1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ኤኮኖሚና የቻይና ተጽዕኖ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2003

የሕዝባዊት ቻይና የኤኮኖሚ ተጽዕኖ ምናልባትም በአፍሪቃ ወይም በማዕከላዊው እሢያ እንደሚታየው ብዙ ክብደት ሳይሰጠው ይቆይ እንጂ በአውሮፓ ክፍለ-ዓለምም እያደገ በመሄድ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Pq8U
ምስል picture-alliance / dpa

እንደሚታወቀው የማዕከላዊና የደቡብ አውሮፓ አገሮች በተለይም ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ወዲህ ብዙ የገንዘብ ችግር ተጭኗቸው ነው የሚገኙት። እናም ይሄው ሁኔታ ለቻይና አዲስ በር ከፋች መሆኑ አልቀረም። በምዕራቡ ዓለም መዳከም ይበልጥ ሃያል እየሆነች የሄደችው ቻይና በዝቅተኛ ወለድ ፕሮዤዎችን በመቆጣጠር የሁኔታው ተጠቃሚ ስትሆን መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎቿ በተለይም በመዋቅራዊው ግንባታ ዘርፍ ታላላቅ ፕሮዤዎችን በዕጃቸው ማስገባታቸው እየጨመረ ነው። ለምሳሌ ፖላንድ ውስጥ የአንድ አውራ ጎዳና ሥራን በጨረታ አሸንፈው ይዘዋል። ታዲያ ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ሕብረት ክልል ውስጥ በዚህ ዘርፍ ያደረገችው መቆናጠጥ ጀርመንን የመሳሰሉት ምዕራባውያን አገሮች በፉክክር ዝቤት እንዲወነጅሏት ማድረጉ አልቀረም።

ቻይና በተለይም የተፋጠነ ዕድገቷ የሚጠይቀውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ለማሟላት በምታደርገው ጥረት በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የኤኮኖሚ ተጽዕኖዋን ስታጠናክር መቆየቷ ባለፉት ዓመታት ብዙ ሲነገርለት የቆየ ጉዳይ ነው። ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በአፍሪቃ ምድር ምርቶቿን በገፍ ታራግፋለች። የማዕድን ሃብትን ከማውጣት እስከ መዋቅራዊ ግንቢያ ድረስም ያልገባችበት ዘርፍ አይገኝም። ለግንዛቤ ያህል ዛሬ ከ 1,600 የሚበልጡ የቻይና ኩባንያዎች አፍሪቃ ውስጥ በማዕድን፣ በንግድ፣ በእርሻ፣ በመንገድና ሌላ መዋቅራዊ ግንባታ፤ እንዲሁም በምርት ተግባር መዋዕለ-ነዋይ ያደርጋሉ።
የቻይና የንግድ ሚኒስቴር እንደሚለው በተለይ ባለፉት ሃያ ዓመታት በጣሙን እየተፋጠነ የመጣው የሁለቱ ወገን የንግድ ልውውጥ ዘንድሮ የአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላርን ወሰን ያልፋል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ቻይና አፍሪቃ ውስጥ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስራ ላይ ማዋሏ እርግጥ ምዕራቡን ዓለም ማስቆጨቱና ማስቆጣቱ አልቀረም። ይሁንና በርካታ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች የሰብዓዊ መብት ረገጣንም ሆነ ሙስናን የማታነሣውን ቻይናን ይመርጣሉ። ውዳሤ ሲያሰሙ መኖራቸውም እንግዳ ነገር አይደለም።

ሕዝባዊት ቻይና በማዕከላዊው እሢያ የቀድሞ ሶቪየት ሬፑብሊኮች በኡዝቤኪስታን፣ ታጂኪስታንና ኪርጊስታን፤ እንዲሁም በፓኪስታን ወዘተ.ም የንግድ ትስስሯን እያጠናከረች ነው የሄደችው። ዛሬ በአካባቢው ሸቀጣ-ሸቀጦችና የቀላል ኢንዱስትሪ ምርቶቿ የማይራገፉበት ቦታ የትም አይገኝም። ቻይና በአውሮፓም ቢሆን በተለይ በጨርቃ-ጨርቅ ምርቶቿ ርካሽነት ከኢጣሊያ እስከ ስፓኝና ጀርመን ድረስ ብዙዎች የአልባሣት ፋብሪካዎችን ለክስረት ማብቃቷና ባለፉት ዓመታት የዘርፉ ስራ አጥ ቁጥር እንዲጨምር ማድረጓም ይታወቃል። ይህ እንግዲህ በምርቱ መስክ ሲሆን አሁን በመዋቅራዊው ግንባታ ረገድ በፖላንድ እንደሚታየው አዲስ በር መከፈቱ ምናልባት ለበለጸጉት የአውሮፓ አገሮች ራስ ምታት ሆኖ የሚቆይ ነገር ነው የሚመስለው።

እንደሚታወቀው ፖላንድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከኡክራኒያ ጋር በጋራ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አሰናጋጅ አገር ናት። እናም የስፖርቱ አፍቃሪዎችና ደጋፊዎች ከመላው አውሮፓ ወደ ፖላንድና ኡክራኒያ ከመጉረፋቸው በፊት በዋና ከተማይቱ በዋርሶውና በሎጅ መካከል የሚዘረጋው አዲስ ፈጣን አውራ ጎዳና ተሰርቶ ማብቃቱን ትፈልጋለች። መንገዱን የሚዘረጋው ከአንድ ዓመት በፊት በዋርሶው የቀረቡ ሁለት ጨረታዎችን ያሽነፈው የቻይና መንግሥት የምድር ባቡር ተቋም ተቀጥላ ኩባንያ ኮቬክ፤ ማለት የቻይና የባሕር ማዶ ኢንጂነሪንግ ድርጅት ነው።

ይህን መሰሉ የአውሮፓ ሕብረት ታላቅ ፕሮዤ ለአንድ የቻይና ኩባንያ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ኮቬክን ተመራጭ ያደረገው ለግንቢያ የጠየቀው ክፍያ በአውሮፓ የተሻለ ነው ከተባለው ሲነጻጸር በሲሶ ዝቅ ያለ፤ ማለት ሰላሣ በመቶ የረከሰ ነው። ይህ ,ደግሞ ከብራስልሱ የአውሮፓ የግንቢያ ማሕበር አንጻር ፉክክርን ማዛባት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ማሕበሩ የቻይናው ኩባንያ ኮቬክ ርካሽ ዋጋ ለመጠየቅ የቻለው በመንግሥት የሚደገፍ በመሆኑ ነው ባይ ነው።

“የኛ ኩባንያዎች እንበል በ 500 ሚሊዮን ዶላር የመንግሥት ዕርዳታ ቢደገፉ እንኳ የቻይና ኩባንያዎች ይበልጥ ርካሽ ዋጋ ለማቅረብም ይችላሉ። እንግዲህ ኩባንያዎቻችን ከሕዝባዊት ቻይና ጋር ፍትሃዊ የሆነ ፉክክር ለማድረግ አይችሉም ማለት ነው”

ይህን የሚሉት የአውሮፓው የግንቢያ ማሕበር ሊቀ-መንበር ኡልሪሽ ፔትሶልድ እንደሚያምኑት ቻይና የጀርመንንና የሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ኩባንያዎችን በተሰላና አንዳንዴም ፍትሃዊነቱ አጠራጣሪ በሆነ መንገድ ከምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ እየፈነቀለች ነው። በነገራችን ላይ የጀርመን የምጣኔ-ሐብት የምሥራቅ ኮሚሢዮን ጉዳዩን አጥንቶ የደረሰበት ድምዳሜም ከዚህ አይለይም።

“እርግጥ ነው ቻይና አሁን በኢንዱስትሪ በበለጸገው የምዕራብ አውሮፓ ክፍል የተፈጠረውን ቀውስ የገበያ ድርሻዋን ለማሻሻል ትጠቀምበታለች። ለግንቢያው የሚወጣው ገንዘብ ርካሽ መሆኑ ከገበያ ኤኮኖሚ ስሌት አንጻር ያልተጋነነ ቢሆን መቀበሉ ባላዳገተ። ነገር ግን በከፊል ለ 15 ዓመት የተመደበ ከ 1,5 እስከ 2 በመቶ የወለድ ወለድ ስላለበት ሁኔታውን እንዲህ አያደርገውም። እናም ከቻይና በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ በገበያ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የወለድ ተመን ነው ብሎ ለማሳመን ጨርሶ አይቻልም”

ይህን የሚሉት ተሰናባቹ የጀርመን የምጣኔ-ሐብት የምሥራቅ ኮሚሢዮን ሊቀ-መንበር ክላውስ ማንጎልድ ናቸው። ይሁን እንጂ በተለይ በዛሬው የቀውስ ሰዓት ለመካከለኛና ደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት የቻይናን ያህል ርካሽ ወጪ የሚጠይቅ ወገን የትም አይገኝም። በምሥራቃዊው የአውሮፓ ሕብረት አካባቢ በኤኮኖሚዋ ታላቋ የሆነችው ፖላንድም ብትሆን ምንም እንኳ ያለፈው አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ ዓለምአቀፉ ቀውስ ሳያግደው ቢያድግም በሥራ አጥነት ትግል ተወጥራ ነው የምትገኘው።

ከዚህ አንጻር ቻይና የምትፈጥረው የስራ ቦታ በደስታ ተቀባይነት የሚያገኝ ነው። ከዚሁ ሌላ በቀውስ ከባድ ክስረት ላይ የወደቁት ግሪክን የመሳሰሉት የሕብረቱ አገራትም የቻይናን መዋዕለ-ነዋይ አመስግነው ነው የሚቀበሉት። በተለይም ጊዜው የምዕራቡ ወገን የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ቁጥብ እየሆኑ የሄዱበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በቅርቡ በከባድ የበጀት ኪሣራ የተነሣ ከለየለት ውድቀት አፋፍ ላይ ደርሳ የነበረችውን ግሪክን ካነሣን የሕብረቱ አባል አገር ከቻይና ጋር ስልታዊ ሽርክና የመሰረተችው ለነገሩ ገና ከሶሥት ዓመታት በፊት ነበር።

መንግሥታዊው የቻይና የትራንስፖርት ኩባንያ ኮስኮ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የፒሬውስን የኮንቴይነር፤ የዕቃ ወደብ ተግባር ያካሂዳል። የተሰሎንቄ ወደብም እንደሚከተል ነው የሚጠበቀው። የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ በቅርቡ ባለፈው መስከረም ወር አቴንን በጎበኙበት ወቅት አገራቸው የግሪክን የመንግሥት የብድር ዕዳ ለመግዛት እንደምትፈልግም ተናግረው ነበር።
ይህ የቻይና መሯሯጥ ደግሞ ያል ምክንያት አይደለም። የግሪክ የመዋዕለ-ነዋይ አራማጅ ተቋም ስራ አስኪያጅ ክሪስቶስ አሌክሣኪስ እንደሚሉት ግሪክ ቻይና ከአውሮፓ ጋር ለምታደርገው ንግድ ዋነኛዋ መተላለፊያ ድልድይ ናት። አገራችው ከቻይና ጋር ባላት ሽርክና በገንዘብ ብቻ ሣይሆን በዕውቀት ጭምር እንደምትጠቀምም ነው የሚያምኑት።

“ሌላም ለኛ የሚበጅ ጠቃሚ ምክንያት አለ። ቻይና ግሪክ ውስጥ መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ ቁርጠኝነት አሳይታለች። ሌሎች ፈርተው ወደ ኋላ በሚሉበት ሰዓት የቻይናው ኩባንያ ኮስኮ አውሮፓ ውስጥ ጠቃሚ የሆነ የትራንስፖርት ፕሮዥ ለማንቀሳቀስ መነሣቱ የሚደነቅ ነው”

ክሪስቶስ አሌክሣኪስ የቻይና ዕርምጃ ሌሎች የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችም ወደ ግሪክ እንዲያተኩሩ የሚያነቃቃ እንደሚሆን ተሥፋ ያደርጋሉ። ቻይና ሰርቢያ ውስጥም በሰፊው እየተንቀሳቀሰች ነው። በፊታችን ሚያዚያ ቤልግሬድ ውስጥ የዳኒዩብ ወንዝ ድልድይ መታነጽ ይጀምራል። ከወጪው 85 በመቶው የቻይና መንግሥታዊ የውስጥና የውጭ ንግድ ባንክ በብድር መልክ የሚያቀርበው ነው። ይሄው ባንክ ለሞንቴኔግሮም የቻይና መርከብ ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ አበድሯል። እርግጥ በርካሽ ወለድ!

የቻይና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በዚህ ብቻም አያበቃም። ቻይና ከክሮኤሺያ ጋር በጋራ የዋና ከተማይቱን የዛግሬብን አየር ጣቢያ አዲስ ለማነጽ ስትስማማ ቡልጋሪያ ውስጥም ሶፊያ አጠገብ አንድ የቻይና ኢንዱስትሪ ክልል ለማቆም ተወስኗል። ሩሜኒያ ውስጥ ደግሞ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ሲታቀድ በመዋቅራዊ ግንባታ፣ በኤነርጂ፣ በእርሻ ልማትና በማዕድን ዘርፍ ተጨማሪ መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ ይታሰባል። በነገራችን ላይ ሩሜኒያ ውስጥ ከዛሬው አሥር ሺህ የቻይና ኩባንያዎች ይገኛሉ።

የአውሮፓን ሕብረት የውስጥ ገበያ በተመለከተ የቻይና ግስጋሤ እዚህ የራስ ምታት ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ሲሆን ኩባንያዎቹ በመንግሥት አለመደገፋቸው መረጋገጡ ወደፊት መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ ቅድመ ግዴታ እንዲሆን ለማድረግ ይታሰባል። ከዚሁ ሌላ ፖላንድን የመሰሉ የአውሮፓ ሕብረት ሃገራት በመንግሥት የሚደገፉትን የቻይናን ኩባንያዎች ከመሳሰሉት ከተባበሩ የብራስልስን ድጎማ በመሰረዝ በገንዘብ ለመቅጣት ማቅማማቱም አለ። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል የቻይናን የገበያ ግፊት መቋቋም መቻሉ ለጊዜው በጣም የሚያጠያይቅ ነው።

መሥፍን መኮንን