ሌሎች ለጋሽ አገሮች የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ግፊት እንደሚሆንም የሚሼል ዕምነት ነው።

የዓለም መንግሥታት መሪዎች በፊታችን መስከረም ወር ተገናኝተው እስከ 2015ድህነትን በግማሽ የመቀነሱን ውጥን የጠቀለለው የሚሌኒየም ዕቅድ በግቡ አቅጣጫ በሚያደርገው ጉዞ የሚታይበትን የመጓተት ችግር ያጤናሉ።

በሌላ በኩል የብራስልሱ ስምምነት የተፈረመው አንዳንድ ዓባል መንግሥታት ቅሬታ ባሰሙበት ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ጀርመን፣ ኢጣሊያና ፖርቱጋል በተናጠል ባወጧችው መግለጫዎች ከፍተኛ የፊናንስ ችግር እንዳለባቸውና የሕብረቱን የበጀት ኪሣራ ገደብ ለመጠበቅ እየጣሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። የአውሮፓ ሕብረት የዓባል ሃገራትን ገንዘብ የማውታት ብቃት የሚገድቡ መመሪያዎች እንዳሉት የሚታወቅ ነው።
ሆኖም የሉክሰምቡርጉ ባለሥልጣን እንዳስረዱት ሶሥቱ መንግሥታት ያወጧቸው መግለጫዎች የሽሽት ምክንያቶች ሆነው መታየት የለባቸውም። ለርሳቸው የሚያመዝነው የተጠቀሱት ሃገራት ችግር እንዳላቸው ቢያመለክቱም ዋናው ነገር ግዴታውን መቀበላቸው ነው። “Global Call to Action against Poverty” የተሰኘው ድህነትን የሚታገል ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ስብስብ የአውሮፓው ሕብረት የልማት ዕርዳታውን ለማሳደግ ትናንት ብራስልስ ላይ ያደረገውን ስምምነት በመደገፍ ዕርምጃው አሜሪካ፣ ካናዳና ጃፓን ራሳቸው የገቡትን ቃል ያከብሩ ዘንድ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ዕምነቱን ገልጿል።

ለንደን ላይ የሚካሄደው የ G-7 የሰባቱ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ሃያላን መንግሥታት ስብሰባና የስኮትላንድ የ G-8 ጉባዔ ጥቂት ሣምንታት ቀርቷቸው ሳለ ስምምነቱ ገሃድ መሆኑ ግፊቱን እንደሚያጠነክረው ቡድኑ ጨርሶ አይጠራጠርም። ስብስቡ ከዚህ በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በመጠየቅ ጉዳዩ ከአሥር ቀናት በኋላ በሚካሄደው የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ጠንክሮ እንዲነሣ አሳስቧል።